
ሰኔ 07/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሀገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የኮንክሪት አስፓልት 13 ሺህ ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ብቻ 4 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት አስፓልት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ገንብቶ አስረክቧል ብለዋል። በድምሩ 8 ሺህ 113 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የመንገድ ግንባታ አሁን እየተገነባ እንደሚገኝና በሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በድምሩ 9 ሺህ 102 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች ደግሞ በጀት ተመድቦላቸው በፀጥታ ምክንያት ያልተጀመሩ እና በጨረታ ሂደት ላይ ያሉ የመንገድ ግንባታ ስለመኖራቸው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባለቤትነት ብቻ በድምሩ ወደ 22 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ እየተገነባ እንደሚገኝ ለምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ የጎን ስፋቱ እስከ 60 ሜትር የሚሰፋ 151 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሪት ተገንብቶ እንደተጠናቀቀም ተናግረዋል። በከተማው 470 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል። 116 ኪሎ ሜትር ሰፋፊ የእግረኛ መንገድ እንደተሠራም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን እየተሠሩ የሚገኙ የመንገድ ሥራዎችንም በምክር ቤቱ ላይ አንስተዋል።
👉 ከጅጋ – ቋሪት- ቲሊሊ 121 ኪሎ ሜትር፤
👉ከደንበጫ – ፈረስ ቤት – አዴት 137 ኪሎ ሜትር፤
👉ከዱርቤቴ ቁንዝላ 135 ኪሎ ሜትር፤
👉ከማንኩሳ ብርሸለቆ 36 ኪሎ ሜትር ፤
👉ቡሬ ጎመራ 43 ኪሎ ሜትር፤
ጎንጅ ቆለላ 11 ኪሎ ሜትር እና
👉ከባሕር ዳር ጭስ ዓባይ 21 ኪሎ ሜትር
👉በድምሩ 504 ኪሎ ሜትር አስፓልት በዞኑ እየገነባን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በሶማሌ ክልል በአራት ዓመታት ውስጥ የተገነባው የመንገድ አውታር ሶማሌ ክልል ከኾነ ጊዜ ጀምሮ ያልነበረው ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ሁሉም መንገዶች ሲገነቡ ከሽሮ ፈሰስ አሠራር ወጥተው በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ እንዲሠሩ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመት ተኩል ገደማም ከለውጡ በፊት የነበረንን ኮንክሪት አስፓልት የሚስተካከል መንገድ ተሠርቷል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በኮሮና ወረርሽኝና በጦርነት ውስጥ ኾነንም ባለፉት ሦስት ዓመታት በመንገድ በኩል አስደማሚ ሥራ ተሠርቷል” ነው ያሉት።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የመንገድ አውታር 27 ሺህ ኪሎ ሜትር ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ 165 ሺህ ኪሎ ሜትር እንደደረሰ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ እንደሚያመላክተው ከለውጡ በኋላ በድምሩ 38 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተገንብቷል። ይኽ ድምር በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተሠራውን እና በክልሎችና በከተማ አሥተዳደሮች ጭምር የተገነባውን የሚያጠቃልል እንደኾነም አመላክተዋል።
በአሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/