
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ መላኩ ፋንታ እንዳሉት አባቶች አንድን ጉዳይ ሲጀምሩት የስኬቱን ደወል አስቀድመው ይደውላሉ፡፡ ይህ ደወል “በቀኝ አውለኝ” የሚል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደዘበት የሚነገረው ግን ብዙ ተምሳሌታዊ ጉልበት ያለው አባባል ነው፡፡ አማራ ባንክ በኢንዱስትሪው ወጀብ ውስጥ በቀኝ ለመዋል ጠንክሮ ወደ ኢንዱስትሪው የገባ የኢትዮጵያዊያን ባንክ እንደኾነ አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ውስጥ የማንስተው ሃቅ አለ ያሉት ሊቀመንበሩ በቀኝ ለመዋል ሌሎችም በቀኝ እንዲውሉ መመኘትና መደገፍ፣ በቀኝ የሚያውል ሃሳብ፣ ልብ ያለው ውጥን፣ የማይናወጥ ዓላማ፣ ሩቅ የሚወስድ ራእይ፣ ሰውን፣ ሀገርን እንዲሁም ዘርፉን ማእከል ያደረገ እሴት፣ የታሰበበት ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂን የሚደገፉ የትግበራ ምእራፎች፤ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ አማራ ባንክ እነዚህን ቋሚ ሰንደቆች ሃብት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱንም አስረድተዋል፡፡
አማራ ባንክ አክሲዎን ማኅበር ነሐሴ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በነፃ እና በበጎ ፈቃደኝነት የተቋም ግንባታ ፋይዳን በተረዱ የሚናገሩትን በሚተገብሩ አደራጆች እና ደጋፊዎች ተጠንስሶ እና ተመስርቶ እሴት ጨማሪ ባንክ በመኾን የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ አማራ ባንክ ሕዝባዊ መሰረቱን ጠብቆ እና ከፍ ብሎ ለመጓዝ በዛሬው እለት ሥራውን በይፋ መጀመሩን ሲያበስሩ በባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ በአደራጆች፣ በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አማራ ባንክ ራሱን በመስታውት አይቶ የመጣ ባንክ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ባንኩ ከቀደሙት ታላላቆቹ ብዙ መማሩንም ተናግረዋል፡፡ ጥንካሬውን የጉዞው አካል፣ ድክመቱን ደግሞ የመማሪያ እድል፣ አድርጎ ተጠቅሞበታልም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢንዱስትሪው ውስጥ በየጊዜው በሚፈጠሩ በርካታ ተለዋዋጭ ገፊ ምክንያቶች የተነሳ ከፊት ለፊቱ ያለውን ተጠባቂ ውድድር እና የተከማቸ እምቅ እድልን፣ ጎን ለጎን አስቀምጦ ባንኩ እንደሚጓዝ ገልጸዋል፡፡
አቶ መላኩ እንዳሉት አማራ ባንክ የአገልግሎት ፍኖተ ካርታው ገዥ ሃሳብን ከባንክ ባሻገር ብሎ ከገበያው የተቀላቀለ ሲሆን ይህም፡-
•እንደ ንስር ከፍ ብሎ በመብረርና በወጀብ መካከል ጥንካሬውን አጎልብቶ ራዕዩን ለማሳካት
•ያለውን ሰፊ ህዝባዊ መሰረትና ቅቡልነት ትርጉም ባለው ደረጃ ወደ ውጤት በመቀየር
•ኀላፊነት በሚሰማው ኢትዮጵያዊ አባት ተምሳሌትነት ሁሉንም በእኩልነት በማቀፍና በማገልገል
•በፉክክር ሳይኾን በውድድር፣ በተናጠል ሳይኾን በውህደት በሌሎች ኪሳራ ሳይኾን አብሮ በማደግና በሀገር ልማትና የመልማት ፍላጎት ቁልፍ ሚና በመጫወት
•በፋይናንስ ኢንዱስትሪው አስተውሎት ያላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ዘርፎች ደረጃቸውን ማሻሻል እየቻሉ በፋይደናንስ አቅርቦት ችግር ምክንያት እንዳይራመዱ የኾኑትን ለመደገፍ የተለየ አደረጃጀት በመፍጠር
•አማራ ባንክ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ቢዝነስ ብቻ እንዳልኾነ በመገንዘብና ከዚህ ባሻገር ያለ ሃሳብና እምነት ሰንቆ ስለኢንዱሰትሪው ለመነጋገር፣ እንደተቋም ሰርቶ ለመለወጥና ለማደግ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ይቀድማሉ በሚል ነው ብለዋል፡፡
