ʺበደረሰበት እያስጨነቀ፣ በታች ነው ሲሉት በላይ ዘለቀ!”

279

ባሕር ዳር : ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ነጭ ጤፍ እንደ አፈር የሚታፈስበት፣ ወተትና ማር እንደ ግዮን ወንዝ የሚፈስበት፣ ጀግኖች የሚፈልቁበት፣ ሊቃውንት የሚኖሩበት፣ ጠቢባን የተገኙበት፣ ደግነት፣ ጀግንነት የሞላበት ምድር፡፡ ክረምት ከበጋ ጎተራው የማይጎድል፣ ደከመኝ ሳይል የሚያርስ፣ በረዶ የመሰለ ነጭ ጤፍ በሰፊ አውድማ ላይ የሚያፍስ፣ ቅዳሜ እሁድ ጸሎት የሚያደርስ፣ ጠላት ሲመጣ የሚተኩስ፣ ጠላት የሚመልስ ጀግና ሕዝብ፡፡

ጀግና ከሚፈልቅበት፣ ፈሪ ከማይኖርበት፣ ሠንደቅ ከሚከበርበት፣ ጥበብ ከሞላበት ምድር እልፍ ጀግኖች ተወልደዋል፣ እልፍ ጀገኖች የልባቸውን ሠርተዋል፣ በጀግንነት ኖረዋል፣ በጀግንነት ሠንደቃቸውን ብለው ነብሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ከግዮን ምንጭ ጋር ጥበብ የሚፈልቅበት፣ ከለምለሙ ምድር ላይ ጀግና እንደ ችግኝ ተኮትኩቶ የሚያድግበት ምድር ለጠላት አይመችም፣ አንጋዳው አያረማምድም፣ ጠላት አይደፍረውም፣ ፈሪ አይረግጠውም፣ ወላዋይ አይሻገረውም፡፡

የጀግኖችን ሥፍራ ማን አልፎ ይሻገራል፣ የጀግኖችን ቀዬ ማን ችሎ ይደፍራል፡፡ በዓድዋ ተራራ ላይ ጀንበሩ የጠለቀችበት፣ ዝናው የጠፋችበት፣ ክብሩ የተገፈፈችበት የጣልያን ሠራዊት ለሌላ በቀል መሰናዳት ጀምሯል፡፡ በዓድዋ ተራራ ላይ የጥቁሮች ፀሐይ ከፍ ብላ በርታለች፣ የነጮች ጀንበር ወደ መቀመቅ ወርዳለች፣ ነጭ ደንግጧል፣ ጥቁር አጎልብቷል፣ በክንዱ ኮርቷልና ዓለም ተጨንቃለች፣ በጥቁሮች ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ድል ተገኝቷልና፣ ምድር አይበቃውም፣ ጦረኛ አያቆመውም የተባለው የጣልያን ጦር አንድ ቀን ሳይዋጋ በዓድዋ ተራራ ላይ እንዳልነበር ሆኗል፡፡ የጣልያንን ጦር ድል መስማት ሲቋምጡ የነበሩት ሁሉ ደንግጠዋል፣ የሰሙትን ማመን አቅቷቸዋል፣ የነጭን ክፉ አብዮት ያፈራረሱት፣ ኃያል ነኝ ያለውን ያንበረከኩት፣ ይቅርታ ያስለመኑት፣ ከእግራቸው ሥር ያዋሉት፣ የጥቁርን የመከራ ዘመን በደማቸው ፍሳሽ፣ በአጥንታቸው ክስካሽ የፈጸሙት የኢትዮጵያ ጀግኖች በዓድዋ ተራራ ላይ እየሸለሉ፣ እየፎከሩ ድላቸውን አበሰሩ፡፡ ሀገራቸውን ለጠላት አሳልፈው ላይሰጡ ባልደረቀው ደም ቃል ኪዳን አሠሩ፡፡ ቃላቸውን አጠበቁ፤ ከወትሮውም ኢትዮጵያዊ ቃሉን አያብልም፣ ካመነ አይከዳምና ቃላቸውን አይሽሯትም፣ ለሠንደቃቸው ክብር፣ ለሀገራች ፍቅር ሲሉ ጠላት ወዳለበት ፣ መሪር ሞትን ለመታገስ ተማማሉ፡፡

