
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር የትውውቅ መርኃግብር አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌ ተወካዮች፣ እናቶች እና ወጣቶች በተገኙበት የትውውቅ መርኃግብር አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ሌሎች አባላትም በመድረኩ ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) “አንድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በምክክርና በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል”ብለዋል።
ልዩነትን በማጥበብና በመቻቻል የተመሠረተች ጠንካራ ሀገር እንድትኖር የአማራ ክልል መንግሥት ከሀገራዊ ምክክሩ ጎን በመኾን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የልዩነትን አጀንዳዎች ለመቀነስ እና አንድነትን ለማጠናከር አልሞ የተቋቋመ መኾኑን ተናግረዋል።
“የሀገራችን ሕዝቦች ላያግባቡ የቻሉ ጉዳዮችን ነቅሰን በማውጣት እንድንወያይባቸው እና የጋራ መግባባት ላይ እንድንደርስ አልመን እየሠራን ነው” ብለዋል። በዚህ ኹሉ ሂደት ውስጥ ኹሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩል መሳተፍ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲኾን ምንም አይነት የውስጥም ኾነ የውጭ ጣልቃገብነት ሳይኖር እንደሚሠሩም ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።
“ብዙ ጊዜ እርቅ ቢካሄድም ዘለቄታ ግን አልነበረውም ምክንያቱም በበሰለ ውይይትና መግባባት ላይ የተመሠረተ ባለመኾኑ ነው” ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኹሉንም ባካተተ እና በበሰለ ውይይትና መግባባት ላይ በተመሠረተ ሂደት የእርቀ ሰላም ሥራዎችን ያከናውናል ነው ያሉት።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር እና አባል አቶ ዘገየ አስፋው የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ በድርድር የተወሰነ ወገን አሸንፎ የሚወጣበት ሳይኾን የጋራ አጀንዳዎችን በመለየት ለሕዝብና ለሀገር የሚበጀውን ነቅሶ በማውጣት ለመንግሥት የሚያሳውቁበት እንደኾነ ነው የተናገሩት።
መንግሥትም ኾነ የትኛውም አካል በሂደቱ ላይ ጣልቃ አይገባም ብለዋል። በውይይት የተገኙ ውጤቶችን ኮሚሽኑ ለመንግሥት አስረክቦ መንግሥትም እንደ አሠራር አስቀምጦ ተግባራዊ ያደርጋል ነው ያሉት።
“ቀደም ሲል በሀገሪቱ የተለመደው የእሰጥ አገባ አካሄድ በዚህ ኮሚሽን ውስጥ አይሠራም፤ ሂደቱ በሐሳብ የበላይነት፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶችም ምክረ ሐሳብ ጭምር የሚጎለብት ነው” ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የአባቶች፣ የእናቶች፣ የወጣቶች እና የመላ ኢትዮጵያውያን መልካም እገዛ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሌላው ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያም “አሁን ያለንበት ሀገራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢኾንም እንደሰለጠነ ሕዝብ ቁጭ ብለን መነጋገርና መደማመጥ ከቻልን ከገባንበት ሀገራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንወጣለን” ነው ያሉት።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይኽንን የመወያየትና የመግባባት ሂደት ለመምራት ከመንግሥት ዕውቅና አግኝቶ መቋቋሙ ትልቅ ተስፋ እንደኾነም ገልጸዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው ያሉት አቶ መላኩ ለውጤታማነቱ አካታች የኾነ የሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አባላት ካነሷቸው ሐሳቦች መካከልም:-
👉 ኮሚሽኑ ትኩረቱን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማድረግ አለበት፡፡
👉 ከውይይት ይልቅ በመጠላላት ላይ የተመሠረተ ፓለቲካ እንዳይኖር ኮሚሽኑ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶችን ማድረግ አለበት፡፡
👉 ውሳኔ በሚሰጥባቸው የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመላው ሕዝብ ሐሳብ ተሰጥቶበት እንጅ የተወሰኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ብቻ በተስማሙበት መኾን የለበትም፡፡
👉 የተለየ አጀንዳ ይዘው ምክክሩን ሊያደናቅፉ የሚችሉ አካላት በቀጥታ ከመሳተፋቸው በፊት ቀድሞ የማረቅ ሥራ ቢሠራ ጥሩ ነው፡፡
👉 የጦርነትም ኾነ የሰላም ሐሳብ ያላቸው ኹሉም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ መሳተፍ አለባቸው እንጅ አንድም የሚታለፍ አካል መኖር የለበትም።
👉 በምክክር መድረኩ ላይ ወጣቶች በስፋት መሳተፍ አለባቸው። የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ወጣቶችን የመምከር ኀላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸውና ሌሎች መሰል ሐሳቦችም በተሳታፊዎች ተነስተዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/