
ደብረ ብርሃን፡ ሰኔ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰኔ 2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም በአሸባሪው ሸኔ እና በትግራይ ወራሪ ሀይል ተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰበት ነው የኤፍራታና ግድም ወረዳ።
በወረዳው ባለፋት ተከታታይ 4 አመታት በእነዚህ የጥፋት ቡድኖች በደረሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የበርካቶች ህይወት መቀጠፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ለመፈናቀልና ለቁሳዊ ውድመት ኪሳራዎች የአከባቢው ማኅበረሰብ መዳረጉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ባሳዝን ገልጸዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በቅርቡ በሞላሌ የተቃጠሉ 125 ቤቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ባለፉት 4 አመታት አንድ ሺህ 79 የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል ብለው እነዚህ ቤቶች ተመልሰው ተገንብተው ነዋሪዎች በአከባቢያቸው ተረጋግተው ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲገቡ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመንግስትና በተለያዩ ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ርብርብ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በሸዋ የሰላምና ልማት ማህበር 50 ቤቶች እንዲሁም በመንግስት 2 መቶ 42 ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ግንባታቸው ወደ መጠናቀቁ እየደረሱ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅርቡ በሞላሌ የተቃጠሉ 125 ቤቶችንም ተስፋ ብርሃን ከተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ለመሥራት የቁሳቁስ ግዥ ሂደቶች መጀመራቸውንም አቶ ችሮታው ተናግረዋል።
በጉዳቱ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ቀበሌዎች አንዱ የካራቆሪ ቀበሌ ሲኾን የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አዲስ በረደድ በቀበሌው 2 መቶ 10 ቤቶች ተቃጥለው እንደነበረ አስታውሰው በአኹኑ ሰዓት በመንግስትና መንግስታዊ ባልኾኑ ድርጅቶችና በኅብረተሰቡ ርብርብ 83 ቤቶች ተገንብተዋል ብሏል።
ሸዋ የሰላምና ልማት ማኅበር ከቤት ግንባታው ባሻገር የእለት ሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግም ለአከባቢው ማኅበረሰብ እያደረገው ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ የቀበሌው አስተዳዳሪ አመስግነዋል።
በተመሳሳይ አስተያየታቸውን የሰጡን የካራቆሪ ነዋሪዎች መንግስትና ረጅ ድርጅቶች ማኅበረሰቡን መልሶ ለማቋቋም እየሠሩት ያለው ሥራ የሚበረታታና የነዋሪውን የተሰበረ ልብ የጠገነ እንደኾነ ገልጸው ይኹን እንጅ ከዚህ በኋላ መሰል ጥቃቶች በአከባቢው እንዳይከሰቱ የአከባቢው ሰላምና ደህንነት ላይ መንግስት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ባሳዝን በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኀይሎች በየጊዜው የሚነሱ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን በዘላቂነት ለማስቆም በወረዳው በሚገኙ 19 ቀበሌዎች ጋር ከሚዋሰኑ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ቀበሌዎች፣ ወረዳዎችና ከብሄረሰብ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አስተዳዳሪው ጥፋተኞችን ከሰላማዊው ሕዝብ ለመነጠል የሚያስችሉ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራዎችን የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችንና የሰላም ኮሚቴዎችን በማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ሥነጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/