
ደብረ ማርቆስ፡ ሰኔ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በነባር ባህሏ እና በእውነተኛ ማንነቷ ላይ ተመስርታ የምትሠራ ሀገር ጽኑ ናት፡፡ ትውፊቱን፣ ልማዱን እና እሴቱን እየተማረ እና እያወቀ ያደገ ትውልድ ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ቱባ ባህል፣ እልፍ ሀገር በቀል እውቀት፣ ጥንታዊ ጥበብ እና አኩሪ የታሪክ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም በሚገባው ልክ ተሰንዷል፤ በተሠራው ልክ ለትውልዱ ተዋውቋል ለማለት ግን ይከብዳል፡፡
ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ በጥበብ እና በሀገር በቀል እውቀቶች አንቱታን ካተረፉላት አካባቢዎች መካከል አንዱ ጎጃም ነው፡፡ ጎጃም በትርፍ አምራችነቱ ብቻ ሳይሆን በጥበቡም ዓለም ያውቀዋል፡፡ ጎጃም አንጋፋዎቹን የጥበብ ሰዎች ፦ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ አቤ ጉበኛን እና ሌሎችንም ያፈራ ነው።
ጎጃም ሲነሳ የአርበኞቹ የእነ በላይ ዘለቀ ስም በታላቅ ጀግንነት በትውልዱ ሲዘከር ይኖራል፡፡
ጥበብ እና ሀገር በቀል እውቀት ተወልዶ ያደገበት ጎጃም ግን ለዘመናት ጥበቡን፣ ባህሉን፣ ወጉን እና ታሪኩን በአንድ ሰንዶ ለተተኪው የሚያቆይበት የባህል ማዕከል አልነበረውም፡፡ የጎጃም ባህል ማዕከል ግንባታ በሃሳብ ደረጃ ከ15 ዓመታት በላይ ተጠንስሶ ቢቆይም እውን የሆነው ግን በቅርቡ ነበር፡፡ የባህል ማዕከል ግንባታው ከተጀመረ ሦስት ዓመታት አልሞላውም ያሉን የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው ናቸው፡፡ ግንባታው 47 በመቶ መድረሱንም ነግረውናል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ወቅታዊው የግንባታ ቁሳቁስ እጥረት ሂደቱን ቢፈትነውም ችግሩን ተቋቁሞ በታቀደለት የጊዜ መርሃ ግብር ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ 2 ሺህ 500 ሰዎችን የሚይዝ የሲኒማ እና የስብሰባ አዳራሽ የሚኖረው ግንባታው በየአካባቢው እና በግለሰቦች እጅ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን በማሰባሰብ ለትውልድ ጠብቆ ያቆያል ተብሏል፡፡
ትውልድ የሚገነባው ካለፈ ታሪኩ፣ ከነባር ባህሉ እና ከእውነተኛ ማንነቱ ሲቀዳ ነው ያሉት አቶ አብርሃም የባህል ማዕከሉ የአማራ ሕዝብ የባህል ማዕከል እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው ጎጃም እና አካባቢው ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ታላላቅ አበርክቶዎች የነበሯቸውን ሰዎች ያፈራ መኾኑን ገልጸው “የምንገነባው የጎጃም ባህል ማዕከል ለኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲ ማዕከልም ነው” ብለዋል፡፡
የጎጃም ባህል ማዕከል ግንባታ ሲጀመር 450 ሚሊየን ብር ወጭ ይደረግበታል ተብሎ ቢታሰብም አሁን ካለው የግንባታ ቁሳቁስ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ከታቀደለት በላይ ወጭ ሊጠይቅ እንደሚችልም ዋና አስተዳዳሪው ገለጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/