❝ዋልያው ፈርዖኑን ገርስሶታል፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ካይሮን አስደንግጧል❞

148

ሰኔ 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ፍጡር ፈጣሪውን፣ ልጅ አባቱን አይቀድምም፣ ለክብር የተሰለፈ፣ ለድል የቆመ አይወድቅም፣ አይሸነፍም፣ ከአሸናፊ ሕዝብ የተፈጠረ፣ በአሸናፊነት ታሪኩ የጠጠረ ሕዝብ ልኮት፣ አይዞህ በርታ ብሎት የሚሸነፍ፣ ክብሩን የሚያዛንፍ የለም፡፡ በአሸናፊነት ልቆ፣ ክብሩን አስጠብቆ ይመለሳል እንጂ፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በጥቁሮች ምድር በኩራት ተውለብልቧል፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስም በተደጋጋሚ እየተጠራ በሕብረ ዝማሬ ተዘምሯል፣ እንባ በተቀላቀለበት ዜማ ተዚሟል፣ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስም ከዳር እስከ ዳር ተስተጋብቷል፣ ሠንደቁ የአሸናፊነት ምልክት፣ የድል ብሥራት መኾኑን አስመስክሯል፡፡ የእምየ ልጆች በሜዳው ነግሠውበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአንድነት የደስታ እንባ አንብተዋል፣ በልጆቻቸው ብቃት በደስታ ተውጠዋል፣ በሐሴት ባሕር ውስጥ ጠልቀዋል፣ ሠንደቁን ያነገቡት፣ የኢትዮጵያን ስም የያዙት፣ የኢትዮጵያዊነት ውክልና የተቀበሉት ልጆች በጥቁሮች ሰማይ ሥር እንደ አሻቸው ሲኾኑ አይተዋቸዋልና የደስታ እንባ ተናነቃቸው፣ ደስታ ፋታ አሳጣቸው፡፡ ሐሴት አሰከራቸው፡፡
ሚሊዮኖች ልጆቻቸውን በአሻገር እየተመለከቱ ናፈቋቸው፣ ሳሱላቸው፣ መልካሙን ተመኙላቸው፣ በአሻገር አበረታቷቸው፣ በመንፈስ አብረዋቸው በሜዳው ተመላለሱ፣ ሠንደቃቸውን አነሱ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በተደጋጋሚ ከፍ እያለ፣ የአሸናፊው ሠንደቅ ወኪሎች የእምየ ኢትዮጵያ ልጆች አይለዋልና ከኢትዮጵያ ወደ ማላዊ የተሻገሩ የኢትዮጵያውያን ዓይኖች እንባ መላቸው፣ የኢትዮጵያውያን ጉንጮች እንባ ፈሰሰባቸው፣ እንባቸው ግን የሐዘን አልነበረም፣ የደስታ የሐሴት ነው እንጂ፡፡

የግዮን እናት፣ የነጻነት እመቤት፣ የአሸናፊነት ምልክት፣ የጥበብ መፍለቂያ፣ የተጨነቁት መጠለያ፣ ጥቁርን ያኮራች፣ በግፍ የተነሳን ያንበረከከች፣ ለቀኝ ግዛት የመጣውን የደመሰሰች፣ ለተጨነቁት የደረሰች፣ ለጥቁር መብት የተከራከረች፣ ለፍትሕ በዓለም አደባባይ በጽናት የታገለች፣ ታግላ ፍትሕን ያመጣች፣ በጀግና ልጆቿ የማይሻር ታሪክ የቀረጸች፣ በታሪክ ድርሳናት ቀድማ የተመዘገበች፣ ከፍ ብላ የተቀመጠች እመቤት፡፡
መውደቋን የሚመኙት ማሸነፏን ያያሉ፣ ሐዘኗን የሚያልሙ ስትስቅ ይመለከታሉ፣ ጠላት የማይገምታት፣ ማንም የማይደፍራት ንግሥት ናትና፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን የመሠረተችው፣ የአፍሪካ አንድነትን የጠነሰሰችው፣ የጥቁርን ዘር በመላ ያኮራችው፣ ከታሰረበት የጨለማ ቤት ውስጥ ያወጣችው፣ በጨለማ ዘመን ብርሃን እያበራች ሕዝብን የመራችው ኢትዮጵያ በመሠረተችው ድግስ ለመሳተፍ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ነበሩባት፡፡ ጨዋታዎቹን ግን በሜዳሽ አናጫውትሽም ተባለች፡፡ ልጆችሽ በሕዝባቸው ፊል ለፊት፣ በምድራቸው፣ በሜዳቸው በተወለዱበት ሀገራቸው አይጫወቱም ተብላ ተከለከለች፡፡ ምክንያቱ ደገሞ የሚመጥን ሜዳ የለሽም የሚል ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በሜዳየ ልጫወት ብላ በጠየቀችበት ወቅት መሐመድ ሳላህን የመሰለ ተጫዋች በዚያ ስታዲዬም እንዲጫወት የምንፈቅድልሽ ይመስልሻል ወይ? ተብላ ነበር፡፡ ለምን ክብር የሚሰጠው ተጨዋች ነውና፡፡ ይህ መልስ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡

