ʺየቀየውን ማሳ ሜዳና ዳገቱን ያርስ እንዳልነበረ፣ ዛሬ ዘመን ገፍቶት አራሹ ተሰዶ ማሳው ጦም አደረ”

249

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ደመናው ሲመጣ ያስፈራል፣ ዝናቡ ሲያጉረመርም፣ ሰማዩ በጥቁር ደመና ተሸፍኖ ሲጨልም፣ ተራራዎች ጉም ሲሸከሙ፣ አስፈሪ የደመና ክምሮች በፍጥነት ሲተሙ ልብ ይሸበራል፣ ያስፈራል፣ ያስደነግጣል፡፡

ሰኔ ሲያገሳ፣ ሐምሌ ሲያጎራ ልጆች ይሰበሰባሉ፣ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፣ የፈራረሱ የከብቶች ማደሪያ ይጠገናሉ፣ የሚያፈስሱ ጎጆዎች በእሳር ክዳን ይጠብቃሉ፣ እናቶች ክረምት የሚታለፍበትን እንጨትና ኩበት ወደ ቤት ያስገባሉ፡፡ ጨውና በርበሬውን ያዘጋጃሉ፡፡

ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ ሞፈሩ ይሰላል፣ እርፉ ይስተካከላል፣ ከርፈዝና ምራኑ፣ ማነቂያና ወገሉ ይሟላል፣ ወስኮው ይበጃጃል፡፡ ዝናብ ሲወርድ ገበሬው ሸምላና ዘገረን፣ ኳሊና ቦረንን፣ ፈንዛና ባለምዋልን፣ ወይኖና ይመርቀንን፣ ሻሚና ጀንበርን እየጠመደ ማሳውን ያርሳል፣ ያለሰልሳል፡፡ ባረሰውና ባለሰለሰው መሬቱ ላይ ከወፍ አዕላፍ አውጥተህ አብላኝ እያለ ዘሩን ይበትናል፡፡

ፈጣሪውን አብዝቶ የሚያምነው ገበሬ በመሬት ላይ ዘር በትኖ ቡቃያ ይጠብቃል፡፡ የሚያምነው ፈጣሪውም ያመነበትን ያደርግለታል፣ ይሰጠዋል፡፡ ጀንበር ስትዘልቅ ጠምዶ፣ ጀንበር እስክትጠልቅ ደረስ ያርሳል፡፡ አባታቸው ሲያርስ ልጆቹ መቆፈሪያ አንስተው ይቆፍራሉ፣ መጥረቢያ አንስተው ማሳውን ያጸዳሉ፡፡ በክረምት ቦዝኖ የሚውል ገበሬ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ ደክሞ አርሶ የተራበን ያጎርሳል፣ ችግር ሲመጣ ደግሞ ነፍጥ አንስቶ ይተኩሳል፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ ሁልጊዜም ዝግጁ ነውና፡፡

ክረምት ሲመጣ ወንዞች ያገኙትን እየጠረጉ በአስፈሪ ድምጽ ሲፈስሱ፣ ዝናባት ምድርን ሲያረሰርሱ ቤት ያላቸው ወደቤት ይሰበሰባሉ፣ ቤት የሌላቸው ፈጣሪ ቤት ይሰጣቸው ዘንድ ይማጸናሉ፡፡ ʺክረመት ባይመጣ ሁሉ ቤት” እያለ የሚተርተው የሀገሬው ሰው ክረምት ሲመጣ ለቤት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በበጋማ ዛፉ ሁሉ መኝታ ይሆናል፡፡ በክረምት ግን ዝናቡ ሲወርድ፣ ጎርፉ ሲመጣ መኝታ አይደለም መቆሚያ ሁሉ ይጠፋል፡፡ በክረመት የጎን ማሳረፊያ የምትሆን ቤት ታስፈልጋለች፡፡

የሀገሬው ሰው የክረምቱ ወራት ሲደርስ አቤቱ ከክረምቱ መብረቅ ሰውረን፣ የክረምቱን ጨለማ አውጥተህ ከመስከረሙ ብራ አድርሰን፣ ዝናቡ አዝሪት የሚበቅልበት፣ ምድር በአረንጓዴ ካባ የምትዋብበት፣ መስኮች በላም ልጆች የሚሞሉበት፣ ላሞች ወተት የሚሰጡበት፣ በጎችና ፍየሎች የሚረቡበት ይሆን ዘንድ እንለምንሃለን ይሉታል፡፡ ክረምት ሲመጣ የመብረቁ ብልጭታ፣ የወንዞቹ ድንፋታ ያስደነግጣልና። መብረቅ ሳይመታቸው፣ የሞላ ጎርፍ ሳይጠልፋቸው ይኖሩ ዘንድ ይሻሉና ፈጣሪያቸውን አጥብቀው ይማጸናሉ፡፡

ክረምት ሲገባ እረኞች የዝናብ መጠለያቸውን ይዘው ከከብቶቻቸው ጋር ይወጣሉ፣ የደጋዎቹ ግጦሽ ወደ ሚገኝበት ወደ ቆላው ይወርዳሉ፣ ዋሽንቶቻቸውን እያስተካሉ፣ ከጎራ ጎራ ላይ ኾነው እንካ ስላንትያ እየተቀባበሉ፣ በዋሽንቶቻቸው ልብን የሚሰርቅ ዜማ እያዜሙ፣ ግጥም እየደረደሩ ይውላሉ፡፡ ለወትሮው እረኛ ትንቢት ተናጋሪ፣ የመጪውን ዘመን መታሪ ነውና እረኞች የሚገጥሙት ግጥም፣ የሚያዜሙት ዜማ፣ የሚያሰሙት ድምጽ ይጠበቅ ነበር፡፡ አሁን ያ ባይኖርም እነርሱ ግን ማዜማቸውን፣ በጋራ መውጣታቸውን፣ በአንድነት መጫወታቸውን፣ በዋሽንት መመሰጣቸውን አላቆሙም፡፡ ይህ የማይቀር የትውልድ ዥረት ነውና፡፡
ዝናብ ሲመጣ፣ ክረምቱ ሲገባ እንኳንስ የሰው ልጅ የወፍ ልጅ ክረምቱን የምታሳልፍበት፣ በዛፍ ጫፍ ላይ ጎጆ ትቀልሳለች፣ በዋሻ ውስጥ ቤት ታዘጋጃለች፣ ለክረምት መውጫ የሚሆናትን ምግብ አስቀድማ ትሰበስባለች፣ ልጆቿ እንዳይሞቱባት በሰራችው ጎጆ አስቀምጣ እርሷ ምግብ ፍለጋ ትኳትናለች፣ በአፏ የያዘቻትን ምግብ በአፋቸው ታጎርሳለች፣ ዳግም ምግብ ልታመጣ ትበርራለች፣ በአፏ እየያዘች በአፋቸው ታጎርሳለች፣ ጀንበር ስትጠልቅ፣ ጨለማ ካባውን በምድር ላይ ሲዘረጋ ደግሞ ልጆቿን በክንፎቿ አስጠልላ ትጠብቃቸዋለች፡፡ የእናትነት ፍቅሯን፣ የእናትነት ሙቀቷን፣ የእናትነት እዝነቷን፣ የእናትነት አለኝታነቷን ታሳያቸዋለች፣ ትገልጽላቸዋለች፡፡

በክረምት የሀገሬው ገበሬ ከማሳው አይርቅም፣ ከማሳው ሲወጣ ከከብቶቹ፣ ከከብቶቹ ሲለይ ከልጆቹ ጋር ነው፡፡ የቸገረ ነገር ካልገጠመው በስተቀር ቀየውን ለቆ በክረምት አይሄድም፡፡ የዘመድ መጠያየቁም ይቀንሳል፡፡ ለምን ካሉ ጊዜ የላቸውምና፣ አንድ ሰኔ ያለፈውን ሰባት ሰኔ አይመልሰውም ይላሉና የክረምቱ ወቅት እንዲያልፋቸው ፈጽመው አይፈልጉም፡፡
በክረመት ቀያቸውን ለቅቀው የማይሄዱት፣ ከማሳቸው ላይ ዓይናቸውን የማይነቅሉት፣ ጥረው ግረው ሀገር የሚመግቡት ደጋግ ገበሬዎች ዛሬ ላይ ከቀያቸው ርቀው፣ ባድማቸውን ናፍቀው እየኖሩ ነው፡፡ በክረምት የመሸበት እንግዳ አሳርፈው፣ ከአልጋ ወርደው አስተኝተው፣ እግር አጥበው፣ ጠላ አጠጥተው፣ ጤፍ እንጀራ በእርጎ አብልተው የሚያሳድሩት ደጋጎቹ ዛሬ ላይ እነርሱም ቤታቸውን እየናፈቁ በሀዘን መቀመጥ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ወጀብ ሲመጣ የሚጠጉበት፣ ዝናብ ሲዘንብ የሚጠለሉበት፣ ከላሞቻቸው ወተት፣ በበሬዎቻቸው ከታረሰው ከጓሮው እሸት እየተመገቡ፣ ከልጆቻቸው ጋር ዓለም የሚያዩት፣ የላም ልጆቻቸውን በቀየው የሚያሰማሩት እኒያ መልካም ሰዎች ቤታቸው ፈርሶ፣ ሀብታቸው ተወርሶ ከቀያቸው ርቀዋል፡፡ በናፍቆት ተጎድተዋል፡፡

ለወትሮው በዚህ ወቅት ማሳቸውን የሚያለሰልሱት፣ በትጋት የሚያርሱት እኒያ ገበሬዎች ዛሬ ግን ማሳቸውን አያርሱም፣ በቤታቸውም አያጌጡም፡፡ በክፉዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ ቀያቸው እየናፈቃቸው ይኖራሉ እንጂ፡፡ በደል ሳይገኝባቸው በክፉዎች በደል ደርሶባቸው አርሰው ማሳቸውን በዘር በሚሸፍኑበት በዚህ ወቅት በተፈናቃዮች መጠለያ እንዲኖሩ ተፈረደባቸው፡፡

ለልጆቻቸው ወተትና እንጎቻ የሚያቀርቡት፣ በልተው የጠገቡ የማይመስላቸው፣ እንግዳ መቀበል የማይሰለቻቸው ደጋጎቹ ሰዎች ዛሬ ግን ለልጆቻቸውም ምግብ ከሰው እጅ ጠበቁ፡፡ ወተት የለመዱት፣ በእንጎቻ ያደጉት ልጆች ዛሬ ላይ ወተት ቢሉ ወተት የሚያጠጣቸው፣ እንጎቻ ቢሉ ትኩስ እንጎቻ የሚሰጣቸው የለም፡፡ ዛሬ እንጎቻው ከሚነጎትበት፣ ወተቱ ከሚታለብበት ርቀው ሄደዋልና፡፡ ላሞቹ በክፉዎች ተወስደው ግሬራው ጦሙን ውሎ አድሯል፣ ጎተራው ተገልብጦ ምጣዱ ተሰብሯል፡፡

በዋሽንታቸው ጥዑመ ዜማ እያዜሙ ከከብቶቻቸው ስር ስር የሚከተሉት፣ በአንድ ላይ ተቀምጠው በፍቅር የሚጨዋወቱት፣ ወተት በአንድ መጠጫ የሚጠጡት፣ እንጀራ በእንድ ላይ የሚመገቡት እረኞች ዛሬ ላይ ከብቶቻቸው ተወስደው እነርሱ ከአካባቢው ርቀው በቁዘማ ይኖራሉ፡፡ የሰው እጅ ሲያዩ ይውላሉ፡፡ በቀያቸው ያሳለፉት መልካሙ ነገር ሁሉ ትዝ እያላቸው በትዝታ ጎዳና ይባክናሉ፡፡ ከትዝታው መንገድ መቼ እንደሚደርሱ ማን ያውቃል፡፡ የቀየው ስስት ይዟቸው በትካዜ ይባክናሉ እንጂ፡፡

ʺየቀየውን ማሳ ሜዳና ዳገቱን ያርስ እንዳልነበረ፣
ዛሬ ዘመን ገፍቶት አራሹ ተሰዶ ማሳው ጦም አደረ” ሜዳና ዳገቱን፣ ቆላና ደጋውን የሚርሰው አራሹ ገበሬ ከቀየው ተሰዶ ማሳው ጦም አድሯል፡፡ የፈል አፈር የሚናፍቀው፣ ከክረምት ቡቃያ ተስፋን የሚጠብቀው፣ ከቡቃያው አበባና ፍሬን የሚያልመው ደጉ ገበሬ ቀየው በጠላት ተይዞበት በመጠለያ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ እሸት የሚያበቅለው ጓሮ አልታረሰም፣ ማሳው ማረሻ ሳይዞርበት ዝም ብሎ ሊቀር ነው፡፡ ወይም የጠላት ዘመዶች መጥተው ያርሱታል፣ ባለ እርስቶቹ በረሃብ ይኖራሉ፡፡
በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዛሬም በመጠለያ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ከክልሉ ተጠርጎ እስካልወጣ ድረስ ነዋሪዎቹን ወደ ቀያቸው መመለስ እንደማይቻልም የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ደሴ ነግረውኛል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው የመጡ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ኮሚቴ ተቋቁሙ መረጃ የማጥራት ሥራ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ ዜጎች በቆቦ፣ በዋግና በሰሜን ጎንደር በመጠለያ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በክልሉ ውስጥ የሚኖሩም አሉ፡፡

በመጠለያ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች የፌደራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚያቀርብ የተናገሩት ድጋፉ የመዘገየትና ሙሉ ያለመሆን ችግር እንዳለበትም ነግረውኛል፡፡ ድጋፉ በወቅቱ እንዲደርስና ሙሉ እንዲሆን እየተነጋገሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ያለው የዜጎች መጠለያም ከሚፈለገውና ከደረጃ በታች ነውም ተብሏል፡፡ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች በመሆናቸው ወደ ቀያቸው ካልተመለሱ በሚቀጥለው አመትም ተረጅ ኾነው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡ በሽብር ቡድኑ የተያዙ አካባቢዎች ካልተለቀቁ ወደ ቀያቸው መመለስ አይቻልም፣ ባሉበት ግን የሚገባውን ማድረግ ግድ ይላል ብለዋል፡፡
አራሹ በክረምት ሊቀመጥ ነው፣ እሸትና አበባ ሊናፍቀው ነው፡፡ ወተትና ማር ሊጠማው ነው፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየጠላት ኢላማዎችን በአስተማማኝ ኹኔታ ለማውደም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መኾኑን ምዕራብ ዕዝ አስታወቀ።
Next articleየቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለልና ለመልሶ ግንባታ በሚጠቅም መልኩ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ።