“ድሮ የሰው ሀገሩ ምግባሩ፣ ዛሬ የሰው ሀገሩ ዘሩ”

149

ሰኔ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምግባር ካለህ የትም ወገን አለህ፣ ምግባር ካለህ የትም ዘመድ አለህ፣ ምግባር ካለህ የትም ትኖራለህ፣ ከየትኛውም ጋር ትወዳጃለህ፡፡ ሰው በሰውነቱ ይከበራል፣ ሰው በሥራው ልክ ይዘከራል፡፡

በዚህች ታሪክ ባገነናት፣ ደምና አጥንት ባጸናት፣ የፈጣሪ ስም በሰርክ በሚጠራባት፣ ሰውና መላዕክት በጋራ በሚጠብቋት፣ ወተትና እሸት የሚያፈስስ ዝናብ በሚዘንብባት፣ የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ በታደላት፣ የተጨቆኑት እናታችን እያሉ በሚጠሯት፣ የሰው ዘር በተገኘባት፣ ጥበብ በበዛላት፣ ደግነት በተቸራት፣ ዓይኖች ኹሉ ሊያይዋት በሚመኟት፣ ጀሮዎች ኹሉ ስለ እርሷ ለመስማት በሚቋምጡላት፣ እግሮች ኹሉ ምድሯን ለመርገጥ በሚጓዙላት ምድር ሰው በሰውነቱ ተከብሮ ኖሮባታል፣ ጎጆ ቀልሶ ልጆች ወልዶ ዓለም አይቶባታል፣ አርሶና ነግዶ ሀብት አካብቶባታል፣ ሞቶም በክብር አርፎባታል፡፡

ፍትሕ ያጡት ፍትሕን ፍለጋ ባሕር እያቋረጡ ወደ እርሷ ገስግሰዋል፣ በረከት የፈለጉ ዱር ጥሰው፣ በረሃ አቋርጠው ወደ እርሷ መጥተዋል፣ በምድሯም በደረሱ ጊዜ በማይጠገበው አየሯ፣ ታይቶ በማይሰለቸው መልከዓምድሯ፣ በፍቅር ኖረዋል፣ በረከት አግኝተዋል፣ ከአንቺ አይለየን ሲሉ በምድሯ ቀርተዋል፡፡ ነብሳቸውን እርሷን ወደ ሚወዳት ፈጣሪ ሰጥተው፣ ስጋቸውን በአፈሯ አሳርፈዋል፡፡

ሰው ኹሉ የአዳምና የሔዋን ዘር ነው ተብሎ ይታመንባታል፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ይከበርባታልና ከየት መጣህ ሳይኾን እንኳን ደኅና መጣህ ብለው እግሩን ያጥቡታል፣ ፍትፍት ፈትፍተው ያጎርሱታል፣ አፈር ስኾን ብላ እያሉ ይመግቡታል፣ እንግዳቸው እንዲበላላቸው አፈር ስኾን፣ ስሞት ስቀበር ነው ልመናቸው፣ ስሞትልህ እያሉ ይለምኑታል፡፡

ከማሩ ገንቦ ቀድተው፣ ከካቦው ወተት አዝንብለው ያጠጡታል፣ ከአልጋቸው ወርደው የደከመ ጎኑን ያሳርፉታል፣ ለምን ሰው ወደተገኘባት፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ወደሚከበርባት፣ ታላቅ ሀገር መጥቷልና፡፡ ከእንግዳ ጋር በረከት ይመጣል ብለው ያምናሉ፡፡ እንግዳንም አብዝተው ይወዳሉ፡፡ ፈጣሪም ለእንግዳ ተቀባዮች በረከት ይሰጣል፣ ጎተራቸውን ይሞላል፡፡ እንግዳ የሚወደድባት፣ ሃይማኖት የሚጸናባት፣ ፈጣሪ የሚመሰገንባት፣ ስሙ የሚጠራባት ምድር ናት ኢትዮጵያ፡፡

