
ግንቦት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ አፍሪካ አብዛኞቹን የዓለማችን ኀያላን ሀገራትን ቀልብ ከመሳብም አልፎ በአካባቢው ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉም ይስተዋላሉ፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ የዓለማችን ከፍተኛው የንግድ መተላለፊያ መስመር ያለበት በመኾኑ ይህንኑ አካባቢ ለመቆጣጠር ሀገራት የቻሉትን ኹሉ ከማድረግ አይቆጠቡም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዋና ማእከል የኾነችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ዩጋንዳ የዚሁ ቀጣና ዋነኞቹ ሀገራት ናቸው፡፡
አካባቢውን ለማሳደግ ታዲያ እነዚህን ሀገራት ማሰተሳሰር የግድ ይላል፡፡ እነዚህን ሀገራት ከዲፕሎማሲው ባሻገር ሊተባበሩበት የሚችሉበት ቀጣናዊ ትስስር መፍጠር አካባቢውን ለማበልጸግም ይሁን የእያንዳንዱን ሀገራት ሰላም ለማስጠበቅ ወሳኝ መንገድ ነው፡፡
ከ300 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚያካልለው ይህ ቀጠና በባሕል፣ በሕዝብ ትስስር፣በማንነት በታሪካዊ ዳራ በኢኮኖሚም ይሁን በአኗኗር ዘይቤ ሀየተሳሰረ ነው፡፡
የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን እንደሚሉት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አቀማመጡ ወሳኝ በመኾኑ ስጋትንም ኾነ ሰፊ እድሎችን የያዘ ነው፡፡ ከፍተኛ የኾነ የዓለም የንግድ መርከቦች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ በመኾኑም ቀጣናውን ወሳኝ ያደርገዋል፡፡
የዓለማችን የምሥራቁ እና የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ መስመር የሚተላለፍበት በመኾኑ ሀገራት ቀጣናውን በቀላሉ የሚመለከቱትም አይደለም፡፡ የኀያላኑ ሀገራት የአፍሪካ ቀንድ የአየር ክልል መተላለፊያ ዋና መስመር መኾኑ በኀያላኑ ሀገራት በትኩረት እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ እነዚሁ ሀገራት በአካባቢው ሰላም ላይም ከፍተኛ የኾነ ፍላጎትም አላቸው፡፡
ኀያላኑ ሀገራት ለአካባቢው በሚሰጡት ከፍተኛ የኾነ ትኩረት ምክንያት በሀገራቱ መካከል የጥቅም ግጭት የሚመስል ጉዳይም አልፎ አልፎ መስተዋሉ አልቀረም፡፡
በዋናነት ግን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እንዲኾን ኀያላኑ ሀገራት የሚፈልጉትን ያህል ቀጣናውን ለመረበሽ እና አካባቢውን በማተራመስ ግዙፉን የዓለማችን የኢኮኖሚ መተላለፊያ ኮሪደር ለማወክ የሚያስቡ አሸባሪ ኀይሎች ዋና የትኩረት አቅጣጫም በመኾኑ ስጋት ያለበት ቀጣናም ነው፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻወል የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወሳኝ የዓለማችን ቀጣና ቢኾንም አካባቢው ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በችግር ውስጥ እያለፈ ያለ ስለመኾኑም ያስገነዝባሉ፡፡ አካባቢው በሽግግር ጊዜ ውስጥ ያለ በመኾኑ እየተጎዳ ያለም ነው ባይ ናቸው፡፡ አምባሳደር ፍስሃ፥ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሀገራት አብዛኞቹ በሽግግር ውስጥ ላይ በመኾናቸው ከፍተኛ እድሎችም ስጋቶችም የሚታዩባቸው ናቸው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያን በአስረጅነት ያነሱት አምባሳደር ፍስሃ ሀገሪቱ ከዚህ አኳያ ስጋቶችም እድሎችም እንደሚታዩባት አስረድተዋል፡፡
ከዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ተለዋዋጭነት ሁኔታ አኳያ የሀገራቱ ፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ሁኔታም ተለዋዋጭ ከመኾን ባለፈ ፖሊሲ እና ስትራቴጅዎች መዘመን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢው ወሳኝ ሀገር በመኾኗ ሀገራት ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ ይስተዋላሉ፡፡ ቀጣናው ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ የመጀመሪያውን ልዩ መልክተኛ የላከው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሲኾን በኋላ ላይ በተከታታይ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በቅርቡ ደግሞ ቻይና ለቀጣናው ልዩ መልዕክተኛ ሹመዋል፡፡
ለዚህ ዋናው ምክንያት አካባቢው ካለው የጅኦ ፖለቲካል ጥቅም አኳያ በማየት ነው፡፡ ሌላው ምክንያት የአካባቢው ወሳኝ ለኾነችው ኢትዮጵያ ከሚሰጡት ትኩረት አኳያ የሚመነጭ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የሚከሰተው አለመረጋጋት ወደሌሎችም የአካባቢው ሀገራት በቀላሉ ሚዛመት እንደኾነ በመረዳት ሀገራት ለሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀይ ባሕር ፖለቲካን ለመቆጣጠር ካለ ፍላጎት በመነጨ ሀገራት በአካባቢው የራሳቸውን የጦር ካምፕ ለመመስረት ፉክክር ሲያደርጉ ይስተዋላል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላም እጦት ወደ ሌሎችም ተስፋፍቶ የኀያላኑን ሀገራት ጥቅም ይጎዳል በሚል ጉዳዩን በቀላሉ እንዳያዩት አድርጓል፡፡
ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር በዓባይ ተፋሰስ የምትጋራው የኢኮኖሚ መሠረት ያለ በመኾኑ ይህን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ልናጣ እንችላለን በሚል ባልተጨበጠ ትንታኔ ውስጥ ገብተው ሀገሪቱ ደካማ ኹና እንድትቀጥል ሰፊ ጥረት ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡ ለዚህም የሀገር ውስጥ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ሲሠሩ ቆይተዋል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ቀጣና ተረድተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል የሚሉት የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር እሸቴ ዜጎች ለሀገራቸው ሰላም እና መረጋጋት ትኩረት ሰጥተው በመንቀሳቀስ እና በአጣብቂኝ ውስጥ ካለው የቀጣናው እድል ላይ ተጠቅመው ተስፈንጥረው በመውጣት ታላቅ የነበረችውን ሀገር ወደ ነበረችበት ማማ እንድትመለስ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ወሳኝነት አኳያ ብቻዋን ልትወጣ የምትችልበት እድል የለም የሚሉት አምባሳደሩ ሀገራቱን በማስተባበር ለአካባቢው እድገት ተባብሮ መሥራትን በሰፊው መሥራት አለባት፤ ለዚህ ደግሞ ከ500 ያላነሱ ዲፕሎማቶች ሥራ ብቻ ሳይኾን የሀገሩን እድገት የሚፈልግ የኹሉም ዜጋ ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/