
የኔዘርላንድ መንግሥት ከኢንቨስትመንት በተጓዳኝ 10 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቤንት ቫን ሎዝድሬኸት ጋር ትናንት ማምሻውን ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው እንደተገለጸውም አምስት የኔዘርላንድ ባለሀብቶች ክልሉ ቁንዝላ በተባለ ቦታ በ5 መቶ ሄክታር መሬት ላይ በአበባ ልማት ላይ ይሠማራሉ፡፡
በቁንዝላ ከሚካሄደው የአበባ ልማት ጎን ለጎን የኔዘርላንድ መንግሥት ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎች ተቋማትን ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲገነባ ከክልሉ መንግስት ጋርም የድጋፍ ስምምነት ተፈጽሟል፡፡
ነዋሪዎቹም የአካባቢውን ውኃ ጥቅም ላይ በማዋል እንዲያመርቱ እና የግብርና ምርቶችን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡ ከኢንቨስትመንት ሥራው በተጓዳኝ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል የኔዘርላንድ መንግሥት 20 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚመድብ ነው የገለጹት፡፡ በዚህም በአካባቢው የሚኖሩ 10 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ስለአበባ ልማቱ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱንና ከዚህ በፊት የነበሩ የአካባቢው ማኅበራዊ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ የኔዘርላንድ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደር ቤንት ቫን ሎዝድሬኸት ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ክልሉ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆን ሠላምን በማረጋገጥ በኩል መንግሥት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሠላም በሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፍን ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዘላለም አስፋው
ፎቶ፡- በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