
ጎንደር ፡ ግንቦት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ኢግዚቢሽን “ምርምር ለማኅበረሰብ አገልግሎት፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመልሶ መቋቋምና ዕድገት ” በሚል መሪ ቃል ለ30ኛ ጊዜ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ቢኒያም ጨቅሉ (ዶ.ር) የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ኢግዚቢሽኑ በኮረና ወረርሽኝና በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት የተዳከመውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሣሁን ተገኝ (ዶ.ር) ችግርን መሰረት ያደረገ ምርምር በማድረግና ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ቀጣይነት ባለው መልኩ እየሠራ መኾኑን አሳውቀዋል። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግና ችግርን በመፍታት ዩኒቨርሲቲው ተሸላሚ መኾኑን ያነሱት ዶከተር ካሣሁን የምርምር ሥራን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተባባሪ ተቋማት ጋር በመሥራቱ የተመራማሪዎችና የምርምሮች ቁጥር እየጨመረ መኾኑን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከ11 በላይ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከስነ ልቦናዊ ድጋፍ ጀምሮ እስከ ጥሬ ሀብት እገዛ ማድረጉን አሳውቀዋል።
የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ኢግዚቪሽኑን በማዘጋጀቱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ሀገሪቱ አሁን የገጠማትን ማኅበራዊም ኾነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሀገር ውስጥ ምርምር ለመፍታት ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡ የማህበረሰብ አገልግሎት በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲሰጥ ማድረግ ቀጣይነት ያለውና ታዳጊ የኾነ እድገት በዘርፉ ለማስመዝገብ ጥቅም አለውም ብለዋል። እንደ ሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያድግና ዘርፈ ብዙ ልማት ለማስመዝገብ የተቀናጀ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደሚገባም አሳውቀዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሽብር ሥራው ያደረሳቸውን ሰብዓዊ እና ሀገራዊ ጉዳቶችን በምርምር ለይቶ ለማውጣት የሚደርገው ጥረት የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል። እንደ ሀገር የሥራ አጥነት መጠን 8 ነጥብ 8 በመቶ በአማካይ መኾኑን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ያነሱት አቶ ንጉሱ ምርምሮችና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ሥራ አጥነትን ለማቃለል የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በየዓመቱ ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ውጤታማ እንዲኾንና በልዩ ልዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግር ምክንያት እየተባባሰ የመጣውን ሥራ አጥነት ለማቃለል ፖሊሲ በመቅረጽ እና ስትራቴጂካዊ እቅድ በመንደፍ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል። ምንም እንኳን እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚያደርገው የምርምር ሥራዎች ለዚህ መፍትሔ ሰጭ እንዲኾኑ አድርጎ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ዘጋቢ፡-ፍጹምየዓለምብርሃን ገብሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/