
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጥቅሻ የተግባቡት፣ የማይሻር ቃል ኪዳን ያሰሩት፣ እስከ መቃብር ድረስ በአንድነት የቆሙት፣ ቃል ኪዳናቸውን ያከበሩት፣ በክፉውም በመልካሙ ዘመንም የተማመኑት፣ ተማምነው ያመኑበትን መልካም ተግባር የፈጸሙት፣ ዝቅ የሚያደርጋቸውን የረገጡት፣ ከፍ ወደ ሚያደርጋቸው በአንድነት የገሰገሱት፣ ስለ አንድነት ያዜሙት፣ ስለ አንድነት የተቀኙት፣ በአንድነት የኖሩት፣ ለክብር ሲሉ የሞቱት፣ ለፍቅር ሲሉ ከሠንደቅ በፊት የቀደሙት ታሪክ አድንቋቸዋል፣ ብራናው ደመቅ አድርጎ መዝግቧቸዋል፡፡
የሚከፋፍሏቸውን ረግጠዋቸዋል፣ በአንድነታቸው የመጡባቸውን ከእግራቸው ሥር ጥለዋቸዋል፣ በክብራቸው የተነሱባቸውን ክብራቸውን አሳጥተዋቸዋል፣ ወሰናቸውን የረገጡባቸውን አፈር አድርገዋቸዋል፣ ወንዙን የተሻገሩትን በመጡበት አስቀርተዋቸዋል፣ በጎራዴያቸው ቀልተዋቸዋል፣ በጦራቸው ወግተዋቸዋል፡፡ በፍቅር የመጡትን አክብረዋቸዋል፣ ከሚጎርሱት አጉርሰዋቸዋል፣ ከሚጠጡት አጠጥተዋቸዋል፣ ከመኝታቸው ለቀው አስተኝተዋቸዋል፣ ስንቅ አስይዘው፣ ጠባቂ ሰጥተው፣ ወንዙን አሻግረው ሸኝተዋቸዋል፡፡
በጥቅሻ ተግባብተው፣ ቃል ሰጥተው፣ ቃል ተቀብለው፣ ለአንዲት ሠንደቅ፣ ለአንዲት ሀገር የተሰዉት፣ ደም አፍስሰው ጸኑ ሀገር ያስረከቡት፣ እኔ ልቅደም ከሀገር በፊት፣ የሚል ጽኑ አደራ ያስቀመጡት፣ እነዚያ ጠላት የሚፈራቸው፣ ወዳጅ የሚያከብራቸው፣ አብዝቶ የሚወዳቸው ጀግኖች በማይደበዝዝ ቀለም ተቀርጸዋል፡፡ በማይፋቅ ጽኑ ማሕተም ታትመዋል፡፡
በጀግንታሁ ሀገር አጽንታችሁ፣ ከድል ላይ ድል ደራርባችሁ፣ ጠላትን ቀጥታችሁ፣ ምድሯን አስከብራችሁ፣ ስሟን ከፍ አድርጋችሁ፣ ፈተና በበዛበት ዘመን በጽናት ተጉዛችሁ፣ እሾህና አሜካላ በበዛበት ጎዳና በባዶ እግር ተጉዛችሁ፣ ረሃብና ጥሙን ችላችሁ፣ ጠላቶች የሚፈሯት፣ ስሟን ሰምተው የሚደነግጡላት እናት ሀገር አውርሳችኋልና ክብር ይገባችኋል፡፡
አጥንት የተከሰከሰላት፣ ደም የተፈሰሰላት፣ ክቡር ሕይወት የተገበረላት ሠንደቅ የጥቁርን ምድር አጥለቅልቃለች፣ የአሸናፊነት ምልክት ተደርጋ በየአደባባዩ ተውለብልባለች፣ የድል ምልክት፣ የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ ተመዝግብላች፣ ከጥቁሮች ልብ ለዘላለም ላትወጣ ተቀርጻለች፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ አስቀድመው የዘመቱት በድል ተመልሰዋል፣ ከአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ግርጌ የአንድነት ቃል ኪዳን ያሰሩት በቃላቸው ከብረዋል፣ በቃላቸው ተከብረዋል፣ በቃላቸው ጽኑ ሀገር አጽንተዋል፡፡
