“ቅንጡ ተሽከርካሪ ያላቸው ባለሃብቶች ሳይቀሩ የድጎማ ነዳጅ የሚሞሉበት የአሠራር ሥርዓት መለወጥ ይኖርበታል” ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን

218

ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኹኔታዎች ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚኽ ወቅት እየፈተኗት ነው፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክፉኛ የተመታው የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በሽብርተኛው ትህነግ ተደጋጋሚ ትንኮሳ እና ወረራ ምርትና ምርታማነቱን ከመጉዳቱ በሻገር ምጣኔ ሃብታዊ ሳንካውም ተገማች ነበር፡፡

አሸባሪው ትህነግ በተደጋጋሚ የሚፈጥረው የጦርነት ትንኮሳ የንግድ እንቅስቃሴውን ገድቦታል፤ ገበያውን አውኮታል ተብሎም ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሀገሪቱ የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በተለይም የአፈር ማዳበሪያ እና ነዳጅ ላይ የፈጠሩት ቀውስ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በየወሩ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ከሚደጎመው ነዳጅም 85 በመቶ ተጠቃሚ የሚኾኑት ባለሃብቶች፣ የውጭ ኢንቨስተሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና ድርጅቶች ናቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ በተያዘው በጀት ዓመት እስከ መጋቢት ብቻ ለነዳጅ የወጣው ድጎማ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ነው።

በነዳጅ ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ገበያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ ኢትዮጵያ በየወሩ በአማካይ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ የምትደጉመው ነዳጅ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርገው ድሃውን እና መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ሳይኾን ባለሃብቱን ነው ይላሉ፡፡ ከግብር ከፋዩ ሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ተደጉሞ በሚገዛው ነዳጅ የሌሎች ሀገራት ባለሃብቶች ሳይቀር ተጠቃሚዎች ናቸው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡ “ቅንጡ ተሽከርካሪ ያላቸው ባለሃብቶች ሳይቀሩ የድጎማ ነዳጅ የሚሞሉበት የአሠራር ሥርዓት መለወጥ ይኖርበታል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ወደብ ላይ የሚቀረው፣ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚላከው እና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የሚባክነው ነዳጅ በሊትር እስከ 37 ብር በመንግሥት ይደጎማል ነው ያሉት፡፡

አቶ ለሜሳ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉት ሀገራት መካከል ነዳጅ በመንግሥት እየተደጎመ በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጥባት ሀገር ናት፡፡ ይኽም ከፍተኛ የኾነ ሕገ ወጥ የነዳጅ ንግድ እንዲኖር አድርጓል፡፡ መንግሥት እያደረገው ያለው የጥቅል ድጎማ ሥርዓት በሀገር ላይ ጫና በመፍጠሩ ከመጭው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ይደረጋል ተብሏል፡፡
አቶ ለሜሳ እንዳብራሩት ማሻሻያው የሚመለከታቸው ተሽከርካሪዎች እና የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች ይለያሉ፤ መንግሥት ለነዳጅ የሚያደርገውን የድጎማ ሥርዓት በአንዴ የሚነሳ ሳይኾን በየአራት ወሩ የ25 በመቶ ማሻሻያ እየተደረገ በአንድ ዓመት ውስጥ ድጎማው ሙሉ በሙሉ ይነሳል፡፡

እንደ አቶ ለሜሳ ገለጻ ድጎማው የሚቀጥልባቸው ዘርፎች አሉ፤ በተለይም የከተማ ታክሲዎች፣ ለመስኖ፣ ለወፍጮ እና መሰል አገልግሎት ነዳጅ የሚጠቀሙና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የትራንስፖርቱ አገልግሎት ዘርፍ የድጎማው ተጠቃሚዎች ይኾናሉ፡፡ ነዳጅ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት ሰበብ የሚኾንበት እድል ሰፊ እንደኾነ ያነሱት አቶ ለሜሳ የነዳጅ ድጎማ ወጭ ጫና በመንግሥት ጫንቃ ላይ የቆየ ነበር ብለዋል፡፡

በዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ መምሕር፣ ተመራማሪ እና አማካሪ የኾኑት ዘካሪያስ ሚኖታ (ዶ.ር) የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እና እጥረት በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚፈጥረው ውስንነት ዘርፈ ብዙ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ችግሩ በውጭ ንግድ ገበያ ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ንግድ ላይም ያለው ተፅዕኖ ከባድ እንደኾነ እየታየ ነው ይላሉ፡፡

ዶክተር ዘካሪያስ እንዳብራሩት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በምዕራባዊያን ሀገራት ላይ የነዳጅ ዋጋ 40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖው እስካሁን ተከስቷል ባይባል እንኳን በቀጣይ ችግሮቹ ሰፊ ሊኾኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ የጥቅል ድጎማን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ቅቡል ቢኾንም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግን ጥልቅ ዕይታ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡

የምጣኔ ሃብት ምሑሩ የድጎማው መነሳት በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ መንግሥት በስፋት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በጤና ተቋማት በኩል የሕክምና ወጪን በስፋት መደጎምም ያስፈልጋል። የምጣኔ ሃብት አማካሪው የነዳጅ ኮንትሮባንድ ሀገሪቱን በዓመት 400 ሚሊየን ብር ገደማ እንደሚያሳጣት ጠቁመው ድጎማው ለሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ክፍተት እንዳይፈጥር ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo Ebla 30/2014
Next articleመተባበር አማራጭ የሌለው ምርጫ