እየተከናወነ የሚገኘው የሕግ የማስከበር ተግባር የአካባቢያቸውን ሰላም ማረጋገጡን የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

125

ጎንደር፡ ሰኔ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር በጋራ በተሠራው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ በአካባቢው ይስተዋሉ የነበሩ ሕገ ወጥ ድርጊቶች መቀነሳቸውን የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በመጠቆምና በማጋለጥ የማኅበረሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የወረዳው ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፣ ሠርቶ ውጤታማ እንዳይኾን ሲገዳደሩት የነበሩትን የሕግ ጥሰቶች ለማስተካከል መንግሥት በተለያየ ቦታ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እርምጃ መውሰድ ላይ ነው።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኪንፋዝ በገላ ወረዳም የሕግ የበላይነትን የማስፈን ሥራ እየተሠራ ይገኛል። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው የአካባቢያቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በተሠራው ሕግ የማስከበር ሥራ ከአሁን ቀደም ይታዩ የነበሩ ወንጀሎች ቀንሰዋል፤ የአካባቢያቸው ሰላም ተረጋግጧል፡፡

ወይዘሮ የአቦነሽ አወቀ በወረዳው የጸጥታ መዋቅሩ ከነዋሪው ጋር በሠራው ሥራ በወረዳው ይስተዋል የነበረው የጥይት ተኩስ፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ስርቆት፣ ዘረፋ እና ሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶች መቀነሳቸውን ነግረውናል። ይሕም ነዋሪው በሰላማዊ መንገድ የልማት ሥራውን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ማኅበረሰቡ ጥቆማ በመስጠት፣ ወደ ጠላት የሚላኩ ንብረቶችን ጭምር በመያዝና ወንጀለኛን በማጋለጥ ለጸጥታ አካላት አጋርነቱን እያሳየ መኾኑንም አንስተዋል።

በወረዳው ሰላም ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ ያገኘናቸው አቶ ገብሬ ሙጬ እንደነገሩን የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በሠራው ሥራ በወረዳው ይስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን መቅረፍ ተችሏል።

ለሚፈጠሩ ግጭቶችና ወንጀሎች መቀነስ የሀገር ሸማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደኾነም ነው ያነሱት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ማሬ ታደሰ እንደገለጹት በወረዳው የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር ባከናወነው የቅድመ መከላከል እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አካባቢያቸው ሰላም ኾኗል።

የተጠናከረ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው፤ የማኅበረሰብ ስጋት የኾኑ ጥርጣሬዎች ሲፈጠሩ ቀድሞ እርምት በመውሰድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ከምንጩ ማድረቅና ማክሸፍ መቻሉን አንስተዋል። በተለያዩ ድርጊቶች የተሳተፉትን ደግሞ ለሕግ የማቅረብ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ወንጀለኞችን በማጋለጥ የማይተካ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ነግረውናል።

የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስር አለቃ ዋኘው ምኅረቱ በወረዳው ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ ማኅበረሰቡ በሰላም የዕለት ከዕለት ሥራውን እንዲከውን ኾኗል።

በወረዳው በተደረገው ጥናት 34 የሚኾኑ የማኅበረሰቡን ሰላም ሲያውኩ የነበሩና በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተለይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለያየ ወንጀል የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በሕግ ቁጥጥ ሥር የዋሉ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ሰብዓዊ መብት በተጠበቀ መንገድ ጉዳያቸው በሕግ እንዲጣራ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኀላፊው እንዳብራሩት ከሕዝቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር ወደ ተግባር የተገባው፤ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎችና ከወጣቶች ጋር በጋራ መሥራት መቻሉ ደግሞ ሥራውን ውጤታማ አድርጎታል፤ ማኅበረሰቡ ወንጀለኞችን በመጠቆምና በማጋለጥ ያሳየው ትብብር ለተገኘው አመርቂ ውጤት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሕዝቡ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleለሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ከተጓዙት 3 ሺህ 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1 ሺህ 128ቱ አልተመለሱም።
Next articleመንግሥት ጥፋተኛ የኾኑ ግለሰቦችን ለሕግ ሲያቀርብ ሕብረተሰቡ ሊተባበር እንደሚገባ ተጠቆመ።