
ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የተራራ ሰንሰለቶቹ ስብጥር እውቅ የምህንድስና ጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ይመስላሉ፡፡ ብርቅ እና ድንቅ የኾኑት የብዝሃ ሕይዎት ሃብቶቹ አካባቢውን በዓለም ሕዝብ ዘንድ እጅግ ተናፋቂ ያደርጉታል፡፡ ጉም እንደባዘቶ የሸፈነው ሰማይ የአካባቢው ልዩ ግርማ ሞገስ ነው፡፡
ሰማይ ጠቀስ ተራሮች እና የሚምዘገዘጉ ፏፏቴዎች የተጠመጠሙበት ፓርኩ በዓለም ጎብኝዎች ዘንድ ታይቶ አይጠገብም፡፡ ወጣ ገባ መልክዓ ምድር የበዛበት አካባቢው የአፍሪካ ጣሪያ፣ የምስራቅ አፍሪካ የውኃ ጋን እና የቀጣናው የብዝሃ ሕይዎት ሚዛን ማስጠበቂያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ለቀሪው ዓለም ሕዝብ ባይተዋር የኾኑት ዋልያ አይቤክስ፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ጭላዳ እና ቀይ ቀበሮ እትብታቸው ከኢትዮጵያዊው ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውጭ አልተቀበረም፡፡ አዕዋፍት ቅዝቃዜ ያየለበትን የአየር ጸባይ ተቋቁመው ከፍ ካለው ተራራ በላይ ከፍ ብለው እየበረሩ የሚያሰሙት ሕብረ ዝማሬ ለጎብኝዎቹ ተጨማሪ ሐሴትን ይሰጣል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ1958 ዓ.ም ክለላ ተደርጎለት ተቋቋመ፡፡ በ1962 ዓ.ም ደግሞ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚለውን ሕጋዊ ሰውነት እና እውቅና አገኘ፡፡ የፓርኩን ልዩ ተፈጥሯዊ እና ብዝሃ ሕይዎታዊ ሃብት ያጤነው የተባበሩት መንግሥታት  ድርጅት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ፓርኩን የዓለም ሃብት በማድረግ በ1978 (እ.አ.አ) መዘገበው፡፡
የአካባቢውን ብዝሃ ሕይዎት መመናመን ተከትሎ በ1988 ዓ.ም ብሔራዊ ፓርኩ አደጋ ውስጥ ከገቡት የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ኾኖ ቀረበ፡፡ ብሔራዊ ፓርኩን ከመጥፋት ለመታደግ በተደረገው ርብርብም ሰኔ/2009 ዓ.ም ከዩኔስኮ የጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው የዓለም ቅርሶች መዝገብ መካከል ወጣ፡፡ ነገር ግን 2011 ዓ.ም በፓርኩ ክልል ውስጥ በተከሰተ የእሳት አደጋ የፓርኩን ሕልውና ቋፍ ላይ ጣለው፡፡
በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን እሳት ለማጥፋት ከተደረገው ርብርብ ባልተናነሰ መልኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፓርኩን ብዝሃ ሕይዎት ለመመለስ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ነበር ያሉት  የስሜን ተራራዎች  ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ አበባው አዛናው ናቸው፡፡ 2012 ዓ.ም የአማራ ክልል ወጣቶች እና ሁሉም ዞኖች በጋራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደው ነበር ያሉት ኅላፊው በ2013 ዓ.ም በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በአማራ ክልል የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ችግኝ ተክለዋል ብለዋል፡፡


ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ከ87 በመቶ በላይ ጸድቋል ያሉት አቶ አበባው ፓርኩ ከደረሰበት የእሳት አደጋ አገግሞ ወደ ቀደመ የብዝሃ ህይዎት ገጽታው ተመልሷል ነው ያሉት፡፡ በ2014 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ከ50 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ በቅንጅት እና በትብብር እንደሚካሄድ የገለጹት የፓርኩ ኅላፊ የሰሜን ጎንደር ዞን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓትም በፓርኩ ችግኝ በመትከል እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡


ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
 
             
  
		