በባሕር ዳር ከተማ የባጃጅ ወይም የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 2:00 ብቻ እንዲኾን ተገደበ፡፡

242

ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ምክር ቤቱ በአደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቋል።
ከተወሰኑ ልዩ ልዩ መሠረታዊ ውሳኔዎች መካከል ደግሞ የመጀመሪያው የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን ይመለከታል ብሏል።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አሁን ካለንበት ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ለከተማው ሰላምና ደኅንነት ሲባል ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውም የባጃጅ ወይም የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ እስከ ምሽቱ 2:00 ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም የባጃጅ ተሽከርካሪ ላይ ለሚወሰድበት ማንኛውም ቅጣትና እርምጃ ኀላፊነቱን ባለቤቱ ወይም አሽከርካሪው ይወስዳል ነው ያለው።
ማንኛውንም ወንጀል መከላከል የሚቻለው የኅብረተሰብ ተሳትፎ የላቀ ሲኾን መኾኑን የገለጸው ምክር ቤቱ የከተማው ነዋሪ እንደተለመደው ጥቆማዎችን በመስጠትና ከሕግ አስከባሪዎች ጎን በመቆም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱ “በፀጥታ ኀይላችን ብርቱ ትግል፣ በሕዝባችን የማይቋረጥ ደጀንነት የአፍራሽ ኀይሎች ምኞት አይሳካም ” ብሏል፡፡ መረጃው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

Previous article“የሀገሪቱ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ አሁንም የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው!!” ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
Next articleሚሊሻው የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር ተልእኮውን በአግባቡ መፈፅም እንደሚገባው ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ አሳሰቡ።