“የማያርሱ ገበሬዎች፣ ማረስ ማፈስ ናፋቂዎች”

190

ሰኔ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሰማዩ ሲያጉረመርም፣ ደመናው በነፋስ እየተለጋ ሲተምም የገበሬ ደስታ ከፍ ይላል፡፡ ከጎተራው ያለውን ዘር ፈጣሪውን አምኖ በባዶ መሬት ላይ ይበትናል፡፡ ከወፍ አዕላፍ አውጥህ አብላኝ እያለ በባዶ መሬት የሚጥላት አንዲት ፍሬ ብዙ ኾና ትነሳለች፣ ጥቂት በትኖ ጎተራ ሙሉ ትኾናለች፣ የዓመት ቀለቡን ትችላለች፡፡ ሀገሬውንም አጉርሳና አልብሳ ታኖራለች፡፡
ማን እንደገበሬ ፈጣሪውን ያምናል? ማን እንደ ገበሬ ለፈጣሪው ይታመናል? አንተ ታውቃለህ ብሎ በማሳው የጎተራውን ዘር ይጥላታል፣ ሲያምኑት የማይከዳው ፈጣሪውም የተሰጠውን አደራ በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ፣ ከበረዶና ከምች ከልሎ ይሰጠዋል፡፡ የሚሰጠው ፍሬ የእምነቱና የልፋቱ ውጤት ናት፡፡
ደመናው ሲዳምን ገደሉ ይወረዛል፣ ጉምና ጉርምርምታ ይበዛል፣ ምድርን የሚያረሰርስ ዝናብ ወደ ምድር እንዲወርድ ይታዘዛል፣ ዝናቡ ምድርን ሲያረሰርሳት፣ የተጠማችውን ሲያጠጣት፣ ቅጠላቸውን ያረገፉት ዛፎች ልምላሜያቸው ይመለሳል፣ ልምላሜ አጥሯት የከረመችው ምድር አረንጓዴ ካባ ትለብሳለች፣ በፏፏቴዎች ትመላለች፣ ላሞች ወተት ይሰጣሉ፣ በሬዎች ያለ ድካም ይታረሳሉ፣ እንቦሶች የእናታቸውን ወተት እየጠጡ ሜዳውን ያካልላሉ፣ እረኞች በዋሽንታቸው እያዜሙ በጋራ ይሰለፋሉ፡፡

