የዋሊያው መገኛ ቦታ ከፍታ ነው!

203

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ የስልጣኔ ጣራ ማማዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከኤርታሌ የዝቅተኛ ቦታ መዳረሻ እስከ ራስ ደጀን ከፍታ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ውብ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ድምብል ጌጥ ናት፡፡ በረሃ ካጠላበት የሰሃራ በረሃ ምድረበዳ ቅርብ ርቀት ላይ የገነት (ጀነት) ደጆች በኢትዮጵያ ምድር ስለመኖሯ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሽንጠ ረጅሙ የዓባይ ወንዝ እና የተንጣለለው የጣና ሐይቅ ገጸ በረከት ለአፍሪካ ምድር የእርካታ ምንጮች ናቸው፡፡

አልሸነፍም ባይነት፣ የዓላማ ጽናት እና ብርቱ ሀገራዊ ፍቅር የኢትዮጵያዊ መገለጫው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የነካችው ሁሉ ወርቅ፤ የዳበሰችው ሁሉ እርቅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንኳን ግብሩ ስሙ እንኳን ሃያላንን አርዷል፤ ትዕቢተኞችን አዋርዷል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማ መለያው አሸናፊነት እና አልንበረከክም ባይነት ለመኾኑ የአህጉሪቷን በርካታ ሀገራት ሰንደቅ ቀና ብሎ መመልከት ብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡

በሮም አደባባይ በታላቁ የሩጫ ውድድር ማራቶን 42 ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ ሮጦ ሀገሩን በወርቅ ያራቀቃት ሻለቃ አበበ ቢቂላ አሸናፊነቱ ከስፖርታዊ ውድድርም ይሻገራል፡፡ አበበ በሮም ያሳየው አሸናፊነት እና ድል አድራጊነት የኢትዮጵያን ማንነት እና ምንነት ለአውሮፓዊያኑ ሜዳቸው ድረስ ዘልቆ ያመላከተ ሃቅ ነበር፡፡ አበበ ድል አድርጎ ለሀገሩ ያመጣው ሜዳይ ብቻ ሳይኾን ያስመለሰላት እያወቁ የዘነጉትን የኃይለኝነት ታሪክ ጭምር ነበር፡፡

ደራርቱ ቱሉ በሴቶች የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ስታጠልቅ የወከለችው በመሰል ድሎች የተዘነጋውን አህጉር ነበር፡፡ ኃይሌ በአትሌቲክሱ መስክ ደጋግሞ የሀገሩን ሰንደቅ በአሸናፊነት ከፍ ሲያደርገው ያሰረዘላት በድህነት እና ኋላ ቀርነት የወየበውን ስሟን ነበር፡፡ በቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሽ ስህን፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጥምረት በአንድ ውድድር ድርብ ድርብርብ ሜዳይ ሲያነሱ ያስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በልጆቿ ትብብር ታፍራ እና ተከብራ የምትዘልቅ ሀገር መኾኗን ነው፡፡ “አረንጓዴ ጎርፍ” እስከመባል የደረሰው በአትሌቲክሱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ብቻ የተሰጠ የክብር መገለጫ ምልክት (ተብሲር) ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለአህጉራዊው የእግር ኳስ ትንሳኤ ብቅ ማለት አብሪ ኮከብ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ የአህጉራዊው ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር መድረክ መስራች ብቻ ሳትኾን ክብሩም ናት፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ የታሪክ ስፍራ ተሳታፊ እና መስራች ብቻ ሳይኾን አሸናፊ የሚለውንም ዝና እና ክብር ይወክላል፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው ትልቅ የእግር ኳስ መድረክ መጫዎትም፣ በብቃት መምራትም እንደምትችል የክቡር ይድነቃቸው ተሰማን ስም መጥቀስ አንገት አያስደፋም፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር መድረክ ላቅ ያለ እሳቤ ባለቤት እንደነበረች ለማሳየት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በዘር የጨቀየውን የአፓርታይድ ስርዓት በማውገዝ እና በመቃወም አንቱታን አትርፋለች፡፡ የዓለም እግር ኳስ ባለቤት ፊፋ ዘረኝነትን የስፖርቱ ዓለም ጽዩፍ አድርጎ በሕግ ከመደንገጉ በፊት ኢትዮጵያ በተግባር ሞግታበታለች፡፡ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ አበርክቶ በዓለም የእግር ኳስ መርህ መነጸር ፍትሐዊ ሆኖ ከታየ አርአያ የምትባል ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ በመሰረተችው፣ ደጋግማ በተመላለሰችበት እና ዋንጫ ባነሳችበት የአህጉራዊው ታላቅ የእግር ኳስ ድግስ ቀስ በቀስ ስትሸሽ ዳግም ለመመለስ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ይፈጅባታል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ ቀልብ የሚስቡ ደጋፊዎች፣ አቅልን የሚያስት የእግር ኳስ ፍቅር፣ ምትሃታዊ እግሮች እና አይበገሬ ልጆች ያሏት ኢትዮጵያ ለዘመናት ከውድድሩ መድረክ የውኃ ሽታ መኾኗ ለብዙዎቹ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ቁጭትን ፈጥሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ መሰረተችው የውድድር መድረክ ለመመለስ ያደረገው ጥረት እምነት የሚጣልበት ባይኾን እንኳን ተስፋ ሰጪ የሚባል ነው፡፡ ከ31 ዓመታት መጥፋት በኋላ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተቆራረጠም ቢኾን ኢትዮጵያ በመድረኩ አለሁ ማለት ጀምራለች፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ ባይችል እንኳን ግብ ማስቆጠር የሚችል ስብስብ መኾኑን ማሳየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተሳተፈችባቸው የመድረኩ ውድድሮች ከልብ የማይጠፉ ደጋፊዎችን እና ውብ የእግር ኳስ ተፈጥሯዊ ችሎታን አሳይታ ተመልሳለች፡፡ የኢትዮጵያዊያኑን ውብ የደጋፊዎች ሕብረ ዝማሬ ለማየት እና ልብ አንጠልጣይ የእግር ኳስ ተፈጥሯዊ ክህሎት ለመመልከት ወደ ሜዳ የሚገቡት በርካቶች እንደነበሩ ተስተውሏል፡፡

