“አሚኮ የጣቢያዎቹን ቁጥር እያሳደገ የአገልግሎት አይነቱን እያሰፋ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እና ወንድማማችነትን ለማስረጽ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል” የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ

102

ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሁለተኛ ቻናሉን “አሚኮ ኅብር” መደበኛ ስርጭቱን አስጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ላለፉት 27 ዓመታት የሚዲያ ዘርፍን ከመለማመድ ጀምሮ የራሱን አሻራ እስከማሳረፍ የደረሰ ሚዲያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለቤቱ ሕዝብ የሚያገለግለውም ሕዝብን የሆነ አዳጊ የሚዲያ ተቋም እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ አሚኮ በየጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የሕዝቡን ፍላጎት እና የሚዲያ ውድድር በግብዓትነት በመጠቀም ሁሌም በእድገት እና መሻሻል ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አሚኮ ሁሉንም የሚዲያ አይነቶች በመያዝ ሕዝብን የሚያገለግል የሕዝብ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በውስን ባለሙያዎች የሚዲያ ሥራ መስክ አገልግሎቱን በአማርኛ ቋንቋ እንደጀመረ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የጣቢያዎቹን ቁጥር እያሳደገ የአገልግሎት አይነቱን እያሰፋ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እና ወንድማማችነትን ለማስረጽ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ማገልገልና መሠረታዊ ኃላፊነትን መወጣት የጀመረው ከ17 ዓመታት በፊት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ብሔረሰቦችን ብዝኃ ልሳን እና ግብረ ብዙ በመሆን ሲያገለግል መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ አሚኮ በክልሉ ለሚነገሩ ቋንቋዎች ማደግ እና መስፋፋት ያበረከተው አስተዋጽኦ የማይተካ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የብሔረሰብ ቋንቋዎች የአየር ስዓት ጭማሪ እየተደረገባቸው ዛሬ ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል፡፡
አሚኮ በሁሉም ቋንቋዎቹ እና ሚዲየሞቹ ሕዝቡ ሁለንተናዊ ጉዳዮችን የሚናገርበት የባለቤቱ ልሳን ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በክልሉ ውስጥ ከሚነገሩ ቋንቋዎች በተጨማሪ ሀገራዊ መስተጋብሩን ለማጠናከር፣ የተዘሩ የሃሰት ትርክቶችን በማስተካከል፣ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጎለብት፣ ከመጠራጠር ይልቅ መገናዘብ እና አንዱ የሌላውን እውነታ መረዳት እንዲችል ሃብት እና አቅም ባገናዘበ መልኩ የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ተጨማሪ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለስርጭት እያበቃ በየጊዜው እድገት እያሳየ የሚገኝ ሚዲያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የውጭ ሀገር ቋንቋዎችን በጥናት እየለየ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ እንግሊዘኛ እና አረብኛ ዝግጅቶች ቀደም ብለው የተጀመሩ የአሚኮ ኅብር ጣቢያ አካል ሆነው የሚቀጠሉ ዝግጅቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
አሚኮ በይዘት ቀረጻ እና አቀራረቡ የራሱ ቀለም እና መለያ ያለው ሚዲያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የራሳቸው ፍኖት ካላቸው ሚዲያዎች አንዱ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከለውጥ በፊትም ሆነ በለውጥ ሂደቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካ፣ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እያለፈ ሲያገለግል ቆይቷልም ነው ያሉት፡፡
አሚኮ በአሁኑ ጊዜ 6 የራዲዮ፣ 2 የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና 4 ጋዜጦችን በማስተዳደር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የዘገባ ፍትሐዊነት እና ተደራሽነትን በክልሉ ውስጥ ማዕከል አድርጎ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ተጨማሪ 2 የራዲዮ ጣቢያዎችን ለማስጀመር የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አቶ ሙሉቀን ገልጸዋል፡፡ ለሀገራዊ እውቀት እና እሴት መዳበር አሻራውን ለማሳረፍ የግዕዝ ቋንቋ ስርጭት መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ዘመናትን ተሻጋሪ የሆኑ ሀገራዊ ጥበባት እና እሴቶች በሚገባቸው ስፍራ ላይ እንዲቀመጡ ኅብረተሰባዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሟሟላት፣ የሰው ኃይል ማብቃት እና የማስፋፊያ ሥራዎች ቀጣይነት ባላቸው ሁኔታ እየተከናወኑ ይቀጥላሉም ነው ያሉት። በአዲሱ ሚዲያ ዘርፍም ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ወጣቱን እና በውጭ ሀገር የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ የመረጃ ተደራሽ እንዲሆን፣ ከሀገሩ ጋር ያለውን መስተጋብር ማጠናከር እንዲቻል እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
አሚኮ በመደበኛ ሚዲያው የሚያገለግልባቸውን ሁሉንም ቋንቋዎች በአዲሱ ሚዲያም የሚያስተላለፍ እና መረጃ የሚያቀብል እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ አሚኮ በ7 ሀገራዊ ቋንቋዎች እና በ2 የውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ጉምዝኛና አፋርኛ በስርጭት ላይ እንደሚውሉም አስታውቀዋል፡፡
አሚኮ በ11 ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ በጥናት እያሳደገ እና እያሻሻለ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ አሚኮ ኅብር በመደበኛ ስርጭት መጀመሩ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የብሔረሰብ ቋንቋዎች የተሻለ የአየር ስዓት እና የይዘት ስብጥር እንዲኖቸው የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በአዲስ ወደ ስርጭት የገቡት አፋረኛ እና ጉምዝኛ ቋንቋዎችን ጨምሮ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል የሚነገረው ኦሮሞኛ ቋንቋ በስፋት በመጠቀም ለሕዝብ መስተጋብር መጎልበት አስተዋጽኦ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
አሚኮ በቀጣይ ጥናትን መሰረት ያደረገ ሁሉ አቀፍ ማሻሻያ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ጥናትን እና እውቀትን፣ የሕዝብን እና የሀገርን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የለውጥ ሥራዎቹ እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡ በሂደት እየተማርን እና እየሠራን እውቀትን እና መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረግን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲመጡ፣ የፖለቲካዊ እሳቤዎች እንዲዘምኑ፤ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እንዲፈቱ እና የሕዝብ ቅሬታ እንዲቀረፍ በጥልቅ ዘገባዎች እና የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመተግበር ሥራው እንደሚያጠናክርም አስገንዝበዋል።
ዘመናትን ተሻጋሪ እና ትውልድ አሻጋሪ የሆኑት እሴቶች እንዲጎለብቱ እና አሁን ለገጠመን ፈተና መሻገሪያ ድልድይ ሆነው ማገልገል እንዲችሉ አሚኮ ትኩረት ያደርግባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ ሌሎች ሚዲያዎች የተጀመረውን በትብብር የመስራት አዲስ ጅማሮ በማጠናከር የትብብር ጋዜጠኝነትን እና ይዘት መለዋወጥንና ውስን ሀገራዊ የሚዲያ ቴክሎጂ ሃብት በጋራ በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እና የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሁሉን አቀፍ የሚዲያ አቅም ግንባታ ሥራዎችን በመስራት ጠንካራ ሚዲያዎች እንዲኖሩ ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ለአሚኮ ድጋፍ ያደረጉና እያደረጉ የሚገኙ አካላትንም አመስግነዋል፡፡
አሚኮን ለማሳደግ የሚዲያው መሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ከባለቤቱ ሕዝብና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኩር ጋዜጣ – ሰኔ 13/2014 ዓ.ም ዕትም
Next article❝በቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በኾነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)