ምርትን ለማሳደግ መላ መዋቅሩን አስተባብሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

215

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ ምቹ ጸጋ እንዳላት ይነገራል። ከ50 ሚሊየን እስከ 72 ሚሊዮን ሄክታር ለእርሻ ምቹ የኾነ መሬት እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ። ግን ደግሞ ዛሬም ከበሬና የገበሬ ጉልበት ያልተላቀቀው እርሻችን እንደ ዓለም ባንክ የ2018 (እ.አ.አ) ሪፖርት 14 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ያልበለጠ መሬት በሰብል እየተሸፈነ ነው ከ110 ሚሊየን በላይ ሕዝብን እየመገበ ያለው።

አማራ ክልል የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ የሰብል ምርት እንደሚሸፍን ይገለጻል። በ2014/15 የመኸር እርሻ ወቅት 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን አቅዶ እየሠራ ስለመኾኑም የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳውቋል።
ከዚህም 143 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ነው ያቀደው።
ባለፈው ዓመት ከነበረው በሄክታር አምስት ኩንታል ምርት ጭማሪ ለመግኘትም ታቅዷል ተብሏል።
ባለፈው ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኖ 118 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት እንደተቻለም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ዓለም አቀፍ ጫናዎች ለፈጠሩት የግብዓት እጥረት ክልሉ ምን አስቧል?

ዓለም አቀፍ ጫናው የፈጠረው ችግር በግብርናው ዘርፍ በተለይ ከውጭ ሀገር የሚገቡና እንደ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ያሉ የግብዓት እጥረት ፈጥሯል፡፡ የሀገሪቱና የክልሉ ወቅታዊ ሰላም፣ የኑሮ ውድነቱ ተዳምሮ የግብርናው ዘርፍም ተፈትኗል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ተመራጭ መፍትሔዎችን በመከተል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አስታውቋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደሚሉት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ ግብርና ቢሮ መላ መዋቅሩን አስተባብሮ የሥራ ኀላፊዎችን፣ የባለሙያዎችንና የአርሶ አደሩን አቅም በማቀናጀት የታቀደውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ካለፈው ዓመት የተገኘውን ልምድም በመቀመር ውጤታማ አሠራሮች በመከተል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

ምክትል ኀላፊው በትኩረት የሚተገበሩ የተቀመሩ ውጤታማ አሠራሮች ብለው ካነሷቸው መካከል ጥቁር አፈርን ማጠንፈፍ፣ የክላስተር አሠራርን መዘርጋት፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን ላይ በስፋት መሥራት እና መሰል ዘርፎች ይገኙባቸዋል፡፡ በምርታማነታቸው የተመረጡ ሰብሎችን እንደ ስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ቦቆሎ ያሉትን በስፋት የማምረት የአሠራር ስልት ተነድፎ እየተሠራ ሰለመኾኑም ነው አቶ ቃልኪዳን የተናገሩት።

ምክትል ኀላፊው እንደገለጹት የአማራ ክልል በዘንድሮው ዓመት 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ነበር እቅድ ያስቀመጠው፡፡ እንደ ሀገር በገጠመው እጥረት ምክንያት የተመደበለት ግን 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ብቻ እንደኾነ ታውቋል። ይህም የዋጋ ጭማሪው እንዳለ ኾኖ የሚቀርበው የእቅዱን 59 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።

እንደ ቢሮው መረጃ
•ከታቀደው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል።
•ከዚህም 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሰራጭቷል።
•1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ከአርሶ አደሩ እጅ ገብቷል።

ምክትል ኀላፊው አቶ ቃልኪዳን እንደተናገሩት ከኾነ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱን ለማካካስ አማራጭ መፍትሔዎች ላይ እየተሠራ ነው። አርሶአደሮች በስፋት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መኾኑን አስታውቀዋል።

ምርታማነትን የሚጨምሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት)፣ በሀገር ውስጥ አፈር ምርምር የተዘጋጀ (ቨርሚ ኮምፖስት)፣ (ባዮሳላሪ) የተባለ እና አርሶ አደሩ ራሱ የሚያዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን የገባ (ኢኮ ግሪን) የተባለ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በአማራጭነት እየቀረቡ ነው ተብሏል፡፡ አሲዳማ አፈርን በማከም ረገድም ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል።

(ኤልሴራም) የተባለ ፈሳሽ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ከቱርክ ሀገር ማስገባት መቻሉም ተነግሯል።

በዚህም እስካሁን
•ከ36 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተዘጋጅቷል።
•31 ሺህ 860 ኩንታል (ቨርሚ ኮምፖስት) ተዘጋጅቷል።
•53 ሺህ ሜትር ኪዩብ (ባዮሳላሪ) ተዘጋጅቶ ከማሳ ጋር የማዋሀድ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው የተባለው።

ከዚህም በተጨማሪ በግብዓት እጥረት ምርት እንዳይቀንስ የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በብዛት ጥገኛ ያልኾኑ ሰብሎች ላይ ማተኮር እንደ አማራጭ መወሰዱን ነው አቶ ቃልኪዳን የተናገሩት።

የምርጥ ዘር አቅርቦት ለተያዘው እቅድ ስኬት:–

ለዘንድሮው የምርት ዘመን በክልሉ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዳለ አቶ ቃልኪዳን ተናግረዋል። በቂ ባይኾንም ክልሉ ዘር አምራች መኾኑ፣ አንደ ሀገርም የምርጥ ዘር እጥረት አለመኖሩ በታቀደው ልክ ለማምረት የዘር አቅርቦት ችግር አይኾንም ብለዋል።

የዘር መሬት በመጨመር፣ በዘር አባዥ ድርጅት፣ በአርሶ አደር ደረጃም ተባዝቶ በክልሉ ኳራንታይን ተቋም እንደተረጋገጠው ወደ 248 ሺህ ኩንታል ይሰበሰባል ተብሏል። እስከ አሁን ድረስም ወደ 219 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደተሰበሰበ ተገልጿል።

ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ከኾነ
•የበቆሎ ምርጥ ዘር በተመለከተ 85 ሺህ 222 ኩንታል ቀርቧል።
•እስካሁንም 59 ሽህ 088 ኩንታል ተሠራጭቷል።

በአሸባሪው ትህነግ ወረራ የተጎዱ አካባቢዎች ለሚኖሩ አርሶ አደሮች ምን ታቅዷል?

አቶ ቃልኪዳን እንደገለጹት በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን የሚደግፉ ፕሮጀክቶች ከሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ አርሶ አደሮችን በግብርና ግብዓት አቅርቦትም እንዲያግዙ ተደርጓል።

የብድር ተጠቃሚነትን በማመቻቸት የሚፈልጉትን የግብርና ግብዓት እንዲያሟሉ ኹኔታዎች ተመቻችተዋል ብለዋል።
አርሶ አደሮች የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን እጥረት የሚያካክሱ አማራጮችን በመጠቀም፣ የግብርና ሙያተኞችን ምክረ ሃሳብ በመተግበር፣ ምርታማነትን በማሳደግ ማምረት እንዳለባቸው መክረዋል። እያንዳንዱ አርሶ አደር በግብርና ግብዓት እጥረት የእርሻ ማሳዬ ጦም ሊያድር ነው እያለ ከመስጋት ለአዳዲስ አሠራሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች ቅርብ መኾን ይገባዋል ነው ያሉት አቶ ቃልኪዳን።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበ2013 ዓ.ም ክረምት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 80 በመቶው መጽደቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleዜና መጽሔት ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ)