በጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ በተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተፈጸመ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሰት እንደሆነ ተገለጸ፡፡

500

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ ‹ቡሆና› በተባለው አካባቢ በተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የሚል መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሠራጨ ነው፡፡ አብመድ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ግን ‹‹ከመተማ ወደ ጎንደር ሲጓዝ የነበረ ሚኒባስ ቡሆና አካባቢ በከባድ መሳሪያ ተመትቷል›› በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን ከአካባቢው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳኘው በለጠ ባለሙያዎችን ቦታው ድረስ በመላክ አረጋግጠናል በማለት ለአብመድ እንደገለጹት በአካባቢው መስከረም 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከተከሰተው ጥቃት ውጭ የተፈጸመ ሕገ ወጥ ድርጊት (ጥቃት) የለም፡፡

‹‹በአካባቢው አሁን አንጻራዊ ሠላም አለ፤ ጥምር የፀጥታ ኃይሉም ተቀናጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ የትናንቱ መግለጫ ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል›› ብለዋል አቶ ዳኘው፡፡ ትናንት ምሽት በተሰጠው መግለጫ ልክ የፀጥታ ኃይሉ አካባቢውን አስተማማኝ ሠላም የሠፈነበት ለማድረግ እንዲሰራ ነዋሪዎች እያሳሰቡ መሆኑንም ነው አቶ ዳኘው ያመለከቱት፡፡

ኅብረተሰቡ ዛሬ የተፈጸመ ጥቃት አለመኖሩን አውቆ የተረጋጋ መደበኛ ሕይወቱን እንዲመራ ያሳሰቡት መምሪያ ኃላፊው በማኅበራዊ ሚዲያ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የቆዬ መረጃ እየለቀቁ ሕዝቡን ማደናገር እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous articleኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከጎረቤት እና ከዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የግንኙነት ፖሊሲ በጥንቃቄ መቅረጽ እንዳለባት ተመላከተ፡፡
Next articleዳዳብ በተባለ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ድጋፍ ጠየቁ፡፡