
ግንኙነቱን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ጠቁሟል።
ግንቦት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደገለጹት፤ ከበርካታ ርብርብ በኋላ ጫናዎቹ በተወሰነ ደረጃ የመለዘብ ምልክት ቢያሳዩም ተጽዕኖዎቹ አሁንም በተለያየ መልክ ቀጥለዋል።
እነዚህን የውጭ ጫናዎች ለመቀልበስ አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ሥራ በተጠናከረ መንገድ ማከናወን ከኹሉም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን እየጣሰ መኾኑንና ዕርዳታ ለዜጎች እንዳይደርስ እንቅፋት እየኾነ ነው የሚል ክስ እንደሚያቀርቡ አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
የተቀናጀ የክስ ዘመቻ በማካሄድ የሰብዓዊ መብት ጉዳይን እንደፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም ጫና ሲያሳድሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ግን ሀገራቱ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስና ግንኙነታቸውን መልሶ የማሻሻል አዎንታዊ ለውጦችን ማሳየት ጀምረዋል ያሉት አቶ ደመቀ፤ ኾኖም አኹንም በጀርባ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መኾኑን አመላክተዋል።
ይህንን ጫና ለመመከት ለአሜሪካ ሴኔትና ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ጭምር የማነጋገር ሥራ ተሠርቷል። ይህ አይነት ጥረቶች ዳያስፖራውን ባሳተፈ መልኩ በተለያዩ ሀገራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በተለያዩ ፍላጎቶችና የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጦች ምክንያት እንዲሁም የዓለም ሥርዐት ተገማች ባለመኾኑ የዲፕሎማሲ ሥራችን በዕጅጉ ፈታኝ ኾኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን የማስጥበቅ እንዲሁም ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ጫና ፈጣሪዎቹን በማስገንዘብና በማለዘብ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነታችንን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
የዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመከላከል ረገድ የዳያስፖራው ሚና ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ደመቀ፤ ዳያስፖራው ለሀገራዊ ጥሪዎች በተለይም ወደሀገር ቤት ለተደረጉ ታላቅ ጥሪዎችና የህዳሴ ግድብ ድጋፎች ሰፊ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የተለያዩ ሀገራትን ባለስልጣኖች በማነጋገርና ሰልፍ በማካሄድ ለኢትዮጵያ ጥብቅና መቆሙን ገልጸዋል።
ዳያስፖራው የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመከላከልና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አቅም ኾኖ የሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ መሳተፉን አድንቀዋል። ወቅታዊና ሀገራዊ አጀንዳዎችን መነሻ ባደረጉ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት የበቃ ወወይም No more ንቅናቄን በውጤታማነት በማስተባበር ሚናቸውን ለተወጡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዳያስፖራዎች ምሥጋና አቅርበዋል።
ከዚህ ጥረት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን ለመጨመር ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደሀገሩ ገንዘብ እንዲልክ በተደረገው ክትትልና ድጋፍ በዘጠኝ ወሩ ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መላኩን አመላክተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 97 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ዳያስፖራዎች ወደኢንቨስትመንት መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ዳያስፖራው ለመከላከያ ሠራዊትና ለኅልውና ዘመቻው፣ ለበጎ አድራጎት ሥራዎችና በልዩ ልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች በድምሩ 263 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ለሀገሩ አለኝታ መኾኑን ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ከዳያስፖራው ባለፈ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም አንድነታቸውን በማጠናከርና ሰላማቸውን በማስጠበቅ የዲፕሎማሲ ሥራው ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
“የሀገር ሰላምና አንድነት ሲጠናከር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይም የተቀናጀ ሥራ ማከናወን እንችላለን፤ ወደቀጣናው ብናተኩር በጂኦፖለቲካል ፍላጎትና በልዩ ልዩ ውስጣዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ዲፕሎማሲያችን የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪና ቀድሞ መንቀሳቀስ የሚፈልግበት ዘመን ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ተደማጭነትን ለማሳደግና ተደራሽነታችንን ለማስፋት ካለፉት ዓመታት ልምዶችና ዘመኑ የሚጠይቀውን ተልዕኮ መነሻ ያደረገ ተቋማዊ የለውጥ ሥርዐት ተግባራዊ መኾን መጀመሩን እንደገለጹ ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት አላት ያሉት አቶ ደመቀ፤ ከኤርትራ ጋር የጋራ ጥቅሞቻችንን መሠረት በማድረግ በትብብር እየሠራን እንገኛለን፤ ግንኙነቱን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን ጠቁመዋል።
“የድንበር አካባቢ ንግድ የሚያሳድጉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የጉምሩክና የኢሚግሬሽን እንዲሁም የኹለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎችን ለማበጀት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።
በተመሳሳይም ከጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሌያና ሌሎቹም ጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር በመሥራት የሚነሱ ችግሮችን ለማፍታትና የንግድ፣ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ መኾኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ሀገራት፣ ሩሲያ፣ ቻይና ሕንድና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በነበረችበው ወቅት ኹሉ ያለማወላወል በዓለም አቀፍ መድረኮች ላሳዩት ድጋፍ አቶ ደመቀ መኮንን ምሥጋና አቅርበዋል።
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/