አሁን ደግሞ በ2023 ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ በተያዘለት የአህጉሩ የእግር ኳስ ታላቅ ድግስ ለመሳተፍ ሀገራት ከመሰንበቻው የማጣሪያ ውድድሮችን አድርገዋል፡፡ በዚህ የማጣሪያ ውድድር የእግር ኳስ ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው የዋሊያዎቹ ስብስብ ነበር፡፡ በውድድር መድረኩ ከኢትዮጵያ ጋር መስራች የነበረችው እና ሰባት ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚዋ ሀገር ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽ ነች፡፡ ዋሊያዎቹ በምድብ ማጣሪያው በምድብ አራት ከፈርኦኖቹ ጋር ሲደለደሉ ቅድመ ትንበያዎች ፈርኦኖቹ ቀዳሚ እንደሚኾኑ ያመላክቱ ነበር፡፡

በአህጉራዊው የእግር ኳስ ባለቤት ካፍ የሜዳ ጥራት መመዘኛ መስፈርት ለውድድር የሚያሟላ ሜዳ የላችሁም የተባሉት ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ማድረግ የሚገባቸውን ማጣሪያ ሀገር አዝለው ሰንደቅ አንጠልጥለው በባዕድ ሀገር እንዲያደርጉ ተገደዱ፡፡ ፈርኦኖቹ ሁለተኛውን የማጣሪያ ውድድር በቀላሉ ዋሊያዎቹን አሸንፈው ምድቡን ከወዲሁ ይመራሉ የሚለው ቅድመ ግምት ከ90 በመቶ በላይ አመላከተ፡፡

እግር ኳስን ከሌሎች ውድድሮች በተለየ ተወዳጅ ያደረገው ግን በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ታሪክ የሚቀየርበት የውድድር መስክ መኾኑ ነበር፡፡ ፈርኦኖቹ ሜዳ ገብተው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ያሳዩት እንቅስቃሴም የነበረውን ቅድመ ትንበያ የሚደግፍ ኾኖ ነበር፡፡ ዋሊያዎቹ ከወትሮው በተለየ በላቀ የራስ መተማመን ፈርኦኖቹን ከፈጣን እንቅስቃሴዎቻቸው ገትተው በምትኩ እንደ ሀውልት በየሜዳው ገተሯቸው፡፡ ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት የሚያየውን ምትሃታዊ እንቅስቃሴ ማመን ተሳነው፡፡ ፈርኦኖች እየኾነ ያለውን አምኖ መቀበል ከበዳቸው፡፡