የግብጽ እግርኳስ ፌደሬሽንም ሙሉ ወጫችሁን ልሸፍንላችሁ እና በሜዳችሁ የምትጫወቱትን ጨዋታ ካይሮ ላይ ተጫወቱ ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ አዝኖላት አልነበረም፤ የራሱን ክብር ለማስጠበቅ እንጂ፡፡ በደካማ ጎን ገብቶ የሥነ ልቦና ጫና ለማድረስ ከኢትዮጵያ እንሻላለን ለማለት ነበር ጥያቄውን ማቅረቡ፡ ነገር ግን ጥያቄው ለኢትዮጵያ ክብር የሚመጥን አልነበረምና ውድቅ ተደረገበት፡፡ እኛ ክብር አዋቂ ሕዝቦች ነን፣ ለክብር እጥፍ አንልም የሚል መልስ ተሰጣቸውና ዝም አሉ፡፡
ባለሀገሮቹ ሀገር እንደሌላቸው፣ ሕዝብ እንደማይወዳቸው ተሰደው ተጨዋቱ፣ የመረጧት የመጫወቻ ሀገር ደግሞ ማላዊ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በመሠረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ድግስ ላይ ለመሳተፍ በምድብ ማጣሪያው ውጤት መሰብሰብ ግድ ይላታል፡፡ እርሷ በተደለደለችበት ምድብ ከእግር ኳስ በላይ የተለየ ትርጉም የሚሰጠው፣ የሁለቱ ሀገራት ሕዝብ በተለየ አተያይ የሚጠብቀው ተጋጣሚ ነበራት፡፡ ይህችም ተጋጣሚ ግብጽ ነበረች፡፡
የኢትዮጵያና የግብጽ ጨዋታ ከስፖርታዊ ተዝናኖት የዘለለ ትርጉም አለው፣ ሜዳ ላይ የሚመዘገበው ውጤት በስፖርት አምድ ብቻ ተለክቶ የሚቀር አይደለም፤ ብዙ መልክ አለው፣ በብዙ መንገድ ይተነተናል፡፡ ከስፖርት በተጨማሪ ሌላ ትርጉም፣ ሌላ ክብደት ይሰጠዋል እንጂ፡፡ የካይሮ ሹማምንት በጉጉት ይጠብቁታል፣ በሜዳ ላይ የሚያገኙትን ድል ከሜዳ ውጭ ለሌላ ትርክት ይፈልጉታል፣ አሸናፊዎች ነን እያሉ ይዘምሩበታል፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚገኝ ድል ለካይሮ ሹማምንት ልክ የሌለው ደስታ፣ ወሰን የለሽ እርካታ ነውና፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ድልን መቀዳጀት የሚሹት፣ የኢትዮጵያን መሸነፍ መሽቶ እስከሚነጋ የሚመኙት ግብጻውያን ሜዳ አልባዋን ኢትዮጵያን ማሸነፍ ሌላ እርካታ ይሰጣቸዋል፡፡ ከደስታ ላይ ደስታ ይጨምርላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ከቻሉ የሚያሸንፏት በእግርኳስ እንደኾነ ተማምነዋል፤ ሌላው ግጥሚያ ኹሉ እንደማይኾንላቸው አስቀድመው ተረድተውታል፣ በታሪካቸው አውቀውታል፣ በደንብ አድርገው ተምረውበታል፡፡ ልጆቻቸውን ከካይሮ ወደ ሊሎንጎዌ ሲሸኙ በድል እንደሚመለሱ አልተጠራጠሩም፡፡
ኢትዮጵያውያንም ቢኾኑ ይሄን ጨዋታ እንደ ጨዋታ ብቻ አይመለከቱትም፣ በቀላል ነገር አያዩትም፣ በክብራቸው ለክተው፣ እጅግ ጓጉተው ያዩታል እንጂ፡፡ ኹልጊዜም የኢትዮጵያን መሸነፍ በምትመኝ ሀገር ፊት መሸነፍ ስብራቱ ከባድ ነው፡፡ ለወትሮው በኢትዮጵያ ላይ የድል ጭላንጭል ስትመለከት የምትደሰተው ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ድል ካመጣች ምን ሊሰማት እንደሚችል አስቀድመው ይረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያና የግብጽ ጨዋታ ታሪክ የሚመዘዝበት፣ የሥልጣኔ ቀደምትነት የሚጠቀስበት፣ የግዮን ወንዝ የሚነሳበት፣ የሥርዓት የበላይነት የሚቆጠርበት፣ ትናንት የሚታወስበት፣ ዛሬ የሚፈተሽበት፣ አቅም የሚታይበት፣ ነገ የሚተነበይበት ነው፡፡ እንደሌሎቹ ተጫውተው የሚረሱት፣ እንደ ቀላል ድል የሚያዩት አይደለም፡፡ ከፍ ያለ ክብር ይሰጠዋል፡፡