ባሕር አቋርጦ፣ የብስ ሰንጥቆ ከአንበሶቹ መክረሚያ የገባው የጣልያን ሠራዊት የተነሳበትን ቀን እየረገመ በዓድዋ ተራራ ላይ የሳንጃ፣ የጦርና የጎራዴ እራት እየሆነ አለቀ፤ እድል የቀናው ጀግኖች አርበኞችን እየተማፀነ እጅ ሰጠ፣ የሆነለት ነብሱን ሊያድን ወደ ኋላ ፈረጠጠ፡፡ ነጮች አይተውት የማያውቁት ውርደት ገጥሟቸዋልና አንገታቸውን ደፉ፣ የሮም ጎዳናዎች በእኩለ ቀን ፀሐይ ጨለመችባቸው፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ሀፍረት ዋጣቸው፣ ልጆቻቸውን ለዘመቻ የላኩ እናቶች እንባ ተናነቃቸው፣ በኢትዮጵያ ተራራዎች ላይ የወጣችው ጀንበር ግን አሻግራ ማብራት ጀምራለች፣ በዓለም ዙሪያ የተኛው ጥቁር ሁሉ ቀስቅሳለች፣ ከገባበት ዋሻ ውስጥ ጨረሯን እየላከች ብርሃን አሳይታለች፣ በጨረሯ ልክ ፍትሕና እኩልነትን አሳይታለች፡፡

በዓድዋ ተራራ ላይ ቅስሙ የተሰበረው የጣልያን ሠራዊት ለአርባ ዓመታት ድምጹን አጥፍቶ ተዘጋጀ፡፡ ከዓድዋው የበለጠ ዝግጅት አድርጎ፣ ሌሎች እቅዶችን ነድፎ ዳግም ለበቀል ተነሳ፡፡ ቅድሰቲቷን ሀገር ሊደፈር፣ ኢትዮጵያውያንንም ሊያሳፍር ገሰገሰ፡፡ ምድሯን ረገጠ፣ ድንበሯን ደፈረ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተነሱ፡፡ ከጠላት ጋር ጉሮ ለጉሮሮ ተናነቁ፡፡ ዳሩ እንደ ዓድዋው በአንድ ጀንበር እድል አልቀናቸውም፡፡ ጦርነቱ ተራዘመ፤ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ለዓለም አቤት ይበሉ ተብሎ ወደ ውጭ ተላኩ፡፡ አርበኞች የሚሰበስባቸው ጠፋ፣ አንድ የሚያደርጋቸው ታጣ፤ አርበኞች ግን ንጉሣችን ወጥተዋል፣ ጠላትም አይሏል ሳይሉ ከጠላት ጋር ትንነቃቸውን ቀጠሉ፤ በዱር በገደሉ እየተመላለሱ ጠላትን ይወቁት ጀመር፡፡

ከጀግኖች ምድር ከወደ ጎጃም የተፈጠረው፣ ወተትና ማር ጠጥቶ ያደገው፣ ጀግንነት ከአባቱ የወረሰው፣ ነፍጥ በልጅነቱ ያነሳው የዘለቀ ላቀው ልጅ ወጣቱ በላይ ጠላትን ሲያይ ልቡ መረረች፣ አብዘቶ ተቆጣ፣ የነጭ ድፍረት አበሳጨው፣ ʺ ይህ ሊጥ መልክ” ሲል እንደ ነብር ተቆጥቶ፣ እንደ አንበሳ አግስቶ በልጅጉን አንስቶ በረሃ ወረደ፡፡ ከዓባይ በረሃ የበለጠ ክንዱ የሚፋጀው፣ አፈሙዙ ጠላትን እየለቀመ የሚፈጀው በላይ ጠላትን እያለመ ወቃው፣ ሰቅዞ ይዞ አስጨነቀው፡፡

ገና በልጅቱ የአባቱን ʺናስ ማሰር” ጠመንጃ አንሰቶ ያነገተው፣ ዒላማ የለመደው፣ ለአንድ ጠላት አንድ ጥይት የሚሰጠው በላይ ተኩሶ መሳት አያውቅም ነበርና ጠላት ጨነቀው፣ ማምለጥ ተሳነው፡፡ ኮስታራ ወንድ ነውና ጀግናው በላይ የጦር ስልቱ ከጠላት የረቀቀ ነበርና ጠላትን እያገላበጠ ወቃው፡፡
በላይ ደግነቱ፣ ጀግንነቱ፣ አርቆ አሳቢነቱ፣ መልካም ባሕሪው ሁሉም የሚከተሉትን ስቧቸዋል፡፡ የአባ ኮስትር ክንድ አልቀመስ ሲል በላይን ያገኘው የመሰለው ጠላት የጎጃምን ቤት እያቃጠለ ሕዝቡን ያሰቃይ ጀመር፣ በላይ ደሙ ፈላ፣ አልህ ያዘው፣ ጠላትን በየደረሰበት ወቃው፡፡ የጣልያን ሠራዊት በዘመናዊ መሳሪያ እየታገዘ በአየር በምድር እየደበደበ ቢታገልም በልጅግ የጨበጠው በላይ አልቀመስ አለ፡፡ ከጠላት ሠፈር ገስግሶ እየገባ፣ በመንገድ ላይ ድንገት ጥቃት እያደረሰ ጠመንጃና ጥይት እየማረከ፣ በማረከው ጥይት እየተማታ ጠላትን አሰቃየው፣ መውጫ መግቢያ ነሳው፡፡ ከምርኮ ላይ ምርኮ እየጨመረ፣ ከግዳይ ላይ ግዳይ እየደረደረ ትግሉን ቀጠለ፡፡
መጀመሪያ አሻፈረኝ ብሎ በረሃ ሲወርድ ጥቂት የነበረው የበላይ ተከታይ እየበረከተ መጣ፡፡ ሕዝቡ እንዲረዳው ዐዋጅ አስነገረ፣ በጠላት እጅ ጉዳት እንዳይደርስበትም ሕዝቡን አስጠነቀቀ፡፡ ሕዝቡ ተከተለው፣ አለንልህ አለው፡፡ እንኳን ተከታይ አፍርቶ ለወትሮውም ጀግና ነበርና ክንዱ በረታ፡፡