ሞትን ንቃችሁ፣ ስቃይና መከራን ረስታችሁ፣ ጋሻና ጦራችሁን አስቀድማችሁ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ በልባችሁ ቀርጻችሁ፣ ክብሩን በልባችሁ ጽፋችሁ፣ አንድ ኮዳ ውኃ ለሳምንት እየጠጣችሁ፣ ባልተመቸ ማደሪያ ላይ እያረፋችሁ፣ ዱርና ገደሉን፣ ሜዳና ሸለቆውን እያቆራረጣችሁ፣ ጠላት ያልደፈራት፣ የተጨነቁት እፎይታ የሚያገኙባት፣ ተስፋ ያጡት ተስፋችን የሚሏት፣ መንገድ የጠፋባቸው መንገዳችን ያሏት፣ ስሟን ከፍ አድርገው የሚጠሯት ታላቅ ሀገር አውርሳችኋልና ለክብራችሁ እጅ እንነሳለን፡፡
በየአውደ ውጊያው ስለፈሰሰው ደማችሁ፣ ስለተከሰከሰው አጥንታችሁ፣ ላትመለስ ስለአሸለበችው ሕይወታችሁ፣ ለሀገር ክብር ስትሉ ስለ ተቀበላችሁት መከራችሁና ስቃያችሁ ምስጋና እናቀርብላችኋለን፡፡
ግብራችሁ አሸናፊነት፣ አንድነት፣ ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት የሆነ እናንተ ኃያሎች ክብር ይገባችኋል፡፡ ለጀግንነታችሁ ወደር ያልተገኘለት፣ በወንድነታችሁ እንከን ያልተገኘበት፣ የጦር ስልታችሁን፣ የአስተዳደር ብልሃታችሁን፣ አርቆ አሳቢነታችሁን፣ በምክንያት ተጓዥነታችሁን፣ በመከራ የማይፈታው አንድነታችሁን፣ በጦር የማይበገረው ግርማችሁን ጠላቶች ያደነቁላችሁ፣ እነዚህ ድንቆች ናቸው ብለው የመሰከሩላችሁ ጀግኖች ሆይ ስማችሁን እንጠራለን፣ ሥራዎቻችሁን እንዘክራለን፣ ቃላችሁን እናከብራለን፣ እናንተ ስለሞታችሁላት ኢትዮጵያ ሳናቋርጥ እንዘምራለን፡፡ እናንተ የተቀበላችሁት መከራ እንቀበላለን፣ እናንተ የኖራችሁለትን ክብር እንኖራለን፣ እናንተ ያሰራችሁት የአንድነት ቃል ኪዳን እናጠብቃለን፡፡
በመከራ ሸርተት ያላለው አንድነታችሁ፣ በእሾህና አሜካላ ያልቆመው መንገዳችሁ፣ ረሃብና ጥም ያልበገረው ጽናታችሁ፣ የማይሻረው ቃል ኪዳናችሁ መጽናት ምክንያት ስለሆነችው ቢጫ ወርቋ ኢትዮጵያ ያለንን እንሰጣታለን፣ ስለ ክብሯ እንመሰክራለን፡፡ እነሆ እናንተ ምንም ያልሳሳችሁላት፣ ሁሉንም የሰጣችኋት፣ ከፍ አድርጋችሁ ያስቀመጣችኋት ኢትዮጵያ ዛሬም ችግር ገጥሟታል፡፡ ከጓሮዋ እሸት እየበሉ የሚጠሏት፣ ከወተቷ እየጠጡ የሚነክሷት፣ ወርቅ ስትሰጣቸው ጠጠር የሚመልሱላት፣ ከባሕር ማዶ ጠላቶቿ ጋር እያበሩ ውድቀቷን የሚመኙላት፣ በእለት ጉርሳቸው፣ በዓመት ልብሳቸው የዘላለም ቤታቸውን፣ መመኪያና መከበሪያቸውን የሚክዷት ተበራክተዋል፡፡ ወዳጅ መስለው ገዳይ ሆነዋል፡፡ ሀገር አልባ ክብር ያለ ይመስል በልጆቿ ደም መፋሰስ ነዋይ ማግበስበስ የሚሹት በዝተዋል፤ እንደ አንድ ልብ ምከር፣ እንደ አንድ ቃል ተናገር፤ እንደ አንድ ልብ የመከሩት እንደ አንድ ቃል የተናገሩት፣ በአንድነት ተነስተው፣ በአንድነት የመከቱት፣ ከፋፋዮቻቸውን ጥለው፣ በአንድነታቸው የቀጠሉት ናቸው በባድማቸው የኖሩት፣ የአባታቸውን መሬት ያረሱት፣ የእናታቸውን ሀገር ያለቀቁት፡፡ አንድ የሆኑት ናቸው ያሸነፉት፣ አንድ የሆኑት ናቸው መከራውን በድል የተሻገሩት፣ አንድ የሆኑት ናቸው ጠላቶቻቸውን ያሸነፉት፡፡
ጠላት ዙሪያ ገባውን በመላበት፣ የክፋት እጆች ወደ ኢትዮጵያ ባነጣጠሩበት፣ ለጥል የተዘጋጁ ጠላቶች የኢትዮጵያውያንን መደካም በተጠንቀቅ በሚጠባበቁበት በዚህ ዘመን መከፋፈል ቀድሞ እጅ እንደመስጠት ይቆጠራል፡፡ የአባቶችህ መንፈስ ይኑርህ፣ የአባቶችህ ቃል ኪዳን ይሠርህ፣ የአባቶችህ ጽናት ያጽናህ፣ ያባቶችህ ራዕይ ይኑርህ፣ ከኢትዮጵያዊነት ክብር የሚያወርድህን፣ መለያየት የሚሰብክህን እርሳውና የአባትህን ቃል ኪዳን አንሳ፣ የአባትህን አደራ ተቀበል፡፡
በመለያየት የአባት ባድማ አይታረስም፣ ከአባት ማሳ ምርት አይታፈስም፣ የእናት ሀገር አይወረሰም፣ የእናትህ ሀገር እንዳይናፍቅህ፣ የአባትህ ባድማ እንዳይርቅህ አንድ ሆነህ ታገል፣ ለመከራዎች በቀላሉ አትዛል፡፡
ጠላቶች ቂማቸውን ረስተው በኢትዮጵያ ላይ ለመዝመት ወንዝ ወርደው ይማማላሉ፣ በምድሯ የተፈጠሩት ጥቅመኞች ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ያለ እንቅልፍ ይታትራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚለያዩበት ቀዳዳ ቢገኝ እያሉ ሲቆፍሩ ውለው ሲቆፍሩ ያድራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ከኢትዮጵያዊው የሚጋደልበትን ድንጋይ ያቀብላሉ፣ እሳት አንድደው ከዳር ቆመው መሞቅን ይመኛሉ፣ ንጹሐኑ በእሳቱ ነዲድ ሲቃጠሉ እነሱ በእሳቱ ዙሪያ ድግስ ደግሰው ይበላሉ፡፡
አንድ የሆኑት እንጂ የተከፋፈሉት አሸንፈው አያውቁም፣ የሰከኑት እንጂ የቸኮሉት ድል አላጣጣሙም፣ በምክንያት የሚጓዙት፣ በምክንያት የሚነሱት፣ በብልሃት የሚጓዙት፣ በጽናት የሚራመዱት ድል ከእነርሱ ጋር ናት፡፡ የኢትዮጵያውያንን ታሪክ መለስ ብለህ ተመልከት በአንድነታቸው ነው ደማቅ ታሪክ የጻፉት።
ጠላቶቻቸው ሊከፍሏቸው በተነሱበት ጊዜ አይሆንም ብለው ነው መከራውን ያለፉት፡፡ የተከፋፈለን የመጣው ሁሉ ያዋርደዋል፣ የዘመተው ሁሉ ይረተዋል፣ የዘመተው ሁሉ እንዳይረታህ፣ ጦር የሰበቀው ሁሉ እንዳይጎዳህ መለያየትን ረስተህ በአንድነትህ ጸንተህ ተጓዝ፡፡ ያን ጊዜ ትከበራለህ፣ ጠላቶችህ ከእግር ሥር ትጥላለህ፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/