“የአማራ ክልል መንግሥት ሕግ የማስከበር ሙሉ አቅም አለው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

1159

ባሕር ዳር: ግንቦት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የአማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ወያኔና የወያኔ ፈረሶች ናቸው ብለዋል። በግንባር አካባቢ የወያኔ ፈረስ ኾነው የሚያገለግሉትን ኃይል አዘጋጅተን እየተፋለምን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በዝርዝር አጥንቶ ክልሉን ለማዳከም የሚሠሩ ጠላቶች መኖራቸውን አረጋግጧል ብለዋል። የውስጥ ጠላቶችን ለመዋጋት የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ነው ያሉት። የኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ እየወደቀ መኾኑንም ተናግረዋል። ውስጡን እያዳከመና እየከፋፈለ የሚገኝ ኃይል እንዳለም አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ሕገወጥ ተኩስ በአጭር ካልተቀጨ በስተቀር ለኅብረተሰቡ ስጋት ይኾናልም ነው ያሉት። የልማት እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዳይከናወኑ እየተደረገ መኾኑን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድም ፈታኝ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል። አንዳንዱ ሕገ ወጥ ንግድ በጦር መሳሪያ ጭምር እየታገዘ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በታጠቁ ኃይሎች ምክንያት የመንግሥት አቅጣጫዎች እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።

ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ እርስ በርስ በማጋደል ክልሉ የፀጥታ ስጋት ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መገኘታቸውን አመላክተዋል። ይህም ለውጭ ጠላት ተገላጭ እንዲኾን እያደረገ መኾኑንም መገምገማቸውንም ጠቁመዋል።

በየደረጃው ያለ አመራር እየተሳተፈበት የሕግ ማስከበር ሥራው እየተከናወነ መኾኑንም አስታውቀዋል። እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ጅማሮው አበረታች መኾኑንም አንስተዋል።

ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን በማስለቀቅ እና ሕጋዊ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የሕግ ማስከበር ሥራው አስፈላጊና ስኬታማ እንደሚኾን ተናግረዋል።

ሕግ የማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል። የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እንሠራለን ነው ያሉት።

እርስ በርሱ የተከፋፈለ ሕዝብ ለጠላት ተጋላጭ መኾኑንም አንስተዋል። ሕግ የማስከበሩ ሥራ የመንግሥትን ኃላፊነት የሚያረጋግጥ እና ሕዝብን የመታደግ መኾኑንም አስታውቀዋል። ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በመኾን ለሕግ ማስከበሩ ሥራ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ተጠርጣሪዎችን እየያዙና በውይይት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።ያለ አግባብ የተያዙ ሰዎች ካሉ አጣሪ ኮሚቴው እያጣራ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣልም ነው ያሉት። ጥፋተኞች ግን በሕግ አግባብ ሊቀጡ ይገባል ነው ያሉት። ከክልሉ ውጭ ተይዘው ጠፉ የሚባሉት ትክክል አይደለም መስተካከል አለበትም ብለዋል። የተፈጠረ ስህተት ካለም መታረም አለበት ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት ሕግ ለማስከበርና ሙሉ አቅም አለው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ሕገወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን የመቆጣጠር አቅም አለው ነው ያሉት። እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ ኅብረተሰቡ ከአሉባልታ ተቆጥቦ በጥንቃቄ እንዲመረምረውም አሳስበዋል።

የጦር ነጋሪት እየጎሰመ ያለውን ጠላት በመከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ኃይል፣ በሚሊሻና በፋኖ ሕዝባችን ደጀን አድርገን እንመክታለን ነው ያሉት።

ሕዝቡ እንዲከፋፈል ዘመቻ እንደተከፈተበትም ተናግረዋል። ሕዝቡ ተከፋፍሎ እንዲዳከም እየተደረገ ነው፤ ሕዝቡ ይሄን መገንዘብ አለበት ነው ያሉት።

መንግሥት እያደረገ ያለው ሕገወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን መቆጣጠር እንጂ ሌላ ዓላማ የለውምም ብለዋል። ሕገ ወጦች ተጠያቂ መኾን አለባቸው፤ ያላጠፋ ነጻ ይኾናልም ነው ያሉት። “በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው” ብለዋል።

“የአማራ ክልል መንግሥት የጦር መሳሪያ አያስፈታም፤ የክልሉ መንግሥት ፋኖን የሚያዋክብ አይደለም፣ ፋኖዎችን አመሰግነናል፣ ሸልመናል፣ ነገር ግን በፋኖ ስም የሚነግዱ አሉ፤ በነጻነት እና የአማራ የክብር ስም በኾነው ፋኖ እየተንጠላጠሉ ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም የሚፈልጉ አሉ፤ ሕግ ስናስከብር ፋኖ ነው የሚባለው ውሸት ነው፣ እኛ ሕገወጦችን እንጂ ፋኖዎችን የመንካት ዓላማ የለንምም” ነው ያሉት። ዓላማችን የዜጎችን ሰላምና አንድነት ጠብቀን የጋራ ጠላታችን በጋራ መጠበቅ ነው ብለዋል።

የመንግሥትን ሥራ የሚገዳደር ኃይል ሊኖር አይችልምም ብለዋል። ሕዝቡ ከፀጥታ መዋቅር ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል። ሰላምና ደኅንነታችን በራሳችን እንገባ፣ ይህን የማድረግ አቅም አለንም ብለዋል። ማርኮ የያዘ ሰው መሣሪያውን አይነጠቅም፣ ነገር ግን ማስመዝገብ አለበትም ብለዋል።

መሳሪያውን ለችግር ጊዜ እንዲጠቀምበት የሚያደርግ ስልጠና እንሰጣለን ፣ መሳሪያ ያላቸው እንዲያስመዝግቡ ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።

በተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጥሩ ለውጥ መገኘቱን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ በቅርቡ ከተኩስ ድምፅ ነጻ የኾኑ ከተሞችን እንፈጥራለንም ብለዋል። ከሕግ ማስከበሩ በተቃራኒ የቆሙት ኹሉ ለአማራ ሕዝብ የማያስቡ መዃናቸውንም አንስተዋል።

ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ የኾነ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት መሥራት እንደሚገባውም አንስተዋል። የተያዙ ግለሰቦችን በአግባቡ እንይዛለንም ብለዋል። ኅብረተሰቡ ሕገወጦችን እያወጣ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላምን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ እንሠራለን፣ ከአቅም በላይ ሲኾን እርምጃ እንወስዳለንም ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበኲር ጋዜጣ ግንቦት 8/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleሰዓተ ዜና ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2014 ዓ.ም (አሚኮ)