ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገዉን የአፈር ማዳበሪያ መጠን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

367

አዲስ አበባ: ግንቦት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ግዙፍ የአፍር ማዳበሪያ አምራች ሀገራት ምርት ከሀገራቸዉ እንዳይወጣ ማገዳቸዉ እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ መጨመር ለአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ንረት ምክንያት ቢኾንም ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገዉን የአፈር ማዳበሪያ መጠን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በ2014 ዓ.ም የምርት ዘመን 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱ ተመላክቷል፡፡

ግዥ የሚፈጸመዉ የክልሎችን ፍላጎት ታሳቢ ተደርጎ እንደኾነ የገለጸዉ ሚኒስቴሩ ለአማራ ክልል ከከረመዉ 790 ሺህ ኩንታል የአፈር መዳበሪያ እና በአዲስ ከተገዛዉ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጋር ተዳምሮ በጥቅሉ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለክልሉ ይቀርባል ተብሏል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት እና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መንግሥቱ ተስፋ ከአሚኮ ጋር በነበራቸዉ ቃለ ምልልስ አርሶ አደሩ ለአፈር ማዳበሪያ ያለዉን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ግዥ እና አቅርቦት እየተካሄደ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ አቶ መንግሥቱ አሁን እየቀረበ ያለዉ የአፈር ማዳበሪያ 2013 ዓ.ም ሚያዝያ እና ግንቦት ላይ የተሰበሰበዉን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ነዉ ብለዋል፡፡

ሊፈጠር የሚችለዉን የአቅርቦት እጥረት ታሳቢ በማድረግ በዚህ ዓመት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተጠባባቂነት ማስቀመጣቸዉንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መገዛቱን የገለጹት አቶ መንግሥቱ በ2014 ዓ.ም የምርት ዘመን በጥቅሉ 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን እና ሊፈጠር የሚችለዉን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታት ታሳቢ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡ እስከ አሁን 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ጅቡቲ ወደብ ሲደርስ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ የማከፋፈያ ማዕከላት መጓጓዙን ገልጸዋል፡፡

ማዕከላዊ መጋዝኖች ከደረሱ በኋላ አርሶ አደሩ በቀጥታ ግዥ ወደ ሚፈጽሙባቸዉ የህብረት ሥራ ማኅበራት ይሰራጫሉ ያሉት ዳይሬክተሩ እስከ አሁን 4 ሚሊዮን የአፍር ማዳበሪያ ወደ እያንዳንዱ የህብረት ሥራ ማኅበራት መጓጓዙን ተናግረዋል፡፡

የከረመዉ አዲስ ከተገዛዉ የአፈር ማዳበሪያ ጋር ተዳምሮ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል አለ ያሉት ዳይሬክተሩ እስከ አሁንም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እጅ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡

.
አቶ መንግሥቱ 1 ሚሊዮን ኩንታል ዬሪያ የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ እየቀረበ ያለዉ የአፈር ማዳበሪያ በርካታ ዉጣ ዉረዶችን ያለፈ እንደኾነ ኅብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የአፈር ማዳበሪያ የጨረታ ዋጋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ዓለማቀፋዊ በመኾኑ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ነው ያስረዱት፡፡

ግዙፍ የአፍር ማዳበሪያ አምራች ሀገራት እንደ ቻይና እና ራሽያ የሚያመርቱትን የአፈር ማዳበሪያ ከሀገራቸዉ እንዳይወጣ ከማገዳቸዉ በተጨማሪ አሜሪካ የሚገኘዉ ግዙፍ ፎስፌት አምራች ድርጅት በኮቪድ እና ተዛማጅ ችግሮች ምርት በመቀነሱ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በመጨመሩ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋውን እንዳናረው ነዉ ያብራሩት፡፡

አሁን ላይ የአፈር ማዳበሪያ ከእነጭራሹ እንደማይቀርብ እና እጥረት እንዳለ የሚሠራጨዉ መረጃ ትክክል እንዳልኾነ ያነሱት አቶ መንግሥቱ ጉዳዩን ለማጥራት በተደረገዉ የመስክ ምልከታ በየህብረት ሥራ ማኅበራቱ የማዳበሪያ ክምችት ስለመኖሩ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ የማከማቻ ማዕከላት እና የህብረት ሥራ ማኅበራት የአፈር ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሮች በወቅቱ እንዲያደርሱ አስፈላጊዉ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ ስለመኾኑም አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleኢትዮጵያ እና ቱርክ በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ ስምምነቶችን ተፈራረሙ፡፡
Next articleአምስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።