ክረምት ዘር ተዘርቶ ቡቃያ የሚታይበት፣ ቡቃያው የሚያብበት፣ አበባው ፍሬ የሚሰጥበት፣ የደረቀው የሚለመልምበት፣ የጠወለገው የሚፈካበት፣ የበጋው ወቅት ስንቅ የሚሰነቅበት፣ ተስፋ የሚጣልበት፣ የዓመት ጉርስ የሚሰበሰብበት፣ በሬና ገበሬ የሚወዳጁበት፣ ፈጣሪ ምድርን በልምላሜ የሚያስጌጥበት፣ የሚያምኑትን ገበሬዎች የሚጎበኝበት የተስፋ ወቅት ነው፡፡ የተስፋው ወቅት ካለፈ ኹሉም አላፊ ይኾናል፣ በክረምት ካላረሱ በበጋው ጥጋብ አይኖርም፡፡ ʺሞትና ክረምት አይቀርም” የሚለው የሀገሬ ሰው ክረምትን በጉጉት ይጠብቀዋል፣ በዝናብ መመታት፣ በውርጭና በቁር መሰቃየት ቢኖረውም ያለ ክረምት ቤት አይሞላም፣ ያለ ክረምት ጥጋብ የለምና ክረምትን በናፍቆት ይጠብቀዋል፡፡
የሀገሬ ገበሬ በሀገር ረሃብ እንዳይኖር፣ ሰብል እንዳያጥር ወገቡን እርፍ እየለጋው ከበሮቹ ጋር ሲታገል ይከርማል፡፡ ወስኮና ሞፈሩን፣ እርፍና ማረሻውን፣ ድግርና ከርፈዙን በአንድ ላይ አሰካክቶ፣ ኳሊና ጀንበርን፣ ቦረንና ሞላን፣ ዘገርና ቦጋለን በሌሊት አብልቶ፣ በማለዳ አጠጥቶ ጀንበር ከመስኮቷ ሳትዘልቅ ገና በማሳው ሄዶ በሰፊ ድግር ይተልማል፡፡ ጀንበር ሳትዘልቅ የጠመደው ገበሬ ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ ከማሳው አይጠፋም፣ እጁ ከእርፉ አይነቃነቅም፡፡
ገበሬ የሰኔዋን ጀንበር በዋዛ አያሳልፋትም፣ ያለ ሥራ አያባክናትም፣ የሰኔ ጀንበር ውድ ናት፣ የሰኔ ጀንበር ይሳሳላታል፣ እንደ ኢያሱ ጀንበርን ቁሚ ብሎ ማስቆም ቢችል በወደደ ነበር፡፡ ጀንበሯን አቁሟት ያሻውን ለማረስ፣ ለማንደፋረስ፡፡ የኢያሱን ጸጋ ባይቸረውም ጀንበር ዘልቃ እስከጥጠልቅ ድረስ ያለውን ጊዜ ግን ቁጭ ብሎ አያሳልፋትም፤ ላቡን እያንቆረቆረ፣ ወገቡን እንዳሰረ ሲደክም ይውላል እንጂ፡፡
“የበሮቹ እንኳን አላቸው ጥራት፣
ሾሩን ሲቀደው ይመስላል መብራት” የሚባልለት የሀገሬ ገበሬ ጥራት ባላቸው በሬዎቹ፣ ዝናብ ያረሰረሰውን መሬት ሲቀደው ሾሩ ያምራል፣ ፈሰሱ ደስ ይላል፡፡ ይህ ሀገር ሰላም ሲኾን በማለዳ ወጥቶ በጨለማ ወደ ቤቱ የሚመለሰው ገበሬ ሀገር ተደፈረች ሲባል ደግሞ እርፍ በጨበጠበት እጁ መውዜርን አንስቶ፣ ስንቁን አዘጋጅቶ ለጦርነት ይነሳል፡፡ በጀግንነት ተዋድቆ ሀገሩን ያጸናል፣ ጠላትን ያሳፍራል፣ ወዳጅን ያኮራል፡፡
ገበሬ እያረሰ ያጎርሳል፣ እየተኮሰ ጠላት ይመልሳል፣ ለሰላሙም ለክፉውም ጊዜ ዝግጁ ነው፡፡ ሰላም አለ ብሎ ከመተኮስ፣ ክፉ ቀን መጣ ብሎ ከማረስ አይቦዝንም፡፡ እነኾ ክረምቱ መግባት ጀምሯል፤ በበጋው ፀሐይ ያደረቀው የኢትዮጵያ መሬት በዝናብ መረስረስ ጀምሯል፡፡ ምድር አረንጓዴ ካባ ልትለብስ ነው፣ ቅጠላቸውን ያረገፉት ዛፎች ወደ ወዛቸው እየተመለሱ ነው፡፡ አዕዋፋት ጎጇቸውን ቀልሰው፣ የክረምት ወቅት ምግባቸውን ሰብስበው ወደ መክረሚያቸው ይሰበሳባሉ፡፡ የሀገሬ ገበሬ የክረምቱን መግባት መጀመር ተከትሎ ውሎው በማሳው ኾኗል።

“አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት
ያንገበግብ የለም እንደ እግር እሳት” የሚለው አርሶ አደር አርሶ መራብንና ተኩሶ መሳትን እንደ ነውር ይቆጥራል፡፡ አርሶ መራብ፣ ተኩሶ ማሳት ያማል ያንገበግባልና የሀገሬ ገበሬ አርሶ እንዳይርበው፣ ሀገርም እንዳይወቅሰው፣ ጎተራው እንዳይጎድል በትጋት ያርሳል፡፡ ለገበሬ ትልቁ ሕመም በክረምት አለማረስ፣ በመኸር አለማፈስ ነው፡፡ ማራስና ማፈስ እንደማይችል በክረምት ተቀምጦ መዋል ሕመሙ ነው፡፡
በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ቀያቸው የተወረረባቸው፣ ሀብትና ንብረት የወደመባቸው፣ በሬዎቻቸው ታርደው የተበሉባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች በማያባክኗት ወርኃ ሰኔ ቁጭ ብለው መዋል ግድ ኾኖባቸዋል፡፡ ወስኮው ተፈልጦ ሥጋ ተጠብሶበታል፣ ግሬራው ተሰብሯል፣ ማረሻው ተወስዷል፣ ቀየው ተወሯልና ማረስ እያማራቸው፣ ቀየው እየናፈቃቸው፣ ክረምቱ ትዝ እያላቸው እጥፍ ኩርትም ብለው ተቀምጠው ይውላሉ፡፡ ለልጆቻቸው ወተት ሲሉ ወተት፣ እሸት ሲሉ እሸት፣ እንጎቻ ሲሉ እንጎቻ መስጠት እንደማያውቁ ዛሬ ላይ የሰው እጅ አይተው ያድራሉ፣ ነጭና ጥቁሩን ያለ ስስት ከጎተራ አውጥተው እንደማይበሉ ዛሬ ላይ የሰው ፊት እየገረፋቸው ይኖራሉ፡፡ በሀገራቸው ባይተዋር ኾነው ተቀምጠዋል፡፡
ክረምት የሚናፍቃቸው ገበሬዎች በክረምት ወቅት ከቀያቸው ርቀው፣ ከማሳቸው ተለይተው፣ በሬዎቻቸውን አጥተው፣ ፍየሎቻቸውና በጎቻቸው ተበልተውባቸው በሐዘን እየኖሩ ነው፡፡ በሰኔ አንድም ቀን ማባከን የማይሹት ገበሬዎች ለልጆቻቸው እሸትና ወተት መስጠት ተስኗቸው በመጠለያ ውስጥ እየኖሩ ነው፡፡ ልጆች እሸት አይቀምሱም፣ ወተት ቢጠይቁ አይሰጡም፡፡ እንጎቻ አያገኙም፡፡ ለምን ካሉ እነርሱ ቦርቀው ከኖሩበት፣ አፈር ፈጭተው ጭቃ አቡክተው ካደጉበት ቀየ ርቀዋልና፡፡ የሚጠይቁት ኹሉ ትዝታ ኾኗልና፡፡ ቀያቸው ናፍቋቸዋል፣ ሜዳና ሸንተረሩ ትዝ ይላቸዋል፡፡

