የጀግኖቻችንን የአብራክ ክፋዮች ዝቅ ብሎ ከፍ ማድረግ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው!

247

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊ ስትኾን የጀግና ልጅ ትኾንና በአስተዳደግህ ላይ ሁሉ ዋጋ ትከፍላለህ፡፡

ያለአሳዳጊ ፈተናዎችን በማለፉ የልጅነት ዕድሜን ማሳለፍ ለዘመናት የኖረ የብዙ ጀግና ኢትዮጵያዊያን ልጆች ያለፉበት የህይወት መንገድ ነው፡፡ የባለራዕዩ ንጉሥ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ገና በልጅነቱ ለግዞት፣ ለናፍቆት እና ብስጭት ተዳርጎ መከራን ተቀብሎ ያለፈው የጀግና ኢትዮጵያዊ ልጅ ስለነበር ነው፡፡

የኋለኛው ዘመን ተወዳጅ ንጉሥ ምኒልክ የልጅነት ዘመናቸው እስከ አምባ ላይ ግዞት የደረሰ ውጣ ውረድን ያሳለፈ ነበር፡፡ ከእያንዳንዱ ጀግና ኢትዮጵያዊ ጀርባ ስለሀገር ሲባል ደስታቸውን የተነጠቁ፣ ፍቅራቸውን የተቀሙ እና መከራን የተቀበሉ ልጆች ነበሯቸው፡፡

ከአንቀልባቸው ሳይወርዱ እና የእናቶቻቸውን ጡት ሳይጥሉ አባቶቻቸው በጀግንነት ያለፉባቸው እልፍ ኢትዮጵያዊ ሕጻናት በትውልድ ጅረት ውስጥ አልፈዋል፡፡ አባቶቻቸውን በስም ብቻ እንጅ በአካል የማያውቁ፣ በአባቶቻቸው እቅፍ ያልሞቁ ኢትዮጵያዊያን ሕጻናት የኢትዮጵያ ታሪክ አንድ አካል ነበሩ፤ አኹንም ድረስ ናቸው፡፡

ትውልድ ዑደታዊ ሂደት ቢኾንም የራሱ ተፈጥሯዊ ሕግ አለው፡፡ ልጅ ተወልዶ ወላጅ እስኪኾን ከቤተሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ እና ከሀገሩ የሚቸረው የልጅነት ጸጋ ብዙ ነው፡፡ የወላጅ ፍቅር እና እንክብካቤ ለነገ ሀገር ተረካቢ ልጆች የእድገታቸው አፈር እና ውኃ ነው፡፡ ይኽን የልጅነት ፀጋቸውን ተነጥቀው የወላጆቻቸው ፍቅር ለሀገር ኅልውና ገጸ በረከት የተቸረባቸው እልፍ ሕጻናት በየዘመኑ አልፈዋል፡፡

ልክ እንደ አሸባሪው ትህነግ ሀገር የሚጸናው በደም በተሰመረ መስዋእትነት እና ጦርነት ነው ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም ጦርነት ግን አፍራሽ መኾኑን መካድ አይቻልም፡፡ ጦርነት ሰብዓዊ ፍጡርን ያጎሳቁላል፣ አዛውንቶችን ያለጧሪ ልጆችን ያለአሳዳሪ ያስቀራል፣ ሃብት እና ንብረትን ያወድማል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ድህረ ጦርነት የልብ ስብራቱ ጠሊቅ፣ ሐዘኑ ዘመን ተሻጋሪ እና ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

ከእያንዳንዱ ጦርነት የሚያተርፉት ውስኖች የግጭቱ ነጋዴዎች ቢኖሩም በእያንዳንዱ ጦርነት ተጎጂ የሚኾኑት ብዙኃን ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ጦርነት ብርቋ አይደለም፡፡ ከውስጥ እስከ ውጭ በኢትዮጵያ ላይ ያልተነሳ አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ሽንፈትን አሜን ብላ እና ውርድትን ተቀብላ አታውቅም፡፡ በየዘመኑ ስለሀገራቸው ሉዓላዊነት እና አንድነት፤ ስለሰንደቃቸው ክብር እና ፍቅር የቤተሰቦቻቸውን መጻዒ ሕይዎት መስዋእት ለማድረግ የማይሰስቱ ልጆች አሏት፡፡ ግንባራቸውን ለአሩር፣ ደረታቸውን ለጦር እና እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው በየዱር ገደሉ የወደቁት ጀግኖች አያሌ ናቸው፡፡

ከእነዚህ እልፍ ጀግኖች ጀርባ የአባቶቻቸውን ፍቅር ያጡ ሕጻናት ትናንት የመኖራቸውን ያክል ዛሬም እያየን ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ ላይ ከፈጸመው የክህደት ጦርነት በኋላ በርካታ ሕጻናት ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ አባቶቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ ሀገርን አስወርሮ እና ሚስትን አስደፍሮ በውርደት ከመኖር ለነጻነት እና ለክብር ተፋልሞ መሞትን እንኳን አባቶቻቸው ሕጻናቱ እንኳን የሚመርጡት ኢትዮጵያዊ እሴት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ስትኾን ለክብር መሞት ከመቃብር በላይ የሚወሳ፣ ሀገርን፣ ቤተሰብን እና ትውልድን የሚያኮራ እና የሚዘከር ገድል ይኖረዋል፡፡

ትናንት ኢትዮጵያ ተገድዳ በገባችበት ጦርነት በርካታ ሕጻናት አባቶቻቸውን አጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ጥቂቶቹን በእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ ዓይተናል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ አባቶቻቸውን አጥተው ትናንት ያየናቸው የጀግና ልጆች እና እስካሁንም ያላየናቸው በርካታ ሕጻናት የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊያን የአደራ ልጆች ኾነዋል፡፡

የጀግና ልጆችን ተቀብሎ በፍቅር፣ በክብር እና በእንክብካቤ ማሳደግ ተተኪን ማፍራት ነው፡፡ ህጻናት ከሚሰሙት የወላጆቻቸው የጦር ሜዳ ውሎ ጀብዱ ጀርባ የመሰል ታሪኮች ተጋሪ የሚሆኑበትን ዘመን በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውን እና ሰንደቃቸውን በአደራ ተቀብለው ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የጀግኖቻችንን የአብራክ ክፋዮች ዝቅ ብሎ ከፍ ማድረግ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው!

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም የሌላት የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች ሀገር “
Next article“የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት እና ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን እንሠራለን” የፌዴሬሽን ምክር ቤት