ኢትዮጵያዊነት የተራበን ማጉረስ፣ የታረዘን ማልብስ፣ ለተቸገረ ከዓይን ጥቅሻ፣ ከከንፈር ንክሻ ፈጥኖ መድረስ፣ ርስት ለመውረስ፣ ሀገር ለማርከስ የመጣን በአሻገር መመለስ፣ ለወሬ ነጋሪ ሳይተው መደምሰስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩና ለክብሩ ሞትን የሚንቅ፣ በሀገሩና በክብሩ የተነሳበትን በአንድነት ክንድ የሚያደቅ ኃያል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት መፈቃቀር፣ ኢትዮጵያዊነት መከባበር፣ ኢትዮጵያዊነት ከራስ በላይ ለሰው መኖር ነው፡፡ ፍትሕን ሽተው፣ መከራና ስቃይን ሸሽተው የመጡት ኹሉ በኢትዮጵያ ነገሥታት አቀባባል ተደርጎላቸዋል፣ የሚያርሱት መሬት፣ የሚያርፉበት ቤት ተሰጥቷቸው በሰላም ኖረዋል፡፡ መጓጓዣ ፈረስ ተችሯቸዋል፣ የኢትዮጵያን ክብር ጠብቃችሁ፣ በኢትዮጵያ ኮርታችሁ፣ ሀገራችን ናት ብላችሁ ኑሩ ተብለዋል፡፡እንደተባሉትም በፍቅርና በክብር ኖረዋል፡፡ ሀገራችሁ ሩቅ፣ ከእኛ ጋርም ዝምድና የላችሁም አልተባሉም፡፡ ሰዎች ናቸው በሰውነታቸው ተከብረው፣ በክብር ኖረዋል፡፡

አበው የሰው ሀገሩ ምግባሩ ይላሉ፡፡ ምግባር ካለው ሀገሩ የትም ነው፡፡ ምግባር የሰው ልጅ ሀገር ነው፡፡ ምግባር በሰላምና በፍቅር ያኖራል፡፡ ምግባር በፍቅር ያስተሳስራል፡፡ ምግባር ያስከብራል፡፡

የቀደሙት ኢትዮጵያውያን የሰው ሀገሩ ምግባሩ በሚለው ብሒላቸው በኢትዮጵያ በየትኛውም ጫፍ ሄደው ጎጆ ይቀልሳሉ፤ ልጆች ይወልዳሉ፤ ሃብት ያፈራሉ፤ በየትኛውም ጫፍ ቢኾን ከኢትዮጵያ ምድር እስካለቀቁ ድረስ ሀገራችን፣ እናታችን እያሉ ኑሮ ይመሠርታሉ፡፡

ከእናት ላይ ተከፍሎ የአንተ፣ ተከፍሎ የእኔ ነው የሚባል ነገር የለም፤ እናት የልጆቿ ናት፤ እናት የኹሉም ናት፡፡ ለዚያም ነው፤ በእናታቸው መሬት እንደ አሻቸው ሕይወት የመሠረቱት፡፡ በአፈሯ የተወለዱት ብቻ ሳይኾን ከእርሷ ያልተወለዱት በፍቅር ለመኖር የፈለጉትና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትም በፍቅር ኖሯል፡፡ ምግባራቸው ምሥጉን ነውና ፍቅር እንጂ ጥል አያውቃቸውም፡፡ ወዳጄ ተባብረን እናልማ፣ መልካም ጎረቤት እንሆናለን ይባባሉ፡፡ በአንድነትም ይኖራሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን በዚህ መልካም እሳቤያቸውና እሴታቸው ወሰን ሳይከልላቸው፣ ሃይማኖት ሳይገድባቸው፣ አካባቢ ሳያለያያቸው ተዋህደው በውድ ሀገራቸው በመዋደድ ኖረዋል፡፡

በሰሜን የተወለደው፣ ደቡብ ሄዶ ይኖራል፣ ምዕራብ የተወለደው በምሥራቅ ያድጋል፡፡ ሀገሩ ናትና በመረጠው ሄዶ መኖር መብቱ ነው፡፡ የሰው ሀገሩ ምግባሩ እንጂ ሌላ የሚያስፈልገው ነገር የለም ይላሉ፡፡ ምግባር ቢያጣ እንኳን በሀገር ባሕል፣ በሀገር ወግና ሥርዓት መክረው ያስተካክሉታል፤ በየቀየው ሕግና ሥርዓት እንዲተዳደር፣ ሰው እንዲወድ፣ ከሰው ጋር በፍቅር እንዲኖር ያደርጉታል እንጂ ዘርህ ከዘራችን፣ ሃይማኖትህ ከሃይማኖታችን፣ ቋንቋህ ከቋንቋችን አልገጠመምና ውጣልን፣ ሂድልን አይሉትም፡፡

አሁን ደገኛው ዘመን ተዳክሞ፣ ክፉ ዘመን መጥቶ፣ ክፉ ሐሳብ ተንሰራፍቶ፣ የሰው ሀገሩ ምግባሩ በሚባልባት ምድር የሰው ሀገሩ ዘሩ ይባል ተጀምሯል፡፡ ስምህ ከስማችን፣ ዘርህ ከዘራችን፣ ሃይማኖትህ ከሃይማኖታችን አልተገናኘም እና ውጣልን፣ ሂድልን፣ ቦታ ልቀቅልን ይባል ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ድሮ ከባሕር ማዶ እየተሻገረ በውቧ ኢትዮጵያ መኖር እፈልጋለሁ ያለወ ኹሉ በሰላም እንዳልኖረባት፣ ጎጆ ቀልሶ ልጆች እንዳልወለደባት፣ ሃብት እንዳላፈራባት ኹሉ ዛሬ ግን በአፈሯ የተወለደው እንኳን በወሰን ተከለል ይባል ከጀመረ ቆየ፡፡

ሰው ከእናቱ ጉያ ወጥቶ ወደየት ይሄዳል? የትስ ይኖራል? ሀገሩ ኢትዮጵያ ናትና በኢትዮጵያ በመረጠው መኖር እየቻለ፣ በዚህም ኖሮና አድጎ ዛሬ ላይ ውጣልን ይባላል፡፡ ምግባር በገነነባት ዘመን ምድሯን ፍቅር ያረሰርስባት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ አንድነት የጠነከረባት፣ መተሳሰብ ያየለባት፣ መተሳሰብ የጎለበተባት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጥቂቶች የጀመሩት የዘር መንፈስ፣ የክፋት መንገድ ብዙዎች ደመ ከልብ አደረጋቸው፡፡ እናትና ልጅን ለያያቸው፣ ልጆችን ያላሳዳጊ፣ አዛውንቶችን ያለ ጧሪ አስቀራቸው፡፡

ከሚወዳት ሀገሩ፣ ልጆች ከወለደባት፣ ሀብትንና ንብረት ካፈራባት ቀየው ውጣ እየተባለ በክፉዎች ሰይፍ ይመታል፡፡ በግፍ ይሞታል፡፡ ሀገሩን ጥሎ፣ ቀዬውን ለቆ መሄጃ የለውምና የክፋት ውርጅብኝ እየወረደበት፣ የደም ማዕበል እየፈሰሰበት ይኖራል እንጂ፡፡ ዘር በሚል ብሒል ብቻ ሐጥያት ያልተገኘባቸው፣ በደል ያልተቆጠረባቸው ሕጻናት ተቀጽፈዋል፣ እናቶች በሰቀቀን ኖረዋል፣ ከልጆቻቸው ርቀው ሄደው ተገድለዋል፤ ልጆቻቸው በገፍ ሲደሉ በሰቀቀን ውስጥ ኾነው ተመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጋት በምግባር መኖር እንጂ፣ በዘር መታጠር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በምግባር ሲኖሩ ጠላት ፈርቷቸዋል፣ ገብሮላቸዋል፣ በምግባራቸው ተግባባተው፣ አንድ ኾነው፣ በአንድነት ዘምተው ሀገር አስከብረው፣ ድንበር አስጠብቀው ኖረዋል፡፡ ከሰውነት የተለየ ዘር ካለህ ብቻ ዘርህ ከዘሬ አይገጥምም በል፣ ሰው እስከኾንክ ድረስ ግን ሰው ከመኾን የዘለለ ዘር የለህም፡፡

ዘር እየቆጠርክ የገደልካቸው፣ ሃይማኖት እየነጠልክ ያሳደድካቸው ደም ይፋረድሃል፤ እንቅልፍ ያሳጣሃል፣ ጊዜ ዳኛና ጀግና ነውና አንተንም ለግፍ ያቀርብሃል፤ በሰፈርክበት ትሰፈራለህ፣ በመዘንክበት ሚዛን ትመዘናለህ፣ መልካሙን ብቻ አድርግ፡፡ ክፉውን ራቀው፣ አትቅረበው፣ በሕዝብ ዘንድ እንዳያርፍ ራቅ አድርገህ ጣለው፡፡ ምግባርህ አሳምር፣ በምግባርም ኑር፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“የጋራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ማቆም የትውልዱ ኅላፊነት ነው” የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር)
Next article“የሕግ ማስከበሩ ሥራ ለሽብር ተልዕኮ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መልክ ያስያዘ ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