የማያርሱ ገበሬዎች፣ ማረስ ማፈስ ናፋቂዎች ኾነዋል፡፡ ማረስ ይችላሉ ነገር ግን ማረስ አይችሉም፡፡ ማረስና ማፈስ ይናፍቃሉ ነገር ግን ከኹሉም ርቀዋል፡፡ በሚወዷት፣ በሚሳሱላት፣ በናፍቆት በሚጠብቋት በወርኃ ሰኔ ቁጭ ብለው ይውላሉ፣ ቀያቸውን ይናፍቃሉ፣ በትዝታ ይባክናሉ፣ ልጆች የቦረቁበት፣ በግና ፍየል፣ ላምና በሬ ያገዱበት፣ የቀያቸውን ዘፈን እየፈዘኑ የተደሰቱበት፣ ከጋራና ጋራ ኾነው ዜማ የተለዋወጡበት፣ ዋሽንት የነፉበት ኹሉም ይናፍቃቸዋል፡፡
በአማራ ክልል በዋግኽምራ፣ በሰሜን ወሎ፣ በስሜን ጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ ተፈናቅለው ሳያርሱ የሚከርሙ ገበሬዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ዘርተው ቡቃያ አይጠብቁም፣ አበባ አያዩም፣ ፍሬ አይመለከቱም፣ በመኸር ምርት አያፍሱም፣ ጎተራችን ይሞላል ብለው ተስፋ አይሰንቁም፡፡ ለምን ካሉ በሰኔ አላረሱምና፣ በሰኔ ከቀያቸው ርቀዋልና፣ በሰኔ ማረስ እየናፈቃቸው፣ ማለዳ ጠምዶ ማታ መጥፋት ውል እያላቸው ሳይችሉ ቀርተዋልና፡፡
ነገር ግን ያዘኑበት ዘመን አልፎ፣ ደጉ ዘመን ይመጣል፣ ገበሬው ከበሬው ጋር ይገናኛል፣ ወተትና እሸቱ እንደቀደመው ይመለሳል፡፡
የቦረቁበት ቀዬ የናፈቃቸው ልጆች፣ በጋራው ኾነው የሚያዜሙ እረኞች፣ የእናታቸውን ጡት እየጠቡ የሚዘሉ እንቦሶች ወደ ደስታቸው ይመለሳሉ፡፡ በቀያቸው አጊጠው ይኖራሉ፡፡ በክረምት አርሰው፣ በመኸር አፍሰው ጎተራቸውን ይሞላሉ፡፡ ያዘኑት ገበሬዎች ይስቃሉ፣ የተከዙት እናቶች ይደሰታሉ፡፡ ከልጆቻቸው ጋር ዓለማቸውን ያያሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበአሜሪካ ቨርጂኒያ የምትኖረው የ15 ዓመቷ ታዳጊ ኢትዮጵያዊት በደብረ ብርሃን መጠለያ ለተጠለሉ ሴቶች ድጋፍ አደረገች፡፡
Next articleኢትዮጵያና ጣልያን ለተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚውል የ22 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ።