የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ እና ፍላጎት የሚንጠው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር

134

ባሕር ዳር: ሰኔ 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የሁለቱ ሀገራት መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ አካባቢው የቅኝ ገዥዎቹ የተንኮል እጆች ስላረፈበት በቀላሉ ተነጋግሮ መፍታት አልተቻለም፡፡ በተለያዩ ዘመናት ከሦስት ጊዜ በላይ የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ጉዳዩን ተነጋግረው ለመፍታት ቢሞክሩም የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ እና ፍላጎት የሚንጠው ድንበር በመኾኑ እልባት አልተገኘለትም፡፡

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ ወቅት አይተው አቋማቸውን በሚለዋወጡት የሱዳን መሪዎች እና በመልካም ጉርብትና መርህ ላይ በቆሙት ኢትዮጵያዊያን መካከል የማይታረቅ ሀቅ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ደረጃ ችግሮች ባይኖሩባቸውም ሱዳን በየጊዜው ወደ ሥልጣን በሚመጡት መሪዎቿ አማካኝነት የቅኝ ግዛት አሳቢዎችን ፍላጎት በቀጣናው ለማስፈጸም የኢትዮጵያን ክፉ ቀናቶች እንደአጋጣሚ ያልተጠቀሙበት ጊዜ የለም፡፡

ጥቅምት 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ትህነግ አማካኝነት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲያቀና ሱዳን በአወዛጋቢው የድንበር ጉዳይ ላይ ሌላ የግጭት ክስተት ሆና ብቅ አለች፡፡ አንድ ምዕተ ዓመት በዘለቀው የድንበር ውዝግብ ውስጥ በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ እና በ1980ዎቹ የደርግ አገዛዝን መዳከም ተከትሎ እንዳደረገችው ሁሉ ኢትዮጵያ የደከመች ሲመስላት 2013 ዓ.ም ላይ ድንበር ጥሳ አርሶ አደሮችን አፈናቅላ ወረራ ፈጸመች፡፡

ሱዳን ከአንድ ዓመት በላይ የያዘችውን የኢትዮጵያን ድንበር ለቃ እንድትወጣ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ቢቀርቡላትም ከአካባቢው አልወጣችም፡፡ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ታሪካዊ ዳራ እና አሁናዊ መፍትሄ ዙሪያ በአካባቢው ሰፊ ጥናት ያደረጉ የታሪክ ምሑርን አነጋግረናል፡፡

ሱዳን መሬት ላይ ያለውን ሃቅ በሚጻረር መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ተሻግራ ወረራ ፈጽማለች ያሉን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምሕርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ እርቂሁን (ዶ.ር) ናቸው፡፡ ለአንድ ክፍለ ዘመን እልባት ያልተገኘለት የድንበር ውዝግብ ይፋዊ ስምምነት የተፈጸመው እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1902 እንደነበር ያወሱት የታሪክ ምሑሩ ስምምነቱ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በእንግሊዛዊው ኮሎኔል ሀሪግ ሰን መካከል የተደረገ ነበር፡፡ ስምምነቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል በቀጣይ የድንበር መካለል ይካሄዳል የሚል ነበር፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ እንዳብራሩት ነገር ግን በ1903 (እ.አ.አ) ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት እውቅና ውጭ የ1902ቱን ስምምነት በመጣስ በእንግሊዝ በኩል የተወከለው ሻለቃ ጊዩን ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ አካለለ፡፡ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ከዚህ ዘመን ጀምሮ ይመዘዛል፡፡ የቅኝ ገዢዎቹ የሴራ እና የተንኮል እጆች ስላረፈበት ውስብስብ ኾኗል ይላሉ፡፡ እንግሊዛዊው ሻለቃ ጊዩን ድንበር ጥሶ ያካለለው አካባቢ ሰፊ ለም መሬት እና ወታደራዊ ስትራቴጅክ ያለው አካባቢ በመኾኑ በሁለቱም ሀገራት በጥብቅ የሚፈለግ ነው፡፡ አካባቢው በተለምዶ “ነጭ ወርቅ” እየተባለ የሚጠራው ሰሊጥ በሰፊው የሚመረትበት በመኾኑ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ የተለየ ፋይዳ አለው ነው ያሉት የታሪክ ምሁሩ፡፡

ሱዳን የጣሰችው የ1902ቱን ስምምነት ብቻ ሳይኾን የ1972ቱን የሁለቱን ሀገራት ስምምነት እንደኾነ የታሪክ ምሑሩ አብራርተዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ቋሚ የድንበር ማካለል እስኪያደርጉ ድረስ የያዙትን ይዘው እንዲቀጥሉ ስምምነት ነበራቸው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ የታሪክ ምሑሩ ሱዳን ኢትዮጵያ ጠንካራ ኾና በቀረበች ወቅት ወዳጅ፤ ፈተናዎች በበዙባት ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳዳጅ ስትኾን ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም ነው ያሉት፡፡

በ1969 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ አማካኝነት ሱማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር አሁን ሱዳን በወረራ የያዘችውን አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ወረራ ፈጽማበት ነበር፤ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጠንካራ ምት ለቃ መውጣቷን ዶክተር ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡ በ1980ዎቹ አካባቢዎች የደርግ መንግሥት አቅም ሲዳከም ትኩረቱ መሃል ሀገር ላይ በመኾኑ ሱዳን አካባቢውን በድጋሚ ወራ እንደነበር አውስተዋል፡፡ አሁንም አካባቢውን በወረራ የያዙት አሸባሪው ትህነግ ክህደት በፈጸመበት ተመሳሳይ ወቅት በመኾኑ የሱዳንን ወቅት ያየ አቋም አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግሩ ከሰላም እና የዲፕሎማሲ አማራጮች የሚነሳ ቢኾን ይመረጣል ሲሉም አመላክተዋል፡፡ ወቅቱ ሱዳን ከአፍሪካ ኅብረት የታገደችበት በመሖኑ በአህጉራዊ ኅብረቱ ለስምምነት የምትቀመጥበት እድል እንደሌለ የታሪክ ምሑሩ ጠቅሰዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ድርድር ለኢትዮጵያ ያለው ሚዛን የሳተ ታሪካዊ አጋጣሚ ተስፋ የሚጣልበት አይደለምም ባይ ናቸው፡፡ አካባቢው የውጭ ኃይሎች ፍላጎት የሚንጠው በመኾኑ ለጣልቃ ገቦች እንዳይመች ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማየት ተመራጭ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

አሜሪካ እና ምዕራባውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ቀጣናው ዘልቀው ለመግባት ፍላጎት የሚያሳዩበት ወቅት እንደኾነ ዶክተር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ከአህጉራዊ ሽምግልና እና ከሁለቱ ሀገራት የጋራ ውይይት ውጭ ያሉት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች አዋጪ እንዳልኾኑም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተናገሩ፡፡
Next articleበሕዝብ ውይይት የተነሱ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በብቃትና በቁርጠኝነት መመለስ የሚችል የሥራ ኀላፊዎችን ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።