አቶ መላኩ አማራ ባንክ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአክሲዮን ሽያጭ እና የባለአክሲዮን ቁጥር ያስመዘገበ እንዲሁም ከፍተኛ የመነሻ ካፒታል በማሰባሰብ የመጀመሪያ ደረጃን መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ተሞክሮውንም ማካፈል የሚችል ሆኖ የተገኘ፤ ከፍ ብሎ አስቦ የታሰበውን ሃሳብ ከፍ ካለ ድርጊት ጋር ማጣመር እንደሚቻል ማሳያ የሚሆን ባንክ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ይህም በአክሲዮን ሽያጭ ሂደቱ ብቻ ከፋይናንስ ሥርዓቱ ውጪ የኾነ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ እንዲገባ በማድረግና የአክሲዮን ሽያጭ ያካሄዱ አስር ባንኮችም ባንኩ እስከሚመሰረት ድረስ መስርያ ካፒታል እንዲያገኙ እድል የፈጠረ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
አማራ ባንክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ከመያዙም በተጨማሪ መላው የሀገሪቱ ሕዝብን በማሳተፍ ከመበተን ይልቅ መሰባሰብን፣ ከመራራቅ ይልቅ መቀራረብን በሚሻው ሕዝብ ዋና አጋርነትና ባለቤትነት ወደ አንድ ቋት በመሰባሰብ ይህን ግዙፍ ባንክ መመስረት ተችሏል ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፡፡
አቶ መላኩ እንደተናገሩት
•የአክሲዮን ሽያጩ 50 በመቶ በአዲስ አበባ፣ 30 በመቶ በሌሎች ክልሎችና 20 በመቶ በአማራ ክልል መፈጸሙ
•በሰው ሃይል ቅጥርም መመዘኛውን ያሟሉ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገበት
•የቅርንጫፍ ከፈታውም ገበያንና ቅደም ተከተልን ታሳቢ በአደረገ መልኩ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እና ኅብረተሰብ መፈጸሙ የዚሁ አስተሳሰብ ጉልህ ማሳያ ከመኾኑም በላይ ለሕዝብ በሕዝብ የተቋቋመ ተቋም መሆኑን ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡
አማራ ባንክ የካቲት 02/2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በ141ሺህ 356 ባለአክሲዮኖች ፣ በተፈረመ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮንና በተከፈለ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ፈቃድ ማግኘቱን አስገንዝበዋል፡፡ ቀሪው ወደ 44 ሺህ የሚጠጋ ባለአክሲዮን ቃል የተገባ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮንና የተከፈለ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ተቋም ቀርቦ ባለመፈረም 14ሺህ 643፣ የተሟላ መረጃ ባለመስጠት 14 ሺህ 643 እና በውጭ ምንዛሬ መግዛት ሲገባ በብር በመግዛት 1ሺህ 309 በፍቃዱ ውስጥ አልተካተቱም ያሉት ሊቀመንበሩ ወደፊት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የሚስተናገዱ እንደሚኾንም አስገንዝበዋል፡፡
ውኃ ዋና ሳንችል በባህሩ ውበት ተመስጠን ዘልለን ውኃ ውስጥ የገባን አይደለንም ያሉት አቶ መላኩ ይልቁንም መንገድ እንደሚያቋርጥ እግረኛ ቆም ብለን ግራና ቀኛችንን አይተን ከዘርፉ የተቀላቀልን ነን ነው ያሉት፡፡ ሊቀመንበሩ ‟ያልዘራነውን ትጉነት አንሰበስብም፣ ያልሰጠነውን የሰለጠነ አመራር አናጭድም፤ ያልወቃነውን የደንበኞቻችን እርካታ በጎተራ አንከትም፤ ያልተከልነውን ሙያዊ አቅም ከየትም አምጥተን አናሳድግም፡፡ ስለኾነም እንደ ብልህ ዋናተኛ በሰፊው የፋይናንስ ባህር ላይ አሸናፊ ቀዛፊ ለመኾን በባንካችን የተንከባካቢነት ቅርንጫፍ እሴቶች ጉልበትነት ተጠቅመን እንሰራለን፤ ሰፍተን እንዘረጋለን” ብለዋል፡፡