እስከ መጀመሪያው 45 ደቂቃ ዋሊየዎቹ ዘጠኝ ዒላማቸውን የጠበቁ መከራዎችን እና አራት ያለቀላቸው የግብ እድሎችን ፈጥረው ሁለቱን ወደ ግብ ቀየሯቸው፡፡ እስከ መጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ተጫዎቾችን ለመቀየር የተገደዱት ፈርኦኖች ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አንድ ተጫዋች ቢቀይሩም ውጤቱን መቀልበስ ግን ራስ ደጀን ተራራን የመውጣት ያክል ከበዳቸው፡፡ ዋሊያዎቹ በፍጹም የበላይነት ወደ መቀመጫቸው ከፍታው ላይ ወጥተው ነበርና ፈርኦኖቹ ባልጠበቁት መንገድ ፈራረሱ፡፡

ኢትዮጵያ ከ1989 በኋላ ግብጽን አሸነፈች፡፡ የዓባይ ደርቢ በወንዙ ውኃ ባለቤት ሃገር ፍጹም የበላይነት ተደመደመ፡፡ ካይሮ የሃዘን ማቅ አጠለቀች፤ የሃፍረት ሸማ ተከናነበች፡፡ በአንጻሩ የዋልያወቹን መዲና አዲስ አበባን ደስታ እና ፌሽታ እንደ ዓባይ ውኃ አጥለቀለቃት፡፡ የአዲስ አበባ ድል እና የካይሮ ሽንፈት ለዓለም ጆሮ ትኩስ መረጃ ኾነ፡፡ ይህ የትናንት ክስተት ነው፡፡ ሽንፈት ያሸማቀቀው የግብጽ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ሰብሰባ ሲጠራ አንድ ቀን እንኳን መታገስ አልቻለም፡፡ የአሰልጣኙን ሪፖርት ለማድመጥ እና የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የቋመጠው የግብጽ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትምሕርት ነው፡፡

ዋሊያዎቹ ወደ ተፈጥሯዊ መቀመጫቸው ከፍታ ዘልቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ መውረድ ከከፍታ መከስከስ ነው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የማይቻል የሚመስለውን ችለው አሳይተዋል፡፡ በድሮ በሬ ያረሰ የለም፡፡ ስለድሉ የሚበቃውን ያክል ነው ባይባልም እውቅናም ጆሮም አግኝቷል፡፡ አሁን ስለቀጣዩ መምከር፣ ለሚመጣው መዘጋጀት እና ከአሸናፊነት ላለመውረድ መደራጀት ይጠይቃል፡፡

ነጻ ሀገር ያላቸው የዋሊያዎቹ ስብስብ ሀገር ተሸክመው እና ሰንደቅ ዓላማ አዝለው ከሜዳቸው ውጭ ሲጫዎቱ አንገት የሚደፋ እና የሚሸማቀቅ መንግሥት እና ባለድርሻ አካል ካለ ለዛሬ ባይደርስ እንኳን ለነገ ከዛሬ ይጀምር፡፡ ተጫዋቾቹ እንደኾኑ በባዕድ ሀገር ማሸነፍ እንደሚቻልም አሳይተዋል፡፡

የስፖርት ምሁራን የትናንቱ ጣፋጭ ድል ሚስጥር እና የሰነበተው ሽንፈት ምክንያቶችን ዳስሰው ምክረ ሃሳብ ይሰንዝሩ፡፡ የስፖርቱ ባለሥልጣናት ከግብጽ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትምሕርት ወስደው ስለቀጣዩ የቤት ሥራዎቻቸውን ከወዲሁ ይጀምሩ፡፡ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከወቅታዊ ትችት እና ሙገሳ ወጥተው የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን መገንባትን እና የሕዝብ ድጋፍ ማደራጀትን ሥራዬ ብለው ይያዙ፡፡ ተጫዋቾች በትናንት ድል ሳይዘናጉ ከፊታቸው ለሚመጣው ትግል ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ከዚህ በኋላ መውረድ በተሟሟቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ውኃ መቸለስ ነው፡፡

የትናንቱ አሸናፊነት በዋሊያዎቹ ጥንካሬ እንጂ በፈርኦኖቹ ድክመት እስካልተገኘ ድረስ ነገም አሸናፊ ከመኾን የሚያግዳቸው ኃይል የለም፡፡ አሸናፊነት ከውስጥ ሲመነጭ የሌሎች ጥንካሬም ኾነ ድክመት ለአሸናፊዎቹ ቦታ የለውም፡፡ በተረፈ ግን የኢትዮጰያ ሕዝብ ማንንም ቢኾን ማሸነፍ እንደሚቻል ትናንት አይቷልና በነገው አሸናፊነት ፍጹም አይጠራጠርም፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo Caamsaa 30/2014
Next articleየወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው ሲሉ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) አስታወቁ።