የማኅፀን በር ካንሰር ክትባት እጥረት በመኖሩ የ14 ዓመት ታዳጊዎች ብቻ እንደሚከተቡ ተገለጸ፡፡

262

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) በክልሉ ሁሉም ቦታዎች 14 ዓመት የሞላቸው 32 ሺህ 231 ልጃ ገረዶችን የማኅፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በዓለማችን በየዓመቱ ከ530 ሺህ በላይ አዳዲስ የማኅፀን በር ካንሰር ታማሚዎች ይመዘገባሉ፡፡ በኢትዮጵያም በየዓመቱ 7 ሺህ 500 ገደማ አዳዲስ የማኅፀን በር ካንሰር በሽታ ተጠቂዎች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ የአማራ ክልል በ2011 ዓ.ም ባለው መረጃ መሠረት 8 ሺህ 698 እናቶች ምርመራ አድርገው 1 ሺህ 131 እናቶች የቅድመ ካንሰር ምልክቶች ታይቶባቸዋል፡፡ ከነዚህ መካከል የ762 እናቶች ችግር የካንሰር ደረጃ ላይ በመድረሱ የሕክምና ድጋፍ እና ክትትል እያገኙ መሆኑን ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የማኅፀን በር ካንሰርን ለመከላከል ሦስት ዋና ዋና መንገዶች እንዳሉ ተመላክቷል፡፡ ክትባት፣ ለበሽታው በሚያጋልጡ የአኗኗር ዘይቤዎች ላይ ግንዛቤ መፍጠር እና ማከምና ማገገም ናቸው፡፡ ከእነዚህ የመከላከያ መንገዶች መካከል ተመራጭ ተደርጎ የሚወሰደውን ክትባት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ከ2015 እስከ 2017 (እ.አ.አ) የቅደመ ትግበራ ሙከራ በትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ ተካሂዷል፡፡ የሙከራ ትግበራው ተመራጭ መሆኑ ታይቶ ነበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃ ገረዶች ክትባት መስጠት የተጀመረው፡፡

በአማራ ክልል የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የማኅፀን በር ካንሰር ክትባት ለመስጠት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ቢሮው ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና አጠባበቅ ትምህርት፣ ፕሮሞሽን እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያ ወይዘሮ የሺወርቅ አሞኘ ጤና ቢሮው ለመጀመሪያ ዙር የማኅፀን በር ክትባት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ብቻ 32 ሺህ 231 ልጃ ገረዶችን ከጥቅምት 10-14 ቀናት 2012 ዓ.ም በሁሉም የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ይሰጣል ብለዋል፡፡

‹‹ክትባቱ በልጃ ገረዶቹ የግራ ክንድ ጡንቻ ላይ ይሰጣል፡፡ በክትባቱ ወቅት ከክትባቱ ጋር ያልተያያዘ ጥቃቅን የጎንዮሽ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ›› ያሉት ባለሙያዋ የተከተቡበት ቦታ ላይ መቅላት፣ ማበጥ እና ጊዜያዊ የሕመም ስሜት ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ከጭንቀት ጋር በተያያዘ የሚኖር የራስ ምታትም ሊያጋጥም ይችላል፤ ይህ ግን ዘላቂነት ያለው የጤና ችግር እንደማያመጣ ገልፀዋል፡፡

‹‹ከመድኃኒቱ ጥራት እና ደኅንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱት ስጋቶች አሉባልታዎች ናቸው፡፡ የመካንነትም ሆነ ሌላ ዘላቂ ችግር እንደማያስከትል ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ተሞክሮዎች አሉ›› ያሉት ባለሙያዋ የሉሎች ሀገራትን የ27 ዓመታት ተሞክሮችም ለአብነት አንስተዋል፡፡

ክትባቱ ዕድሜያቸው ከ9-14 ዓመት ለሞላቸው ልጃ ገረዶች በስድስት ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት እና ዘንድሮ የሚሰጡት የማኅፀን በር ክትባቶች 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃ ገረዶች ብቻ የሚሰጥ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ የመጨረሻው 14 ዓመት ዕድሜ ሳያልፋቸው ቅድሚያ ለመስጠት መሆኑን ቢሮው አሳውቋል፡፡
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የማኅፀን በር ካንሰር ክትባት 276 ሺህ 402 እና በሁለተኛው ዙር ደግሞ 264 ሺህ 749 (97 በመቶው) የሚሆኑ ልጃ ገረዶች ክትባቱን ወስደዋል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article“ከ139 የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድም ሴት የፓርቲ መሪ የለም:” ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድህን- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር
Next articleየገቢዎች ሚኒስቴር ሀሰተኛ ደረሰኝ ያትማሉ ያላቸውን ድርጅቶች ይፋ አደረገ፡፡