በ2013 ዓ.ም ክረምት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 80 በመቶው መጽደቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

155

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ አምበራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ደሴ አስማረ በ2013 ዓ.ም ክረምት የተተከሉ ችግኞች አብዛኞቹ መጽደቃቸውን ተናግረዋል። አርሶአደር ደሴ በየዓመቱ በወል መሬት እና በተሠሩ ተፋሰሶች ላይ ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል።

የተተከሉት ችግኞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ማኀበረሰቡ እንክብካቤ እያደረገ እንደኾነም ነው የተናገሩት። በተተከለ ችግኝ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች በቀበሌ ማኀበራዊ ፍርድ ሸንጎ ቅጣት እንደሚወሰንባቸው አንስተዋል። አርሶ አደር ደሴ ማኀበረሰቡ ግንዛቤ አለው፣ ችግኞችን ለራሱ ብሎ እየተንከባከበ ነው ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያብራሩት።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሶሊበን ወረዳ ዶገም ቀበሌ ነዋሪው አርሶአደር ደምል ተሻለ በአካባቢው የተሠሩ ተፋሰሶች ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በመኾናቸው አገግመው ጥቅም መስጠት መጀመራቸውን እና የተተከሉ ችግኞች መጽደቃቸውን ነግረውናል።

አርሶአደር ደምል አንዳሉት ማኀበረሰቡ በየወሩ ገንዘብ እያዋጣ ለሁለት ሰዎች ደመወዝ ይከፍላል። በዚኽም ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል። የፈረንጅ ጽድ፣ ግራቢሊያ፣ ዲከረንስ፣ ባህርዛፍ በብዛት የተተከሉ ችግኞች ናቸው ያሉት አርሶአደር ደምል ሀገርበቀል ችግኞችን ለማጽደቅ ፍላጎት ቢኖርም ችግኞቹ አፈር ስለሚመርጡ መጽደቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምሕረት ከተተከሉ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 80 በመቶው በሚፈለግባቸው የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ አቶ እስመለዓለም እንዳሉት በ2013 ዓ.ም ክረምት ላይ ችግኞች ከተተከለባቸው አካባቢዎች መካከል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግምኽራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች በሽብር ቡድኑ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በዚህ ዓመትም ቀድመው በሚዘጋጁ ችግኞች ላይ እንዳልተሳተፉ እና ከጥር ወር ጀምሮ በተዘጋጁት ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በ2014/15 የክረምት ወቅት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለማፍላት ታቅዶ እስካሁን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ችግኖች በአማራ ክልል በሚገኙ በሁሉም ችግኝ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ችግኞች ውስጥ 216 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞች ሀገር በቀል ሲኾኑ የጽድቀት መጠንን ለመጨመር 252 ሚሊዮን ችግኞች በፕላስቲክ ተፈልተዋል ነው ያሉት፡፡ ለሀገር በቀል ችግኞች ቅድሚያ ሠጥቶ ለመትከል ያመች ዘንድ 47 ሚሊዮን ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ቀሪው ጉድጓድ እስከ ሰኔ 15 ባለው ተዘጋጅቶ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“አርሶ አደሮች ያለውን ግብዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች በትኩረት መሥራት ይገባቸዋል” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleምርትን ለማሳደግ መላ መዋቅሩን አስተባብሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።