ግብጽ ከአፍሪካ ተሻግሮ በአውሮፓ የገነነው ልጇ፣ መመኪያ መኩሪያ የምትለው በጉዳት ምክንያት ታላቅ ግምት ከሚሰጠው ጨዋታ ውጭ መኾኑ አስቀድሞ ተረጋገጠ፡፡ የልጇ አለመኖር ብዙ እንደሚያጎድልባት ቢገባትም በኢትዮጵያ ላይ ድል እንደምትቀዳጅ ግን የተጠራጠረች አትመስልም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ ከአፍሪካ ተሻግሮ በዓለም እግር ኳስ ፊት የገነነ፣ የዓለም ተከላካዮች የሚፈሩት፣ አሰልጣኞች አስቀድመው የሚጨነቁበት፣ የአሰላለፍና የአጨዋወት ስልት የሚቀይሩበት ገናና ተጨዋች አልነበራትም፡፡ ነገር ግን ለክብር የሚነሱ፣ በአንድነት ለድል አድራጊነት የሚገሰግሱ ልጆች ነበሯት፡፡
የተጠበቀው ጨዋታ በማላዊ ሰማይ ሥር ተደረገ። የኢትዮጵያውያን ዓይኖች ከመላው ዓለም ወደ ማላዊ ተወርውረው በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ለባሾች ላይ አፍጥጠዋል፡፡ የግብጻውያን ዓይኖችም ከፈርዖኖቹ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ የሚሊዮኖችን አደራ የተቀበሉት፣ ኢትዮጵያን የወከሉት፣ ኢትዮጵያን የሚመስሉት ልጆች ፈርዖኖቹን አጣደፏቸው፡፡ ግብጾች ያልጠበቁት፣ ይኾናል ብለው ያልገመቱት እዳ ወደቀባቸው፡፡ ዋልያዎቹ በተደጋጋሚ የፈርዖኖቹን የሜዳ ክልል አጨናነቁ፡፡ ይባስ ብለው ግባቸውን ደፈሩ፡፡ ፈርዖኖቹ እየተፍረከረኩ፣ ዋልያዎቹ እየፈኩ ሄዱ፡፡ የማላዊ ሰማይ ሥር በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ደመቀች፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ኾነች፡፡ ግብጽ ለኢትዮጵያ እጇን ሰጠች፡፡ የካይሮ ሹማምንት ከእግር ኳስ በላይ የጠበቁት፣ ለሌላ ትንታኔ ያዘጋጁት ግጥሚያ ሳይኾን ቀረ፡፡ ልጆቻቸው እጅ ሰጡባቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በድል ከፍ አሉ፡፡ አሸናፊነታቸውን አስመሰከሩ፡፡ እነኾ ዋልያው ፈርዖኑን ገርስሶታል፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ካይሮን አስደንግጧል፡፡ የኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አጊጧል፡፡ ዋልያ ዋልያ የሚለው ዜማ ከፍ ብሎ ተሰምቷል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሶማሊያ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ላይ መታደማቸው የቀጣናውን ግንኙት ለማሳደግ አንደሚረዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
Next article“በአማራ ክልል ሁሉም የፀጥታ መዋቅር የተወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ከፍተኛ ውጤት የታየበት ነው”፡- የመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት