
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ማሕበረሰባዊ ስሪት የአንድን ትውልድ ማንነት እና ምንነት ወጥ አድርጎ ይቀርጻል፡፡ የግለሰቦች ድርጊት እና ስሜት የፈጠራቸው እና ያነጻቸው ማሕበረሰብ ነጸብራቅ ነው፡፡ ትህትና፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ ሰብዓዊነት እና መሰል በጎ ምላሾች ከመሬት አይበቅሉም፡፡ ትዕቢት፣ ጥላቻ እና እቡይነትም የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪያት አይደሉም፡፡ ክፉም ሆነ መልካም፣ እኩይም ሆነ ሰናይ፣ ሰብዓዊነትም ሆነ አረመኔያዊነት የሰው ልጅ በልምምድ የወረሳቸው እና ከማሕበረሰቡ የተማራቸው ባህሪያት ናቸው፡፡
የአማራ ሕዝብ ሲወድህም ሲጠላህም ፊት ለፊት ነው፡፡ ተደብቆ ጥቃት ተሸሽጎ መውጋትን አያውቅም፡፡ የአማራ ሕዝብ የሰው ልጅ ሁሉ ወንድሙ ኢትዮጵያ ሀገሩ ናት፡፡ እስከሚደክመው ሠርቶ እስከመሸበት አቅንቶ፤ ከሰብዓዊነት ጋር ጸንቶ እና ከአራዊቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን ከጥንት ጀምሮ ተለማምዶታል፡፡ ለሰብዓዊነቱ ገደብ ለርህራሄው ወሰን ስለሌለው ከሀገር አልፎ ድንበር ተሻግሮ ለዓለም ሕዝቦች ነጻናት እና እኩልነት መከበር መታገሉን ታሪክ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡
ዛሬ ላይ ደጋግመን የምናያቸው እና የምናስተናግዳቸው የንጹሃን ዜጎች ግድያ እና ጥቃት ተራ ወንጀሎች አይደሉም፡፡ የጥላቻው መነሻ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጽናት እና የዘመናት ነጻነት የአማራ ሕዝብ የከፈለው ልክ አልባ መስዋእትነት የሚያበሳጫቸው ኅይሎች የዘረጉት የተሳሳተ ትርክት እና ጥላቻ ውጤት ነው፡፡ የውጭ ኅይሎችን ጥላቻ እና ሴራ እንዲያስፈጽሙ ተልዕኮ የተሰጣቸው የገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች ደግሞ መዋቅራዊ አደረጃጀት ፈጥረው ከ1983 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ሲያካሂዱ ተስተውሏል፡፡
ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍናን እንደመታገያ መስመራቸው ይዘው የተነሱት ሽብርተኛው ትህነግ፣ ኦነግ እና መሰል የትግል ድርጅቶች አማራን የጥላቻቸው ማዕከል አድርገው ብቅ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በግልጽ የአማራን ሕዝብ ጠላት ብለው በማኒፌስቷቸው ፈርጀው ትግል ሲጀምሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዘር ተኮር ጭፍጨፋን የሚደግፉ እና የሚያበረታቱ የተሳሳተ ትርክት ሲያሰራጩ ኖረዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ ለዚህ የተሳሳተ ትርክት እና ጥላቻ እውቅና በመስጠት የዘር ማጽዳቱ ሂደት መዋቅራዊ አደረጃጀት ተፈጠረለት፡፡ በክልሉ ለሚኖሩ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እውቅና እና ውክልና የሰጠው አማራ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማራዎች እውቅና እና ውክልና ተነፍጓቸው በየዘመኑ የፈሰሰው ደማቸው ደመ ከልብ ሆነ፡፡ ለዘመናት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር በደስታ፣ በሃዘን፣ በመከራ እና በመስዋእትነት ባጸናት ሀገሩ እንደ ባይተዋር እና መጤ እየተቆጠረ ሲሳደድ፣ ሲገደል እና ሲጨፈጨፍ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም፡፡
በጉራ ፈርዳ በጅምላ ተጨፍጭፈው በጅምላ መቃብር ያረፉት አማራዎች አሁን ድረስ በወለጋ በጅምላ ተጨፍጭፈው በጅምላ ሲቀበሩ እያየን ነው፡፡ ትናንት ለፖለቲካዊ ጨዋታ የጀመሩት የሃሰት ትርክት እና የሃሰት ጥላቻ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ የፖለቲካ ቁማር ማስያዣያ ሲሆን እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ የዘር ማጽዳት ሂደት የሚቆመው ምናልባትም ሕገ መንግሥታዊ መዋቅር የተዘጋጀለት ሕገ መንግሥት ሲሻሻል ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡
በየጊዜው የሚከሰተውን ማንነትን ማዕከል ያደረገ የጅምላ ግድያ ማውገዝ ሰብዓዊነት ቢሆንም ድርጊቱን ያስቆመዋል ብሎ ማሰብ ግን ምናልባትም የጥላቻውን ልክ ካለማወቅ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሰው ተፈጥሮ ሰው ያሰጠላው ቡድን በልመና ይመለሳል በእርግማን ይከስማል ብሎ ማሰብ ሞኝ ያደርጋል፡፡ የችግሩ ምክንያት መዋቅራዊ ጥላቻ በመሆኑ መዋቅራዊ ምላሽ ይጠይቃል፡፡
ማንነትን መሰረት ያደረገው ተደጋጋሚ የጅምላ ግድያ የከፋ የሚያደርገው የጥቃቱ ማዕከላት ንጹሃን እና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው ነው፡፡ ተናግረው ማስረዳት የማይችሉ ሕጻናት፣ ሮጠው የማያመልጡ አዛውንት፣ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እናቶች እና ትጥቅ ፈትተው የተቀመጡ አባቶች ናቸው ተጠቂዎቹ፡፡ ወገንን ማጥቃት ጀግንነት አይደለም እንጂ ጀግንነት ቢሆን ኖሮ ገዳዮቹ ተጠቂዎቹን ፊት ለፊት ለመግጠም የሚያስችል ወኔ እና ልብ የላቸውም፡፡
አዛውንቶችን መግደል በየትኛውም መንገድ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ ህጻናትን ማረድ በምንም መልኩ ቢለካ ጀግንነትን አያሳይም፡፡ ሴቶችን ማሳደድ ወንድ አያሰኝም፡፡
ስለማያውቁት እንጂ የሚገድሉት ሕዝብ ቀበቶ የፈታ ወንድ እንኳን ተደብቆ አያጠቃም፡፡ ቀን እርቆት እና ሰማይ ተደፍቶበት እንጂ አጥቂዎቹ በፊቱ ከቶም ሞገስ ያላቸው ሆነው አይደለም፡፡ ፍትሕ አለ መስሎት እንጂ፤ ተጠያቂነት የሚኖር መስሎት እንጂ እንዲህ ፍትሕ አለመኖሩን ቢያውቅ እና ተጠያቂነት አለመኖሩን ቢረዳ በጀምላ መሞትን ምርጫው አያደርግም ነበር፡፡
“ካንድ ላይ ይውላል ምርት እና ገለባ፣
ነፋስ እስኪለየው ገደል እስኪገባ” እንዲሉ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ውስጥ ይገባ ይሆናል እንጂ ፈጽሞ ግን አይከስምም፡፡ ምርቱ ከገለባው የሚለይበት ጊዜም እሩቅ አይሆንም፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/