
ኮርፖሬሽኑ የዲፕሎማሲ ተቋም ኾኖ ሕዝብን ከሕዝብ እንዲያገኛኝ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ የሽጥላ የአሚኮ ኅብር ሁለተኛ ቻናልን ማስጀመር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው አሚኮ ከምሥረታው ጀምሮ የተጓዘባቸው መንገዶች አስገራሚ ገፅታዎች እንዳሉት ገልጸዋል። ከትንሽ ጀምሮ ትልቅ አስቦ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ መኾኑንም አንስተዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኹሉን አቀፍ የኾነ ጉዞ እና እድገት ያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። በትንሽ የሰው ኀይል ጀምሮ ዛሬ ላይ ግዙፍ ተቋም እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ራሱን ከዘመኑ ጋር እየዋጀ በሰው ኀይልና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እየኾነ የቀጠለ መኾኑንም ገልጸዋል። ብቁ የሰው ኀይል ያፈራ፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ሚዲያ መኾኑንም ተናግረዋል።
አሚኮ ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ መኾኑን ያነሱት አቶ ግርማ ኅብረተሰቡን መሠረት ያደረገ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። እድገቱም ኅብረተሰቡን መሠረት ያደረገ እንደኾነ ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል ሕዝብ የሚፈልገውን እድገት ለማምጣት ጥረት ሲያደርግ ከሕዝቡና ከመንግሥት የሚፈልቁ አጀንዳዎችን ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርስ እንደኾነም ገልጸዋል።
የሕዝባችን ፍላጎትና ጥቅም ማርካት የሚያስችል ሚዲያ ያስፈልገናል፤ አሚኮ በኢትዮጵያ ተመራጭ የኾነ ሚዲያ ነው፤ ነገር ግን አሁንም የኅብረተሰቡን ፍላጎት የሚሞላ ሚዲያ ያስፈልጋልም ብለዋል።
አሚኮ ኅብር ሁለተኛው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን ቻናል መከፈቱ ሰፋ ያሉ አጀንዳዎችን ለማሰራጨት እና ተጨማሪ ቋንቋዎችን ለመጠቀም ያገለግላል ነው ያሉት። የብዝኃ ልሳን ፍላጎታችንን ከስምንት ወደ አስር እናሰፋለንም ብለዋል።
የሚዲያውን የቋንቋ ተደራሽነት በማስፋት እንሠራለን ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው የሶማሊኛ ቋንቋን ለማስጀመር በሂደት ላይ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሚዲያው የዲፕሎማሲ ተቋም ኾኖ ሕዝብን ከሕዝብ እንዲያገናኝ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በመላው ኢትዮጵያ የሚኖሩ አማራዎች በቋንቋቸው ተደራሽ እንዲኾኑ ከማድረግ በላይ በሚኖሩበት አካባቢ ቋንቋም ተደራሽ በማድረግ ሚዲያው አንድነትንና አብሮነትን ከፍ ያደርጋልም ብለዋል። መልካም ሐሳብን እየዘራ መልካም ሐሳብ የሚያፈራና ከአፍሪካም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ የኾነ ሚዲያ መፍጠር ይኖርብናልም ነው ያሉት።
አሚኮ ኅብር ሁለተኛው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን ቻናል ትልቅ የመኾን ራዕያችን ማሳያ ነውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የአማራ ክልል ሕዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት አቶ ግርማ የአማራ ክልል የኢትዮጵያ የዙፋን መቀመጫና የኢትዮጵያ መዲና እንደነበርም አስታውሰዋል። በክልሉ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፉባቸው ታላላቅ ሀብቶች መኖራቸውን አንስተዋል። አማራ በመላው ኢትዮጵያ ያሳረፋቸውን አሻራዎች ለማስተዋወቅና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን አንድነት ለማጠናከር ሚዲያው ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት። በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ ረገድ ሚዲያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በትክክል እንዲያውቁ አሚኮ ታላቅ ድርሻ ይኖረዋልም ብለዋል። ባሕልና ወግን ለማስተዋወቅ፣ ታሪኩን ለማዳረስ በበርካታ ቋንቋዎች መሥራት ይገባልም ነው ያሉት። ተዝቆ የማያልቀውን የአማራን ባሕልና ታሪክ በልዩ ልዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እናስተዋውቃለንም ብለዋል። በርካታ ቋንቋዎችን በመጠቀማችን የጥፋት አጀንዳዎችን መቀልበስ ችለናልም ነው ያሉት አቶ ግርማ።
ሚዲያው እንደ አራተኛ መንግሥት ኾኖ ማገልገል እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በአማራ ሕዝብ ላይ የተሠሩትን የሐሰት ትርክቶች መቀልበስና ትክክለኛውን የአማራ ማንነት በማስረፅ ረገድም ሚዲያው ከፍ ያለ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ፖለቲካ የሰከነ አለመኾኑን ያነሱት የቦርድ ሰብሳቢው የአማራን ጥቅምና ክብር የሚያስከብረው ራሱ አማራ ነውም ብለዋል። የአማራ ሕዝብ በጋራ ራዕይና ጥቅም ላይ መደራጀት አለበትም ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለማፅናት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አካታች በኾነው ሀገራዊ ምክክር የአማራ አጀንዳዎች እንዲደመጡ ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል። የሌሎችን አጀንዳዎች ለማዳመጥ መዘጋጀት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አፋኙን ሥርዐት በመታገል ለውጥ ማምጣቱን ያስታወሱት አቶ ግርማ የሕዝብ አንድነት እንዲጠናከር በትኩረት መሥራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ስም ለማጠልሸት እና የአማራ ሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዳይከበር የሚጥሩ የውስጥ ባንዳዎች እና የተደራጁ ጠላቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ስሙን በማጠልሸት ለጉዞው ፈተና የሚኾኑትን ጠላቶችን በፅናት መታገልና በጀመረው መልካም ሥራ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
ለሚዲያው እድገት አስተዋጽኦ ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች ጋር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ሚዲያውንም ለማዘመንና ዓለም አቀፍ ለማድረግ እንሠራለን፤ እቅዳችንና ፍላጎቶቻችን በጋራ እናሳካቸዋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/