
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ክፍል የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በድጋሜ ለመውረር ባደረገው ሙከራ ከሀገሪቱ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሀገራቸውን ላለማስደፈር በጀግንነት የተዋደቁ በርካታ አርበኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ አርበኞች መካከል ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ አንዱ ናቸው፡፡
የጠላት ጦር ይመቸኛል ባለው የሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተነስቶ ወደ መሀል ሀገር ሲገሰግስ የሰሜን አካባቢ አርበኞች ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ በተለይ የዋግ አካባቢ አርበኞች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሀገሪቱን ለመውረር የጣሊያን ጦር በተንቀሳቀሰበት ወቅት አዲስ አበባ ላይ የጠላትን እንቅስቃሴ ለመግታት የክተት አዋጅ በታወጀበት ጊዜ የዋግ አካባቢ አርበኞች ይህንን የሀገር አደራ ለመወጣት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ሁሉም በአንድነት ተመሙ፡፡ ይህን በወኔ እና በሀገር ፍቅር የተሞላ ጦር የመሩት ደግሞ አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ነበሩ፡፡
በተንቤን፣ አቢአዲ እና ማይጨው በኩል የመጣውን የጣሊያን ጦር ለመመከት የጦር ብልሃታቸውን ያሳዩት አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ድል ቢቀናቸውም የጠላት ጦር የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ያገኙትን ድል ቀልብሶባቸዋል፡፡
የታሪክ ምሁር አያሌው ሲሳይ (ዶክተር) እንደነገሩን የጠላት ጦር የዋግ አካባቢን እንዳይቆጣጠር ለማድረግ ከንጉሥ ግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ጋር በመነጋገር የአርበኝነት ሥራን ይሠሩ ነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ዳህናን ይዞ ስለነበር ይህን አካባቢ ከጠላት እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ የሀገሬውን አርበኞች በማስተባበር የሰርጎ ገብ ጥቃት በመፈጸም እስረኞችን ከማስፈታት በዘለለ ጠላት ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ ረፍት ይነሱት እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ጄነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ “መርቆሪዎስ” በተባለ ዋሻ ለሁለት ዓመታት ከመንፈቅ በመመሸግ ጠላትን ረፍት ነስተዋል፤ አርበኛ ሌተናል ጄነራል ደጅአዝማች ኀይሉ አርበኞችን በማስተባበር “እምቢ ለሀገሬ” በማለት ይታወቃሉ፡፡
ጣሊያን የመጀመሪያውን የአውሮፕላን የመርዝ ጋዝ ለመጠቀምም የተገደደው አስቸጋሪ እና የእግር እሳት በሆነበት በአርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ ጦር ላይ ነበር ብለዋል የታሪክ ምሁሩ፡፡
እንደ ምሁሩ ገለፃ ከሰቆጣ ወደ ዳህና የጠላት ጦር እየገሰገሰ እንደሆነ የተረዱት አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ ከመሸጉበት ወጥተው ጉራንባ ቲኩል ወደ ተባለ ቦታ በማቅናት ነሐሴ 19/1929 ዓ.ም የመጀመሪያውን ጦርነት ከጣሊያን ጦር ጋር አካሄዱ፡፡ ከጦራቸው ጋር በመመካከርም የጠላት ጦር እስኪደመሰስ ድረስ መግፋት እንዳለባቸው በመተማመን በሦስት አቅጣጫ የጠላትን ጦር ተፋልመዋል፤ አምደወርቅ ላይም ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ “አጋዘን መገርሰም” በተባለ ቦታ ላይም ሦስተኛውን ጦርነት በማካሄድ ጠላትን ድል መትተዋል፡፡ “ድግሪሽ ተራራ” ላይ ለአራተኛ ጊዜ ባካሄዱት ውጊያ ጠላትን ድል አድርገዋል፤ ጀግንነታቸውንም አሳይተዋል ብለዋል ዶክተር አያሌው፡፡
አርበኛ ሌተናል ጀነራል ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ በ1929 ዓ.ም በጀግንነት ሕይወታቸው ያለፈ ቢሆንም የሳቸውን ፈለግ የተከተሉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አርበኞች ጣሊያንን ረፍት በመንሳት ሀገራቸውን ነጻ አውጥተዋል፡፡ ከድል በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ ደጅአዝማች ኀይሉ ከበደ ለፈጸሙት አኩሪ ገድል የሌተናል ጀነራልነት ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/