የእግር ኳስ ቡድኖች የስያሜ ለውጥ እንዲያደርጉ መጠየቁ የሕግ ድጋፍ እንደሌለው የሕግ ባለሙያ ተናገሩ፤ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የጻፈው ደብዳቤ እንደሌለ አመልክቷል፡፡

241

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከሰሞኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተወሰኑ የፕሪሚዬር ሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ስያሜ እንዲቀይሩ ማሳሰቡንና የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ምክትል ፕሬዝዳንትን ዋቢ አድርገን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ስያሜን በተመለከተ የኢትዮጵያ የሕግ ድንጋጌዎችን መሠረት አድርገው ማብራሪያ እንዲሰጡን የሕግ ባለሙያ አነጋግረናል፤ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ሐዲስ ሐረገወይን ናቸው፡፡
አቶ ሐዲስ እንዳብራሩት ታዲያ የንግድ ድርጅቶች ስያሜያቸው ከሌላ ተቋም ጋር አሳሳች መሆን አለመሆን፣ ከመንግሥት አካላትና የልማት ድርጅቶች ተመሳሳይ መሆን አለመሆን፣ የታዋቂ ሰዎችን ወይም የሀገር መሪዎችን ስም የተጠቀመ ከሆነ ፈቃድ ማግኘቱ እና ከሕዝብ ሞራል የሚቃረን መሆን አለመሆኑ ተረጋግጦ ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ፋሲል ከነማ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ይዞት የኖረ ስያሜና ማኅበረሰባዊ ቅቡልነት ያለው፣ የማንንም ሞራል የማይነካ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

የእግር ኳስ ቡድኖች ለትርፍ የተቋቋሙ ወይም የሕዝብ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለከቱት አቶ ሐዲስ ፋሲል ከነማ በሕዝብ የተቋቋመ የሕዝብ ቡድን በመሆኑ ታሪካዊ ስያሜን መያዙን ገልጸዋል፡፡ የፋሲል ከነማ አሰያዬም ከሌሎች ሀገራት ቡድኖች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን በመጥቀስም አቶ ሐዲስ አስረድተዋል፡፡ የስፔኑን ሪያል ማድሪድ በአብነት አንስተውም ‹‹የንጉሣዊ ቡድን›› ማለት እንደሆነና ስያሜው በማንም ላይ ተጽእኖ የማያሳድር ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል፡፡

የእንግሊዙ አርሰናል ስያሜ ከመድፍ ጋር መያያዙን፣ ሴልቲክ በስደተኞች የተቋቋመና ያንኑ ስያሜ ይዞ የቀጠለ መሆኑን በመጥቀስም ፋሲል ከነማንም ሆነ ሌሎችን ቡድኖች ስያሜ እንዲቀይሩ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ሐዲስ አመስገንዝበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከንግድ ተቋማትም ሆነ ከማኅበራት ወይም ከፍትሐብሔር ሕግ አንጻር የማያስኬድ ክልከላ በማድረግ ታሪክን ለማደብዘዝ ያሰበ ያስመስለዋል ›› ነው ያሉት፡፡

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አብመድ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጓል፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ‹‹የጻፍነው ደብዳቤ የለም፤ ምናልባት በጽሕፈት ቤት በኩል ተጽፎ ከሆነ አላውቅም፡፡ በእርግጥ ሐሳቡ አለ፤ ግን ‹የትኞቹ ክለቦች ስያሜ ሊቀይሩ ይችላሉ የትኞቹስ ባሉበት ይቀጥላሉ?› የሚለውን ገና አላሳወቅንም፡፡ ሐሳቡ ግን የፊፋ ሕግ አንቀጽ 4 የሚከለክላቸው ዘር፣ ሃይማኖት መሠል ገላጭ የሆኑ ስያሜዎችን የሚመለከት ነው›› ብለዋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤትም አብመድ ያገኘው መረጃ ‹‹የስም ለውጥን በተመለከተ የሚወስነው ጠቅላላ ጉባኤ እንጂ እኛ አይደለንም፤ ደብዳቤም አልጻፍንም›› የሚል ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል የወጣ መረጃ እንደሌለ ቢገለጽም የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ግን ደብዳቤ እንደደረሰው በመግለጽ የስያሜ ለውጥ እንደማያደርግ አቋሙን አሳውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous article‹‹ኅብረተሰቡንና ለጋሽ ድርጅቶችን በማሳተፍ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡›› የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
Next article“ከትምህርት ቤቱ ሀገር የሚገነቡ ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪዎች እንደሚወጡ ሕልሜ ነው” ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው