“በሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

270

ግንቦት 14/ 2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ “በሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም” ብሏል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ትክክለኛ ማንነቱን የዓለም ሕዘብ እየተመለከተው መምጣቱንና በሐሰት ፕሮፖጋንዳ አሰልፎት የነበረው ድጋፍም መቀዛቀዙን ተከትሎ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ልብ እገዛበታለሁ ያለውን የምርኮኞችን መፈታት አጀንዳ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

የወራሪነት፣ የአጥፊነትና የሀገር አፍራሽ ትክክለኛ ገጽታውን ለመሸፈንና ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው መፍጨርጨር አንዱ መገለጫ ይህ ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሐሰት ትርክቱ ነው። የሽብር ቡድኑ የዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር ከዚህም በፊት የሐሰት መረጃዎችን በማቀነባበርና ተባባሪ ኀይሎችን እያሰለፈ የሴራው አካል ሲያደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የሕወሓት የሽብር ቡድን የአማራና አፋር አካባቢዎቸን በኀይል ወረራ ሥር አደርጎ በቆየባቸው ወቅቶች በግዳጅ ይዞ ኢሰብዓዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ ሰዎችንና ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የሀገር ውስጥም ኾነ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው።
መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሠራዊቱ ቤተሰብ አባላት መኾናቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሥራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ኀይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል።

የሕወሓት ሽብር ቡድን ከሰሞኑ የጦርነት ክተት እያወጀና በይፋም እየተዘጋጀ መኾኑን ማስታወቁን ተከትሎ ያለችውን እንጥፍጣፊ ስንቅ ወደ ጦርነት ለማዞርና ለዳግም ጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ለመኾኑ የአሁኑ ድርጊቱ ኹነኛ ማሳያ ነው።

የዚህ እኩይ ሽብር ቡድን ተባባሪ የኾኑና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔና ሌሎችም ታጣቂ ጽንፈኛ ቡድኖች የዚህ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪዎች ናቸው።
የሕወሓት የሽብር ቡድን ከእነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች አባላትን በመመልመልና በማሰባሰብ ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ ኀይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ የእኩይ ተልዕኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን በመንግሥት በኩል የተደረገው ማጣራት አመልክቷል።

መላው ሕዝብም ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ የሚነዙትን ሐሰተኛ ወሬዎች ዓላማና የሕወሓትን የአጥፊነት ተልዕኮ በማስታወስ አሁንም የሚያሰራጫቸው ወሬዎች የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው መኸሸኑን ሊገነዘብ ይገባል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየተቋማትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ሥርዓት የሚያዘምነው የኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የሞጁላር ማዕከል።
Next articleፋሲል ከነማን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ዛሬ ለ11ኛ ጊዜ የሚያገናኘው የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ ይጠበቃል።