ʺበደረሰበት እያስጨነቀ
በታች ነው ሲሉት በላይ ዘለቀ” እንዳለ ዘፋኙ፣ ጠላቶች በታች ሲመጡ በላይ ይታያቸዋል፣ አልመው ሊመቱት ሲጥሩ ቀድሞ ይጥላቸዋል፣ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ይማርካቸዋል፣ ይገድላቸዋል፣ በላይ የማይጨበጥ ጀግና ሆነ፡፡ ቀን ቀን እየመጨረ ጦርነቱ እንደቀጠለ ዓመታት ተቆጠሩ፣ የእነ በላይ ወገብ ትጥቅ ሳይለየው ጊዜው ገሰገሰ፡፡ ጠላት በጎጃም ምድር መኖር አቃተው ተገዶ መልቀቅ ጀመረ፡፡ ሌሎች አርበኞችም በየሀገሩ ተነስተው ጠላትን ያደባዩት ነበርና ጠላት ተፍረከረከ ስንቅና ትጥቁን እየጣለ፣ መሸሽ ጀመረ፣ ጀንበራችን ተመልሳለች፣ ጣልያን ዳግም ኮርታለች ብለው የነበሩት የጣልያን መኳንንትና መሳፍንት ድጋሜ አፈሩ፡፡ የጀግና እናት የሆነችው ኢትዮጵያ ኮራች፣ ዝናዋን ለዓለም አስተጋባች፡፡ ጣልያን ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ወጣ፡፡
በስደት የነበሩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴም መጡ፡፡ በላይም ይከተለው የነበረውን ሠራዊት ንጉሥ ሆይ እኔ እንዲህ በሰላም ጊዜ አርሼ እበላለሁ ሠራዊቴን ይቀበሉኝ አላቸው፡፡ እሳቸውም የሰላም ጊዜ ሥራ አለ፣ ሀገር ማስተዳደር አለ አሉት፡፡ እርሱ ግን ሹመት ሽልማት አይሻም ነበርና አይሆንም አለ፡፡ አግባቡት፡፡ አባ ኮስትር ደጅ አዝማች ሆኗል፡፡ በመካከል አባ ኮስትር ከንጉሡ ጋር ተቀያየመ፡፡ ሸፈተ፣ ሊወጋን ነው እየተባለ ተወራበት፡፡ ከንጉሡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የበለጠ ሻከረ፡፡ የዘለቀ ልጅ እያለ በልጅጉን ካነሳ የማይቀመሰው በላይ ሊወጉት ፈልገው አልቻል አላቸው፡፡ ምህረት አድረግንልሃል ብለው ወደ አዲስ አበባ ወሰዱት፡፡ ነገሩ ሌላ ኖሯል፣ ጠላት የሮጠለትን፣ ባላንጣ የመሰከረለትን ጀግና ይገደል ዘንድ ተወሰነ፡፡ አባ ኮስትር በጎልማሳ እድሜው የጠላት ጥይት ሳይነካው የክፉዎች ገመድ አነቀው፡፡ በወርሃ ጥር 1937 ዓ.ም በ35 ዓመቱ አባ ኮስተር ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡

ʺጠላት ካንዣበበ ክፉ ቀን ከመጣ
ቀስቅሱት በላይን አስተካክሎት ይምጣ”

ጠላት ሲያንዣብብ ክፉ ቀን ሲመጣ በላይን ጥሩት ይቀስቀስ እርሱ አስተካክሎት ይመጣል፡፡ እርሱ ሳይሰለች ተዋግቶ ሀገር ነጻ ያወጣል፤ ክፉ ቀን አሳልፎ መልካም ዘመን ያመጣል፣ የወንዶች ቁና የበረሃው መብረቅ አባ ኮስትር በላይ ሹመት ለምኔ እያለ በላይ የሚለውን ስሙን ይዞ በልጅጉን አንስቶ ለሀገር ተዋድቋል፣ ሁሉ ነገሩን ሰጥቷል፡፡ ክብር ይገባሃልና አባ ኮስትር ሆይ ክበር፡፡ ስምህ በምድር ላይ እስከ ወዳኛው ይኖራል፣ ዝናህ ዳር እስከ ድንበር ይጠራል፡፡
በላይ ነጮች ሀገሩን ሲበድሏት ስለተመለከተ እነርሱን ሰላም ለማለትም ይጸየፍ ነበር ይባላል፡፡ በአንድ ወቅት ጄኔራል ሳንፎርድ የተባለ የእንግሊዝ የጦር መኮንን ሰላም ሊለው እጁን ሲዘረጋ ነጭ እጄን አይነካውም ብሎ ከለከለው ይላሉ አበው፡፡ የበላይ ጀግነነት ይቀስቅስህ፣ የበላይ ወኔ ያስነሳህ፣ ለሀገሬ ሁሉንም እሰጣለሁ ብለህ ተነስ፡፡

በታርቆ ክንዴ

Previous articleየአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች በኅልውና ዘመቻ ወቅት ላበረከቱት ሙያዊ አስተዋፅኦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እውቅና ሰጠ።
Next article“ያልተዘመረላቸው ኢትዮጵያዊ ሌተናል ጀነራል”