
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የማታሸንፉትን አትግጠሙት ትርፉ ድካም ነው፣ የማትገፉትን አትወዝውዙት ትርፉ መውደቅ ነው፣ የማትመቱትን አትተኩሱበት ትርፉ ጥይት ማባከን ነው፣ ድል የማታገኙበትን አትነካኩት ትረፉ ውርደት ነው፣ የማትረቱትን አትሞግቱት ትርፉ መረታት ነው፡፡ በእርሷ ላይ ክንዱን አንስቶ ድል ያገኘ ማነው ? እርሷን ነክቶ በፊቷ ሳይዋረድ የቀረው ማነው ? ለድል የተፈጠረች፣ ጀግና የሚፈልቅባት ዥረት የሆነች፣ ዘመናቱን ሁሉ በድል አድራጊነት የተረማመደች፣ በክፉ ያዩዋትን የቀጣች፣ በመልካም ያዩዋትን የሸለመች፣ የሾመች፣ ያከበሯትን ያከበረች፣ ክብሯን የነኳትን ደግሞ ያዋረደች ናት፡፡
ምደሯ ጀግና ከማፍለቅ ቦዝኖ አያውቅም፣ የአባቱ ጋሻ በልጁ ዘመን አይወድቅም፣ አባቱ ጠላት የመለሰበትን፣ ሀገር ያስከበረበትን፣ ጠላት የቀጣበትን፣ ድል ያገኘበትን ልጁ አንስቶ ታሪክ ያስቀጥልበታል፣ ጠላት ይቀጣበታል፣ ሀገር ያስከብርበታል፣ ሠንደቅ ከፍ ያደርግበታል፡፡ የጋሻ ክብር አለው፣ የጀግናውም ማዕረግ አለው፡፡ አባቱ ያወረሰውን ልጁ እየወረሰ፣ የአባቱን ሡሪ እየታጠቀ፣ ጠላትን እያስጨነቀ፣ ሀገር ከነድንበሯ፣ ሠንደቋን ከእነክበሯ ያቆያል፡፡ አቆይቷል፡፡
ለእናት ሀገር ሲባል ደም እንደ ሐምሌ ጎርፍ ፈስሷል፣ ለሠንደቅ ክብር ሲባል አጥንት ተከስክሷል፣ ለሕዝብ ፍቅር ሲባል ሕይወት ተገብሯል፡፡ በደማቸው ለውሰው፣ በአጥንታቸው አጽንተው፣ በሞታቸው ሕያው ኾነው ሕያው አድርገው ነው ያኗሯት፡፡ በዋዛ የተሰጠች ሀገር አይደለችም እና በዋዛ አልተገነባችም፣ በዋዛ ታሪኳን ከፍ አላደረገችም፣ በዋዛ አልቀደመችም፣ በዋዛ የድል እመቤት፣ የአሸናፊነት ንግሥት አልተባለችም፡፡
ፈጣሪ ያከበራት፣ ለምስክር ያስቀመጣት፣ ከሁሉም አስበልጦ ያላቃት፣ በጥበብ ያስዋባት፣ በረከትን የሰጣት፣ በምስጢር የመላት፣ ቃል ኪዳኑን ያስቀመጠባት፣ አበው ሳያቋርጡ ምልጃና ጸሎት የሚያደርሱላት፣ ከሰማይ በረከት የሚቀበሉባት፣ ጀግኖች ሳያንቀላፉ፣ ትንሽም ሳይዝሉ የሚጠብቋት፣ ድል አድራጊዎች በኩራት የሚኖሩባት፣ የድል እናት ናት፡፡ የተሰጣትን ምስጢር፣ የማይናወጸውን ክብር፣ የፈጣሪዋን ፍቅር ያዩ ሁሉ ይቀኑባታል፡፡
የያዘችውን መንጠቅ ፣ በጉያዋ ውስጥ ያለውን መሥረቅ፣ ምስጢሯን መመርመር፣ ምድሯ በኃይል መውረር ያምራቸዋል፡፡ በጉያዋ የታቀፈችውን እልፍ አእላፍ ምስጢር፣ በምድሯ ውስጥ ያለውን ድንቅ በረከት ሁሉ ለመውሰድ ያምራቸዋል፡፡ ምስጢራት ሁሉ ከእርሷ ይጀምራሉ፣ በእርሷ ይኖራሉ፣ በእርሷም ይፈጸማሉ እና የእነርሱ ለማድረግ ይመኛሉ፡፡ በጥቁሮች ምድር በምሥራቃዊ ንፍቅ ፀሐይ በምትወጣበት፣ ተስፋ በሚመጣበት፣ የመዳን ቀን በሚታሰብት፣ ተድላና ደስታ ባለበት በኩል ረቂቅ የሆነች ሀገር አለችና ረቂቋን ለመውሰድ የሚቋምጡት ብዙዎች ናቸው፡፡
ጠላቶች በየዘመናቱ ጦር ሰብቀው፣ ሠራዊት አሰልፈው፣ ድል ናፍቀው እየተነሱ ወደ ምድሯ ጎርፈዋል፡፡ ታዲያ ጀግንነት ከአባት ወደ ልጅ በሚተላለፍባት ሀገር ጠላት መሰንበት አይቻለውምና እየፎከረ መጥቶ እያለቀሰ ይመለሳል፡፡ ብዙውም ሊወስዳት በተመኛት ሀገር አፈር ይለብሳል፡፡ እርሷን አሸንፎ የተመለሰ፣ በደል የገሰገሰ አልተገኘም፡፡ እርሷ ሁልጊዜም በድል አድራጊነት፣ በጀግንነት፣ በአሸናፊነት ነውና የምትገሰግሰው፡፡ሥሟ ጠላትን ያስበረግጋል፣ በሥሟ የዘመተ ሁሉ ድል ያደርጋል እማማ ኢትዮጵያ፡፡ በሚያስፈራው ሥሟ ተጠርተው የዘመቱት፣ የሚያስደነግጠውን ክብሯን ከፊት አስቀድመው ነፍጥ ያነሱት፣ ሠንደቋን ከፍ አድርገው የተኮሱት ሁሉም አሸንፈዋል፡፡ በጠላት ላይ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ በድል አድራጊነት ተመላልሰዋል፡፡
ሮም ኃያል በነበረችበት በዚያ ዘመን መጣሁብህ ያለችው ሁሉ ይፈራ ነበር፡፡ ተጓዡ የሮም ሠራዊት በሮም አደባባዮች ሲንቀሳቀስ በአሻገር ዝናውን የሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ መውጫ መግቢያው ሁሉ ይጠፋበታል፡፡ እንደ ሮም ሁሉ ኃያል የነበሩት ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ከግዛታቸው እያለፉ፣ ከወሰናቸው እየተሻገሩ ጦርነት ይከፍቱ ነበር፡፡
ኃያል የነበሩት ሀገራት የጥቁሮችን ምድር አፍሪካን ተቀራምተው በጦር ስቃይዋን አብዝተውባት ነበር፡፡ የሮም ሠራዊትም በአፍሪካ ምድር ኃያል ሆኗል፡፡ በየሄደበት ሁሉ ድል እየቀናው የቀኝ ግዛቱን እያሰፋ ነው፡፡ አፍሪካውያን ለነጭ እጃቸውን እየሰጡ የበደልን ጽዋ ተጎነጩት፣ ነጮች ደግሞ በጥቁሮች ላይ የግፍን ዝናብ አዘነቡት፡፡ ከድል ላይ ድል መጎናጸፍ የለመደው የሮም ሠራዊት በታሪኳ ጠላት ነክቷት ወደ ማታውቀው ሀገር ይሄድ ዘንድ በነገሥታቱ፣ በመኳንንቱና በመሣፍንቱ ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡ ሮም በሠራዊቱ ድምጽ ተመላች፣ ሠራዊቱ በድል ይመለስ ዘንድ መልካም ምኞት ተሰጥቶት፣ ሠራዊቱም በድል ተመልሶ የሮምን ገናናነት እንደሚያስጠብቅ ቃል ገብቶ ገሠገሠ፡፡ ሮም ሩቅ ኢትዮጵያ ቅርብ በማለት ከሮም ተነሳ፡፡
ኀያሏ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ቀኝ ግዛት ተፈርዶባት፣ የሮም ሠራዊት ሊያጥለቀልቃት ትዕዛዝ ተሰጥቶት ተነሳ፡፡ የሮም ድንፋታ፣ የሠራዊቱ ጫጫታና ጋጋታ የማያስደነግጣቸው ኢትዮጵያውያን የሚመጣውን ሁሉ ለመመለስ ተዘጋጅተው ጠበቁ፡፡
