
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር በአማራ ክልል ለአምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ድርጅቱ በክልሉ የነበረውን የአምስት ዓመታት ቆይታ የመዝጊያ ፕሮግራም በባሕር ዳር አካሂዷል።
የትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር ኀላፊ መንግሥቱ አስናቀ (ዶ.ር) ድርጅቱ ባደረገው የአምስት ዓመታት ቆይታ በሥነተዋልዶ፣ በእናቶች፣ በጨቅላ ሕፃናት፣ በሕፃናት፣ በወጣቶች፣ በሥርዓተ ምግብና በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ ሲሠራ እንደቆየ አስታውሰዋል። ድርጅቱ በክልሉ በ12 ዞኖች በ94 ወረዳዎች፣ በ38 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ በ517 ጤና ጣቢያዎችና በ2 ሺህ189 ጤና ኬላዎች ነው ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ነው የገለጹት። በአማራ ክልል 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ የድርጅቱ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል።
ድርጅቱ በስድስት ክልሎች ለ57 ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት መስጠቱንም ፕሮግራም መሪው ገልጸዋል። ዶክተር መንግሥቱ እንዳሉት በአምስት ዓመታት ቆይታቸው የጤና ተቋማትን የማሻሻል፣ የመደገፍና የማስተሳሰር ተግባራት ተከናውነዋል።
ድርጅቱ ባደረገው የአምስት ዓመታት ቆይታ በአማራ ክልል የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሥራ ላይ ማዋሉን ጠቁመዋል። ኀላፊው እንዳሉት በተለያየ ወቅት አስቸኳይ የጤና ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል። በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማት ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ 279 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ዶክተር መንግሥቱ ገልጸዋል። ድርጅቱ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ሲደግፍ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) “ትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር በአማራ ክልል የእናቶችንና የሕፃናትን ጤንነት ለመጠበቅ በርካታ ተግባራትን ፈጽሟል” ብለዋል፡፡ የተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ ያሳሰቡት ኀላፊው ክልሉ በርካታ ክፍተቶች ስላሉበት የበለጠ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባልም ነው ያሉት።
ድርጅቱ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙና የተዘረፉ የጤና ተቋማትን መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ዶክተር መልካሙ ገልጸዋል። “ወደ ክልሉ የሚመጡ ሁሉም ፕሮግራሞች የእኛ ነው በማለት አብረን እንሠራለን” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/