
ግንቦት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እንቅልፍእንዳይጥላችሁ፣ ክፉ ነገር እንዳይገዛችሁ፣ በአንድነታችሁ ነፋስ እንዳይገባባችሁ፣ ፍቅራችሁን ጠላት እንዳያይባችሁ፣ ጉልበታችሁን ፈሪ እንዳይለካባችሁ፣ ሡሪያችሁን እንዳይገመትባችሁ፣ የማትገመቱ ጀግኖች፣ የማትደፈሩ አንበሶች፣ የማትጨበጡ ነብሮች ኹኑ፡፡
እትብት የተቀበረባት፣ ተድላና ደስታ የታየባት፣ ጠላቶች የእጅ መንሻ የሚያቀርቡባት፣ አንገታቸውን ደፍተው ይቅርታ የሚጠይቁባት፣ ወዳጆች ሲደክማቸው የሚያርፉባት፣ ሲርባቸው የሚጎርሱባት፣ ሲጠማቸው የሚጠጡባት፣ ተስፋ ሲያጡ ተስፋ የሚሰንቁባት፣ ጀግና እና ኩሩ የሚወለድባት፣ ጠይም መልከ መልካም የሚፈጠርባት፣ በማዕልትና በሌሊት ሳይቋረጥ የፈጣሪ ስም የሚጠራባት፣ ቅዱሳን የሚኖሩባት፣ ስዱዳን የሚጠለሉባት ድንቅ ምድር፡፡
ሌሎች በጨለማ ውስጥ በነበሩበት ዘመን እርሷ በብርሃን ተረማምዳለች፣ ሌሎች በባርነት በነበሩበት ዘመን እርሷ በነጻነት ተመላልሳለች፣ ጠላቶቿን አንበርክካ ምድሯን አስከብራለች፣ ጀግንነቷን አስመስክራለች፣ ዓለማት ባንቀላፉበት ጊዜ እርሷ በስልጣኔ ገስግሳለች፣ ከዋክብትን ቆጥራለች፣ ውቅያኖስን ለክታለች፣ ፊደላትን ቀርጻ፣ ብራና ፍቃ፣ ቀለም በጥብጣ ታሪክ መዝግባለች፣ ፍጥረታትን መርምራለች፣ ሌሎች በደሳሳ ጎጆ በሚኖሩበት በዚያ ዘመን ድንጋይ ጠርባ፣ ዓለት አቅልጣ ሐውልት አቁማለች፣ ዓለም እንዳይደርስባት አድርጋ ከላይ ወደታች በጥበብ አንጻለች፣ ደርባና ምድር ቤተ መንግሥት ገንብታለች፡፡
በኃይላቸው ያሰገበሩት ለእርሷ ገብረውላታል፣ በኃይላቸው ድል ያደረጉት ለእርሷ ግን ሰግደውላታል፣ ማንም አያሸንፈንም ያሉት በክንዷ ተመትተዋል፣ በግርማዋ ወድቀዋል፣ ይቅርታዋን ትሰጣቸው ዘንድ ከሠንደቋ ግርጌ በግንባራቸው ተደፍተው ይቅርታ ለምነዋል፣ የምስጢራዊነቷን ልክ፣ የጀግንነቷን ወሰን በደረሱበት ኹሉ መስክረዋል፡፡ እርሷን ሊያጠቁ በሰሜን የመጡት በሰሜን ቀርተዋል፣ በምዕራብ የመጡት በምዕራብ ጠፍተዋል፣ በምሥራቅ የመጡት በምሥራቅ አመድ ኾነዋል፣ በደቡብ የመጡት ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡ በፍቅር የመጡት ግን ከፍቅሯ ማዕዛ አሽትተዋል፣ ከደግነቷ ፍሬ በልተዋል፣ ከመልካምነቷ ጥላ ሥር ተጠልለዋል፣ በሜዳዎቿ ቦርቀዋል፣ በወንዞቿ ተደስተዋል፣ በተራራዎቿ ተደንቀዋል፡፡
ስለ ክብርሽ ድርሰናቱ ኹሉ የሚመሰክሩልሽ፣ ጥቁሮች ኹሉ እናታችን የሚሉሽ፣ በአንቺ መንገድ ተጉዘው ነጻነትን ያገኙብሽ፣ እልፍ ጀግኖች ልጆችሽ በምድርሽም በሰማይም ስለሚውለበለበው ሠንደቅሽ ሲሉ የተሰውልሽ፣ ደማቸውን ያፈሰሱልሽ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱልሽ እማማ ኢትዮጵያ ኾይ በሚመችም በማይመችም ዘመን ስለ ክብርሽ እንቆማለን፡፡
በስምሽ የዘመቱት ኹሉ በድል ተመልሰዋል፣ ጠላቶቻቸውን አሳፍረዋል፣ ክብርሽን አስከብረዋል፣ ሠንደቅሽን በክብር አውለብልበዋል፡፡ እንደ ማዕበል የመጣውን ጠላት ወኔ አልባ ያደረግሽ፣ ዓለም የመሸነፍሽን ዜና ለመስማት ሲጓጓ የድል አድራጊነትሽን ዜና ያደረስሽ፣ ጥቁር ነጭን አያሸንፈውም በተባለበት ዘመን በልጆችሽ ብርታት በእኩለ ቀን የደመሰስሽ፣ የዓለምን አመለካከትና አካሄድ የቀየርሽ፣ የጥቁርን ዘር በሙሉ ለነጻነት እንዲነሳ የጨለማ ውስጥ መብራት የኾንሽ ቢጫ ወርቋ ኢትዮጵያ ኾይ ለክብርሽ ሞትን እንንቃለን፡፡ ሠንደቅሽን አስቀድመን ለክብርሽ እንዋደቃለን፣ በሠንደቅሽ ግርጌ ቃል ኪዳናችንን አሥረን፣ በቃልሽ ታሥረን እናስከብርሻለን፡፡
ኹሉ ያለሸ፣ ደግነት፣ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ጽናትና ብልሃት የተቸረሽ፣ ለፍትሕ በዓለም አደባባይ የምትከራከሪ፣ ስለ እውነት፣ በእውነት የእውነት የምትኖሪ፣ የጠቢባን እናት፣ የምድር እመቤት፣ የነጻነት፣ የፍትሕና የአሸናፊነት ምልክት፣ ዘላለም ንግሥት የኾንሽ፣ በሰማይና በምድር ሠራዊት የተጠበቅሽ እማማ ኢትዮጵያ ኾይ ስለ ክብርሽ እጅ እንነሳለን፡፡
አበው ኢትዮጵያዊነት በሚል መንፈስ ተግባብተው፣ ኢትዮጵያዊነት በሚል ገመድ ተሳስረው፣ ኢትዮጵያዊነት በሚል መንገድ ተጉዘው፣ የኢትዮጵያን ስም ጠርተው፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ከፊት አስቀድመው ክብሯን እያስጠበቁ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዘመናት አልፈው ዘመናት ተከታትለዋል፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር የማያልፍ አንድ ኃያል ምስጢር አለ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይሉት ኃያል ምስጢር፡፡ ደበዘዘ ሲሉት ፈክቶ የሚያድር፣ ተለያየ ሲሉት የሚያብር፣ ተሰበረ ሲሉት የሚጠነክር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከኹሉም በላይ የሚያስቀድሙት መመሪያቸው፣ የሚመሩበት መርሃቸው፣ የሚጓዙበት መንገዳቸው፣ የሚያሸንፉበት ኃይላቸው ነው፡፡
አባቱ ሲያልፍ ልጁ የአባቱን ጦርና ጎራዴ ከቃል ኪዳኑ ጋር እያነሳ እምየ ኢትዮጵያን ጠብቋል፡፡ በየመዘናቱ እልፍ ጠላቶች ተነስተው፣ በእልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች ተመትተው ኢትዮጵያ በክብር ኖራለች፡፡ በጽናት ዘልቃለች፡፡ የቀደሙት ሀገራቸውን አስከብረው ጽኑ ቃል ኪዳን አኑረው አልፈዋል፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ደግሞ ሀገራቸውን ተረክበዋል፡፡