አባ ዳኛው ምኒልክ ሠራዊታቸውን አስከትለው፣ በአስፈሪ ግርማ በፊት በኋላ ታጅበው ጠላት መጣበት ወደ ተባለው ገሰገሱ፡፡ ድል የለመደው የሮም ሠራዊትም የኢትዮጵያን ምድር ረግጧል፡፡ ለክብር መሞትን ጽድቅ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ጀግኖች ለክብራቸው ተሰለፉ፡፡ ጎራዴው ተስሏል፣ ጠመንጃቸው ተወልውሏል፣ ሣንጃና ጦሩ ተሹሏል፡፡ በአምባላጌ ያገኙትን አፈር አለበሱት፣ በመቀሌ ደገሙት፣ በዓድዋ ደመደሙት፡፡
አሥፈሪዋ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከፍ ብላ ተውለበለበች፡፡ ከሮም የተነሳችው ሰንደቅ በጥሻ ውስጥ ከሠራዊቷ እጅ ተለይታ ወደቀች፡፡ ሮም ዓድዋ ላይ በተተኮሰባት ጥይት፣ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ በደረሰባት ሽንፈት ጸጥ ረጭ አለች፡፡ ኢትዮጵያን መንካት በነዲድ እሳት መጫዎት ነውና እሳት በላቸው፡፡ ዓለም ተደነቀች፣ ሮም በዓለም አደባባይ አፈረች፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከበረች፣ በዓለሙ ሁሉ ናኘች፣ ለተጨቆኑት ተስፋ ሆነች፡፡
በዓድዋ ተራራ ላይ የተሸነፈችው ኢጣሊያ ለዳግም ወረራ ከአርባ ዓመታት በኋላ ተመልሳ መጣች፡፡ የጀግና ምንጭ ይደርቅባት ይመስል፣ ከአርባ ዓመታት በኋላ ተመልሳ ስትመጣ ድል የምትቀዳጅ ኢትዮጵያንም በቀኝ ግዛት ሥር የምታደርግ መስሏት ነበር፡፡ ዳሩ ሌላ ነገሩ፤ የአርባ አመቱን ቂም አንስታ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተች፡፡ የአባቶቻቸው ልጆች ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ተነሱ፡፡ አርባ አመታት የተዘጋጀችው ኢጣልያ በብዙ መልኩ ተዘጋጅታ ነበር፡፡ እንደ ዓድዋው ሁሉ በግማሽ ቀን ከመሸነፍ ድናለች፡፡ ከባዱ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ቀናት ፣ ሳምንታትን ፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን መተካካት ጀመሩ፡፡
ፈጣሪዋንና ጀግንነቷን ተማምና የገጠመችው ኢትዮጵያ ለጠላት እሳት ሆነች፡፡ በዘመኑ ነግሠው የነበሩት አባ ጠቅል ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን እውነት አቤት ለማለት ወደ ውጭ ሄደዋል፡፡ የጠላትን መስፋፋት ያዩት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የአርበኝነቱን ሥራ ተያያዙት፡፡ ዱር ቤቴ ብለው ጠላትን አላላውስ አሉት፡፡ የኢትዮጵያ ተራራዎች ለጠላት መቀበሪያ ሆኑ፡፡ እሳት የሚተፋው የአርበኞች አፈሙዝ ጠላትን አጨደው፡፡
ʺምን ያበደ ነው ምን የሰከረ
የእማማን ድንበር የሠረሠረ
