ተደራጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ ከዚህ በፊት ሲከሰት የነበረውን ወንጀል ማስቀረት መቻላቸውን የእንጅባራ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

155

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በፀጥታ ሥራው በመሳተፋቸው ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎችን መከላከል እና የከተማዋን ሠላም ማስጠበቅ ተችሏል ተብሏል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በበጎ ፈቃደኝነት ማኅበር ተደራጅተው የአካባቢውን ሠላም ለማስፈን ከሚሰሩ ወጣቶች መካከል አቶ አዳነ አለማየሁ ‹‹በእንጅበራ ከተማ ከዚህ በፊት የተደራጀ ዘረፋ፣ የግለሰቦች ሱቅ ስርቆት፣ ማታለል እና የሰው ግድያ ነበር፤ አሁን ግን በአንድ ለአምስት ተደራጅተን በመሥራታችን በሰፈራችን ሲከሰቱ የነበሩ ወንጀሎችን አስቀርተናል›› ብሏል፡፡

የተደራጁ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ከምሽቱ 2፡00 እስከ 7፡30 በአንድ ዙር፤ ከ7፡30 እስከ 12፡30 ደግሞ በሌላኛው ዙር ሮንድ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በየቀበሌያቸው አምስት አምስት ወጣቶች ተራ በማውጣት ሮንድ በመጠበቅ የከተማዋን ሠላም ማስጠበቅ መቻላቸውን ወጣት አዳነ ተናግሯል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሌሊት ሌሊት ወንዶች፣ ቀን ቀን ደግሞ ሴቶች የፀጥታውን ሥራ የዕለት ተግባር በማድረግ እንደሚያከናውኑትም ወጣቱ ተናግሯል፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ አባል ሳጅን ለይኩን ቤዛ እንደገለፁት ደግሞ የፀጥታው አካላት ከሚሠሩት መደበኛ ተግባር በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቁ ሲከሰት የነበረው ከቀላል እስከ ከባድ ወንጀል እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡም ሕገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የሚያገኛቸውን ሰዎች ለሕግ አሳልፎ የመስጠት ባሕል እያደረገ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ የፀጥታ ሥራ የጋራ ተግባር መሆኑን ያስረዱት ሳጅን ለይኩን ነዋሪዎች ለሠላም መስፈን እያደረጉ ያሉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንግሥቱ አድናው እንደተናገሩት ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን የፀጥታው ባለቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙት 34 ሰፈሮች በአንድ ሌሊት ብቻ 170 ወጣቶች በሮንድ ጥበቃ እንደሚሳተፉም አቶ መንግሥቱ ገልፀዋል፡፡
በተሠራው ሥራም ከዚህ በፊት ተደራጅተው በዘረፋ ተግባር የተሠማሩ እና ራሳቸውን ‹‹ቡድን 23›› በማለት የሰየሙ ሕገ ወጦች በሕግ ተይዘው ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 76 ወንጀሎች ተፈጸመዋል፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወንጀሎችን መጠን ወደ 36 መቀነስ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከጎረቤት እና ከዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የግንኙነት ፖሊሲ በጥንቃቄ መቅረጽ እንዳለባት ተመላከተ፡፡
Next articleየኔዘርላንድ ባለሀብቶች በአማራ ክልል በአበባ ልማት ሊሰማሩ ነው፡፡