የቀደሙት እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው፣ ውኃ ከወንዝ ቀድተው፣ በጋሻ መክተው፣ በጎራዴ መትተው፣ በጦር ወግተው ነበር ሀገራቸውን ያስከበሩት፡፡ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ጠላት በጦርና በጎራዴ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ መልሰዋል፡፡ የሞከሯቸውን ደምስሰዋል፡፡ በድል አድራጊነትና በኩራት በጠላት ሰፈር ተረማምደዋል፡፡
የቀደሙት አባቶች ልጆች ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ከአባቶቻቸው ወርሰው፣ የዘመኑን መሳሪያ ታጥቀው ሀገራቸውን ለመጠበቅ ከየአቅጣጨው ተጠራርተው በዳር በድንበር ተቀምጠዋል፡፡ ረሃብና ጥሙን ችለው፣ ብርድና ሀሩሩን ተቋቁመው ለኢትዮጵያ ፍቅር ለኢትዮጵያውያን ክብር ሲሉ አዳራቸውን ምሽግ አድርገዋል፡፡ ሲያሻቸው በሰማይ እየበረሩ፣ ሲያሻቸው በምድር እየሰገሩ ጠላቶቻቸውን ይቀጣሉ፡፡ ኢትዮጵያን እንድፈር ያለውን ኹሉ ቀጥተው ይመልሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት ልበ ሙሉ ነው፡፡ ከታሪክ ላይ ታሪክ ለመደራራብ በእልህ የሚገሰግስ ጀብደኛም ነው፡፡ በአባትና እናቱ የተከበረች ሀገር በእርሱም ዘመን የበለጠ ተከብራ ትኖር ዘንድ ይሻልና፡፡ ኢትዮጵያውያን ይመኩበታል፣ መከታችን ይሉታል፡፡ እርሱም አያሳፍርም፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየቀጣ ወገኖቹን ያስደስታል እንጂ፡፡
ከራስ በላይ ለሀገር የሚል መርህ ያለውን ሠራዊት መቀላቀል አብዝቶ ያኩራል፡፡ ኢትዮጵያን አብዝቶ የሚወድድ፣ ጠላት እንዳይደፍራት የሚሻ ኹሉ ወታደርነትን ይምረጥ፡፡ ወታደር ስትኾን ሀገርህ ትጠበቃለች፣ ወታደር ስትኾን ኢትዮጵያ ትኮራለች፣ ወታደር ስትኾን አንድነት ይመጣል፣ ወታደር ስትኾን ጠላት መውጫ መግቢያ ያጣል፡፡
እማማ በጀግንነት ጠብቁኝ፣ በአንድነት አስከብሩኝ ብላለች፡፡ በንቃት ጠብቃት፣ አንድ ኾነህ አስከብራት፡፡ ስምህን በማያረጀው ብራና ላይ በማይደበዝዝ ቀለም ማጻፍ ከፈለክ ወታደር ኹንና ታሪክ ሥራ፡፡ ለኢትዮጵያ ክብርና ፍቅር ሲሉ ጀግንነት የፈጸሙት ናቸው ስማቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደ ዥረት ሲፈስስ የሚኖረው፡፡ በደማቸው ታሪክ ጽፈዋልና ትውልዱ ኹሉ እየተመካባቸው፣ እያከበራቸው ይኖራል፡፡ ትውልድ የማይረሰው ታሪክ ለመሥራት ወታደር ኹንና ሀገርህን ጠብቃት፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/