ለሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ከተጓዙት 3 ሺህ 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1 ሺህ 128ቱ አልተመለሱም።

202

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ወደ ትግራይ ከተጓዙት ሦስት ሺህ 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንድ ሺህ 128ቱ እንዳልተመለሱ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ አስመልክተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ አሁንም ቀጥሏል።

በክልሉ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። እስካሁን ድረስ ሦስት ሺህ 297 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ጭነው ቢሄዱም አንድ ሺህ 128ቱ አልተመለሱም።

እስካሁን ለሰብዓዊ እርዳታ የተሰማሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሦስት ሺህ 297 መሆናቸውን አቶ ደበበ ጠቁመው፤ እስካሁን የተመለሱት ተሽከርካሪዎች ሁለት ሺህ 169 ሲሆኑ፤ ያልተመለሱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አንድ ሺህ 128 ናቸው። ባልተመለሱ ተሽከርካሪዎች የሚመለከተው አካል ክትትል የሚያደርግ ይሆናል።

ለሰብዓዊ አገልግሎት ከአዲስ አበባ መቀሌ 236 በረራ መደረጉን አመልክተው፤ይህም በአጋር አካላት አማካኝነት ለሰውና ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት ምልልስ የተደረገ ጉዞ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ድጋፉ እየተደረገላቸው ያለው በ95 አጋር ድርጅቶች አማካኝነት መሆኑን ጠቁመው፤ድጋፉ ነዳጅን ጨምሮ ጥሬ ገንዘብ፣ መድኃኒትና የተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑትን ጭምር ያካተተ እንደሆነ ነው አቶ ደበበ ያሳወቁት።በተጨማሪም ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በለጋሽ አካላት አማካኝነት ሁለት ሺ 502 ተሽከርካሪዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው መቀሌ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ደበበ ገለጻ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ በጥሬ ገንዘብ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ፣216ሺህ 91ኪሎ ግራም መድኃኒት እና 421ሺህ977 ኪሎ ግራም የተመጣጠነ ምግብ በአጋር ድርጅቶች አማካኝነት በአየር ትራንስፖርት ወደ መቀሌ መጓጓዙንም ጠቅሰዋል።

130ሺ 200ኪሎ ግራም ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ ውሃ፣ ንጽህና መጠበቂያ መጠለያና ቁሳቁስ እንዲሁም የእርሻ ግብአቶች በአየር ትራንስፖርት መጓጓዙን ተናግረዋል። ለህጻናት፣ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለአጥቢ እናቶች እንዲሁም ለአቅመ ደካማዎች የሚውል112ሺህ 492 ሜትሪክ ቶን የተመጣጠነ ምግብን ጨምሮ በየብስ ትራንስፖርት ከሐምሌ ወር 2013ዓ.ም ጀምሮ እንደተጓጓዘም ገልጸዋል።

ውሃ መጠለያ ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያ እቃዎችን ጨምሮ 15ሺህ 554ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በየብስ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ እንዳለም አመላክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 782ሺህ 396 ሊትር ነዳጅ ከሚያዝያ ወር 2014ዓ.ም ጀምሮ በየብስ ትራንስፖርት እየተጓጓዘ እንዳለ አስታውቀዋል። ኢፕድ እንደዘገበው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኅብር የቴሌቪዥን ቻናል መጀመር ኢትዮጵያዊ አንድነትን እና አብሮነትን እንደሚያጎለብት የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ የሽጥላ ተናገሩ።
Next articleእየተከናወነ የሚገኘው የሕግ የማስከበር ተግባር የአካባቢያቸውን ሰላም ማረጋገጡን የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።