የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ አዎንታዊ ለውጦች እያስመዘገበ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታወቀ፡፡

147

ደብረ ታቦር: ግንቦት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በወቅታዊ የዞኑ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሕዝቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ቡድን ለመመከት የፈፀመው ጀብድ ምንግዜም የሚወሳ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል፡፡
ከኅልውና ዘመቻውና ከድሉ ማግስት አማራ ክልል የገጠሙት ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ዋና አሥተዳዳሪው በደቡብ ጎንደር ዞንም የወንጀልና ወንጀለኞች መበራከት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ብለዋል፡፡ የሕገ ወጥነት መበራከት ሕዝቡ ወጥቶ ለመግባት እስከ መፍራትና በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ አድርጓል፤ በልማትና መልካም አሥተዳደር ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዝርፊያ፣ በግድያ፣ በኮንትሮባንድና በጦር መሳሪያ ዝውውር ሰፊ ችግሮች ስለነበሩ ሕዝቡ ሕግ እንዲከበር በመሠረታዊነት እንደጠየቀ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ዘርፈ ብዙ የኾነውን ሕገ ወጥነት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
ከሕዝቡ ጥያቄ በመነሳትም ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ በመወሰንና ለሕዝቡ በማሳወቅ ወንጀለኖችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ መሠራቱን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው እስካሁን ድረስ 745 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሕግ ማስከበር ሥራ በመሠራቱ በዞኑ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ መኾናቸውን አቶ ይርጋ ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ መዋቅሩ ሕግን ለማስከበርና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ቁርጠኛ መኾኑንም አረጋግጠዋል፡፡ ከሕገ ወጦች ጎን የነበሩ አንዳንድ ኃይሎች የተስተካከለ አመለካከት መያዛቸውን ዋና አሥተዳዳሪው በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
ተደራጅተው ሕገወጥ ሥራ ለመሥራት ምልክት ያሳዩ የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መግባታቸውንና የሕዝቡ ሰላም መመለሱንም ገልጸዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው እንዳብራሩት እየተከናወነ ባለው ሕግ ማስከበር ሥራ በዞኑ በማንኛውም ቦታ ከፀጥታ ኃይሉ ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ቀንሷል፤ ኅብረተሰቡ በሕግ ማስከበሩ ሥራ ንቁ ተሳታፊ ኾኗል፡፡ በዞኑ የሕግ ማስከበር ሥራው ውጤታማ መኾኑን ነው ዋና አሥተዳዳሪው ያረጋገጡት፡፡
በተጀመረው ሕግ የማስከበር፣ ሰላምን የማስፈንና ልማትን የማስቀጠል ሥራ ዋና ተጠቃሚ ሕዝቡ መኾኑን አቶ ይርጋ ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን በመከታተልና ለሕግ አስከባሪዎች በመጠቆም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ በመሥራት ለሰላሙ እንዲሠራ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከደብረ ታቦር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝እማማ በጀግንነት ጠብቁኝ፣ በአንድነት አስከብሩኝ ብላለች❞
Next articleሀገረ ስብከቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ።