
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊ ሰላማዊ እና መደበኛ የልማት ሥራዎች መሥራት የሚችልበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ፋኖ ላይ ያተኮረ እርምጃ እንደማይወሰድም አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ከሰሞኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡ በክልሉ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊ ሰላማዊ እና መደበኛ የልማት ሥራዎች መሥራት የሚችልበት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የተሻለ እፎይታ ያገኘበትና ከጸጥታ ስጋት የወጣበት ነውም ብለዋል፡፡ የጸጥታ ኀይሉ ሕግ የማስከበር አቅሙ እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ከስጋት እየወጣ ለትልልቅ ግቦችና ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ እየተመቻቸ መኾኑንም አመልክተዋል፡፡
መሠረታዊ የኾኑ እንቅፋቶች እየተጠረጉ መኾኑን ያነሱት አቶ ግዛቸው አሁንም ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ የአማራ ክልል ከአንድም ሁለት ጊዜ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ የተቃጣበት የውስጥና የውጭ ኀይሎች አደጋ የደቀኑበት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ጎስቋላ፣ መሪ የሌለው እንዲኾንና አንገቱን እንዲደፋ የሚያደርጉ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም አስታውሰዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን የጅምላ ጭፍጨፋ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ጥፋት አሁንም ጠባሳው አለመልቀቁንም ተናግረዋል፡፡ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሥርዓትን የሚንዱ ሕገወጦች የገቡበት መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል እየተደረገ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ በቂ ምክንያት ያለው፣ ችግሮችን ለመቅረፍና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የሕግ ማስከበሩ እንቅስቃሴ የሽብር ቡድኑንና የውጭ ጠላትን ለመከላከል ለሚደረገው ዝግጅት አንደኛው አካል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ የውስጥ ባንዳዎችን በመግዛት እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ውስጣዊ ሰላም መደፍረስ ለሕግ ማስከበር መነሻ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሕጻናትን ማገት፣ የተደራጀ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ክልሉን እንደፈተኑት ያነሱት አቶ ግዛቸው ይሄን ለማስተካከል ሕግ ማስከበሩ ግድ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ክልሉን አደጋ ውስጥ የሚከቱ እንቅስቃሴዎች መበራከታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተሟላ አቅም ልዩ ኦፕሬሽን በመፍጠር የሕግ ማስከበር ሥራው እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት አጥፊዎችን ለማስተካከል በውይይት፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሚቀርቧቸው ሰዎች ጥረት አድርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ግዛቸው ነገር ግን በዚህ ሁሉ ያልተሳኩ ጉዳዮችን በሕግ አግባብ ማስተካከል ግድ በመኾኑ ሕግ ለማስከበር በተቀናጀ አግባብ መሥራት ግድ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
የመንግሥት ዋነኛው ዓላማ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ እውነታው ሕገወጦችን በሕግ አግባብ መጠየቅና ማረም እንጂ ሌላ ምንም አይነት ዓላማ የለውም ብለዋል፡፡ የሕግ ማስከበሩ ዓላማ ጠንካራ ክልል የመገንባት ሂደትና ሕጋዊ የኾነ የጦር መሳሪያ አያያዝን ለማረጋገጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሕግ ማስከበሩ ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ መንግሥት ለማስተካከል ዝግጁ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ዘራፊና ወንበዴ መታረም አለበት፣ በምንም ተዓምር ፋኖ ላይ ያተኮረ እርምጃ አይወሰድም፣ በፋኖም፣ በልዩ ኀይሉም፣ በፖለቲካ መሪዎችም፣ በሃይማኖት አባቶችም ያጠፋ ይጠየቃል አንድን ወገን ብቻ የሚያጠቃ እንቅስቃሴ የለም ነው ያሉት፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ይሠራል እንጂ አንድን አካል ለይተን ነጥለን አናጠቃም ብለዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች መኾኑን ማሳየት እንጂ የታገለን ፋኖ የማጥቃት ዓላማና ተግባር የለንም ነው ያሉት፡፡
“ሥርዓትና ሕግ የሚያከብሩ፣ የተጋደሉ፣ የተዋጉ ፋኖዎች አሉ፣ በእነዚህ ስም መነገድ አይቻልም፣ ማኅበረሰቡ ለጀግኖች ፋኖዎች የሚሰጠው ክብር ይታወቃል፣ ፋኖነትን ከደሙ ጋር ያዋሀደ ጀግና ሕዝብ ነው፣ እስር ቤት ጥሶ ወንጀለኛን ያስለቀቀ ቡድን ላይ እርምጃ ስትወስድ ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው ይልሃል፣ ይሄ የፋኖ መገለጫ አይደለም፣ ይሄ ትልቁን ክብራችን የማዋረድና የመናቅ ነው” ብለዋል፡፡ ማንኛውም ጥፋት ያጠፋ ይጠየቃል ይሄ ግልጽ መኾን አለበት ብለዋል፡፡ በክልሉ እየተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ትልልቅ ውጤቶች እያመጡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ከኅበረተሰቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች መንግሥት ሥርዓት ያስከብር፣ ዘራፊ በዝቷል፣ መንግሥት መንግሥትነቱን ማረጋገጥ አለበት የሚሉ ጥያቄዎች በትኩረት መነሳታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በጋራ በመኾን አጥፊዎችን እየያዘ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል እየተወሰደ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ሕዝቡ አልደገፈውም የሚባለውም ሀሰት ነው ብለውታል፡፡
ትክክለኛው መረጃ በተገቢው መንገድ ለሕዝብ እንደሚደርስም ገልጸዋል፡፡ ሕግ ጥሰን ሕግ ለማስከበር አንሄድም፣ በሕግ ማስከበር ላይ ክፍተት ካለ እናስተካክላለን፣ ኾነ ብሎ ባልተገባ መንገድ የሚሄድ ካለ እሱም ተጠያቂ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ የአማራን ሕዝብ ወዳልተገባ ብጥብጥ እንዲገባ ለማድረግ የሚጥሩ ኀይሎች አሉ ያሉት አቶ ግዛቸው የአማራ ሕዝብ አስተዋይ በመኾኑ እንዳልተሳካላቸውም ተናግረዋል፡፡
ጠላቶች የአማራን ሕዝብ ዝቅ የማድረግ ዓላማ ይዘው እየሠሩ ስለመኾናቸውም አንስተዋል፡፡ መንግሥት የሃሳብ ነጻነትን አለማፈኑንና እንዲያውም ከገደብ ያለፈ እንቅስቃሴ መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ ሃሳቦች እንደሚንሸራሸሩና የግለሰቦችን ሰብዕና የሚጥሱ ሃሳቦች መበረካታቸውንም አንስተዋል፡፡ ሃሳብን መቃዎም ይቻላል የግለሰቦችን ሰብዕና የሚነኩ ሃሳቦች ግን በሕግ እንደሚያስጠይቁ መታወቅ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ማለት ሰዎችን መሳደብ አይደለም፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨት አይደለም፣ እየተከፈለው የስለላ ሥራ መሥራት አይደለም፣ ይሄን የሚያደርግ የሃሳብ ነጻነት ሳይኾን ሕገ ወጥነት ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የአማራን ሕዝብ ለሚያጠቃ ጠላት የመሳሪያ ዝውውር የሚፈጽሙ አካላት ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡
የአማራን ሕዝብ ለሚያጠቃው የሽብር ቡድን ነዳጅ የሚያደርስ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ ሰላምን በማረጋገጥ የክልሉን ልማት ማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብንም ብለዋል፡፡ ትናንት ጥሩ ሥራ ስለ ሠራሁ ዛሬ ላይ ጥፋት ባጠፋም ተጠያቂ መኾን የለብኝም የሚል አሠራር ሊኖር አይገባምም ነው ያሉት፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ መኾኑን ያነሱት አቶ ግዛቸው በያዛቸው በአማራ ክልል አካባቢዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ሊያጠቃ የሚችለው የአማራ ሕዝብ አንድነት የተሸረሸረ ጊዜ ብቻ ነው፣ አማራ አንድ በኾነ ጊዜ የትኛውም፣ የውጭም የውስጥም ጠላት አማራን ሊደፍረውም ፣ ሊነካውም አይችልም ብለዋል፡፡
የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ አንድነትን ማጠናከር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የክልሉ የጸጥታ ኀይል በሚገባው ልክ መደራጀቱንም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡ ለወራሪ ቡድኑ እንዳይበገር የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ ዳግም ኪሳራ እንዳይገጥመው እየሠራን ነው፣ የመከላከል አቅማችንና ተግባራችን የሚቆም አይደለም፣ የአማራ ሕዝብ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማጠናከር አለበትም ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/