አማራ ባንክ በዛሬው ዕለት ብቻ 70 ቅርንጫፎችን በመላው የሀገሪቱ ክፍል ለመክፈት በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል፡፡ የባንኩን መከፈት በጉጉት ለሚጠብቁት ለባለአክሲዮኖች እና ለሕዝቡ ከፍተኛ ደስታን የሚፈጥርና ቀጣይ ተሳትፎን የሚያጎለብት እንደኾነ እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡ ይህም በቀኝ ለመዋል የመጀመር አንዱ ምእራፍ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡
ሊቀመንበሩ ‟በቀኝ አውለኝ ስንል የኢንዱስትሪውን ህመም መረዳት፤ የሕገወጥነትን መስመር ለማስተካካል በመትጋት፣ በፍጹም ቅንነት የዘርፉን ሰላም መጠበቅ፣ ስብራቱን በጋራ መጠገን መቻል ነው፤ ስለኾነም በአገልጋይነት፣ በባለቤትነት፣ በታታሪነት እና በቁርጠኝነት፤ በጎ መንፈስ ውስጥ ኾነን የባንካችንን ደንበኞች በአገልግሎታችን ማርካት፣ ባለድርሻ አካላትን ማስደሰት እና በአክብሮት ምላሽ መስጠት ዋና ዓላማችን አድርገን ተልዕኳችንን በሚገባ እንወጣለን፤ ለዚህ ደግሞ መሰረታችን እና ጉልበታችን ሕዝባችን መኾኑን በፅኑ እንረዳለን” ብለዋል፡፡
አማራ ባንክ የግለሰቦች ይሁንታ አቅም የኾነ ባንክ ነው ያሉት አቶ መላኩ ግለሰቦች በቀኝ ሲውሉ ማኅበረሰብ ተረጋግቶ እንደሚኖር እንደሚያምኑም ነው የገለጹት፡፡ ማኅበረሰብ በቀኝ ሲውል ሀገር ሰላም እንደምታገኝም እናውቃለን ያሉት አቶ መላኩ ሀገር ሰላም ስትኾን የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ሳምባ ጤናማ እስትንፋስ እንደሚያገኝም አንጠራጠርም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያዊያን ባንክ የኾነው አማራ ባንክ የዘርፉ ቀኝ እጅ ሆኖ ለመገኘት አንደዛሬው ሁሉ በቀኝ ለመዋል ይሠራል፡፡ ከባንክ ባሻጋር ሆኖ ይደምቃል፡፡ በድጋሚ በእሴቶች እየኖረ ሊያገለግል መጥቷል ለዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት፡፡
ይህ ሁሉ ራዕይና ትልም እውን የሚሆነው በዋነኝነት በባንኩ ማኔጅመንትና ሠራተኞች በመኾኑ የባንኩ አመራርና ሠራተኞች በሙሉ ይህንን እንደሚወጡም ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ በሁሉም አካላት ስም በሥነምግባር፣ በብቃትና በብርታት የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ አደራ ብለዋል፡፡ የዳይሬከረተሮች ቦርድም የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣ እምነታቸው እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
አማራ ባንክ በዚህ መልኩ ዕውን እንዲኾን በአንድ በኩል እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጊዜያቸውን፣ በሌላ በኩል የተጠነሰሰውን ሃሳብ ተቀብለው እና አምነው ገንዘባቸውን በመስጠት ታሪካዊ አሻራ ላስቀመጡ ባለአክሲዮኖች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ፣ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ)፣ ለዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሸን እና ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልኾኑ ተቋማት ባንኩ እንዲመሰረት ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/