የበልጅግ ጥይት ጠጥቶ አደረ” እየተባለ የኢትዮጵያን ድንበር የሠረሰረው ጠላት የበልጅ ጥይት እየጠጣ በዱር በገደሉ እየወደቀ ቀረ፡፡ ክብር እና ነጻነት በወጉ የሚገባቸው ጀግኖች አሳምረው ቀጡት፡፡ አገላበጡት ቆሉት፣ አፉን ተመልከት እያሉ እርሳስ አጎረሱት፡፡ ጠላት የሚረግጠው፣ የሚጨብጠው፣ ሁሉም እሳት ሆነበት፡፡ መድረሻ አጣ፡፡ ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት አድርገህ ጠብቅልን የሚሉት አበው በጸሎት፣ አርበኞች በጥይት ጠላትን ለበለቡት፡፡
ልጄ በድል ተመለስ ብላ የላከችው የኢጣሊያ እናት የደም እንባ አነባች፣ ማቅ ለበሰች፣ አብዝታ አለቀሰች፣ አንጀቷን በሐዘን አላወሰች፣ ልጇን የአርበኞች ጎራዴ በልቶት ቀርቷልና። ልጇ በኢትዮጵያ ተራራዎች የአውሬ እራት ሆኗልና፡፡ ልጇ ከኢትዮጵያ አፈር ጋር ተቀላቅሎ ዳግሞ ወደ ኢጣሊያ ላይመስ አሸልቧልና፡፡
ከአርባ ዓመታት በኋላ በሮም ሠማይ ሥር ፈገግ ብላ የነበረችው ጀንበር ዳግም ብርሃኗን ከለከለች፣ ደም መስላ ጠፋች፣ የሐዘን ካባዋን ማውለቅ ጀምራ የነበረችው ሮም ዳግም ማቋን ደረበች፣ ዳግም አፈረች፡፡ ዳግም ተዋረደች፡፡
ልጇ ድል ያደረገው የኢትዮጵያ እናት እልል አለች፣ እንኳን ወለድኩ ስትል ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ተላብሳ በምድሯ ተመላለሰች፡፡ በደስታ ከነፈች፡፡ ከአርባ ዓመታት በፊት በዓድዋ ሰማይ ላይ የተፍለቀለቀችው ጀንበር የበለጠ ደመቀች፡፡ ከዳር ዳር አበራች፣ የጨለማውን ዘመን ገፈፈች፡፡
ታምዕር መሥራት የማይሰለቻቸው ኢትዮጵያውያን ዳግም ታምር ሠርተው ዓለምን አስደመሙት፡፡ የማትሸነፈዋን ሠንደቅ በድል አድራጊነት አውለበለቡት፡፡
እኛ የአሸናፊዎች ልጆች ነን፡፡ አሸናፊዎች ሲል ታሪክ በጉልህ ቀለም የቀረጸን፡፡ ድል አድራጊዎች ሲል ዓለም ያደነቀን፣ ትውልድ ያከበረን፡፡ የማያረጅ ታሪክ፣ የማይደበዝዝ ስም ያለን፡፡ የአሸናፊ ልጅ የሆነ አሸናፊ ደግሞ ችግር አያስበረግገውም፣ መከራ አያስደነግጠውም፣ ንውጽውጽታ ዓላማውን አያስተውም፡፡ ተነስ እንደ አባቶችህ በአንድነት ቁምና ጠላቶችህ ይግረማቸው፣ የማንለያይ ኢትዮጵያውያን ነን በላቸውና አሳፍራቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ክንድ የማያረጅ ድል አምጥተዋል፡፡ ትውልድ ሁሉ የሚኮራበት ታሪክ ቀርጸዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን አንድነትና ብርቱ ጽናት ድል የራባቸው በመለያየትህ ማሸነፍን ናፍቀዋልና አንድ ኾነህ አሳፍራቸው፡፡ ተስፋ እንደ ሌላቸው አሳያቸው፡፡ ማሸነፍ ለኢትዮጵያ እንጂ ለጠላት የተገባ አይደለም በላቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/