
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እድሜ ጠገብ ነች፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ሀገራት እንደ ሀገር ሳይታወቁ ኢትዮጵያ ሥርዓት አንብራ እና ሥነ መንግሥት አዋቅራ በሕግ የምትመራ ሀገረ ቀደምት ነበረች፡፡
የመላው ጥቁር አፍሪካዊያን የባርነት ሰንሰለት የነበረውን ቅኝ ግዛት በተጋድሎ አልቀበልም በማለት ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ጎልቶ ቢጠቀስም ለሰንደቋ ክብር እና ለሉዓላዊነቷ ዘብ በየዘመኑ አያሌ የሕይወት ዋጋ ተከፍሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በአራቱም አቅጣጫዎች በየዘመኑ የጠላት ፍላፃ ሊያወድማት ሞክሯል፡፡
ከዘይላ እስከ በርበራ፣ ከኦጋዴን እስከ ተምቤን፣ ከምፅዋ እስከ አድዋ፣ ከጎንደር እስከ ሀረር፣ ከሸገር እስከ ዳር ሀገር ጠላት ያልወደቀበት እና ጀግኖች ያልተሰውበት ቦታ አይገኝም፡፡ ትህትና ለኢትዮጵያዊያን ጫማ የመኾኑን ያክል ነጻነት ደግሞ ሸማቸው ነው፡፡ የሀገራቸውን እና የሰንደቃቸውን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነገር ባዩ ቁጥር ጫማቸውን አውልቀው ለሸማቸው ይዋደቃሉ፡፡
እውቁ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” በሚል ርእስ ባሳተሙት መፃሐፋቸው ኢትዮጵያን ሲገልጹ፡- “አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል አምባ ተብለው በሚታወቁ ኮረብታማ ቦታዎች የተሞላ ነው፡፡ 4ሺህ 620 ሜትር የሚረዝመውን የሃገሪቱን ከፍተኛ ተራራ ራስ ደጀንን ጨምሮ በባሌ፣ አርሲ፣ ሲዳሞ፣ የሐረር ደጋማ ስፍራዎችን ጨምሮ በርካታ ተራራዎች በሃገሪቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ተራራዎች በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ታላላቅ ጦርነቶች ተካሂደውባቸዋል እንዲሁም በክፉ ቀን የሃገር ቅርስ መሸሸጊያም ኾነው አገልግለዋል” ይላሉ፡፡ እንግዲህ አርበኞች በየዘመኑ የተዋደቁት በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች ነበር ማለት ነው፡፡
አርበኛ ማን ነው?
አርበኝነት ትርጉሙ ምንድን ነው?
የአርበኝነት ታሪካዊ ዳራስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ ማንሳት ዘመኑን የዋጀ ይመስለናል፡፡ ነገር ግን አርበኝነት ከጽንሰ-ሃሳባዊ ትርጉሙ ይልቅ አውዳዊ ትርጉሙ ቢመረመር የተሻለ እንደሚኾን የታሪክ ምሁራን ይስማማሉ፡፡
የታሪክ ጸሐፊው በቃሉ አጥናፉ (ዶክተር) አርበኝነትን ሲበይኑት በዘመነ ፋሽስት አርበኛ ማለት ፋሽስትን የተዋጋ፣ የፋሽስትን ሥርዓት ተቃውሞ ለፋሽስት ሥርዓት እና አገዛዝ ያልተንበረከከና ያላጎበደደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ አርበኛ ነበር ይሉታል፡፡ ነፍጥ አንስቶ፣ ጫካ ገብቶ፣ ጤዛ እየላሰ እና ድንጋይ እየተንተራሰ ለሀገሩ ፍቅር እና ለወገኖቹ ክብር የሚዋደቅ ሁሉ አርበኛ ይባላል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን ህልውናዋ እና ነጻነቷ ቋፍ ላይ ወድቀው ስለነበር አርበኝነት የሚበየነው ለነጻነት ከሚከፈል ማንኛውም የሕይዎት መስዋዕትነት እና ዋጋ ጋር ተሳስሮ ነበር፡፡
ዶክተር በቃሉ የአርበኝነት አውዳዊ ትርጉም ካለንበት ዘመን አንፃር ሲቃኝ ደግሞ በረሃ የወረደ፣ ጫካን የተላመደ እና ከመሳሪያ ጋር የተዋደደ ጀግና ብቻ ማለት ላይኾን ይችላል ይላሉ፡፡ ሰው በጠፋበት ጊዜ በሰዎች መካከል ኾኖ ስለሕዝብ እና ስለሀገር ጥቅም ብልሹ ሥርዓትን በድፍረት የሚሞግት፣ ስልታዊ በኾነ የፖለቲካ ጥበብ ሕዝብን ያነቃ፣ ለግል ጥቅም እና ዝና እጅ ያልሰጠ፣ የሥርዓቱን እንከኖች የነቀፈ፣ የተቸ እና ሥርዓቱን ለማስተካከል ካልተቻለም ለመለወጥ የተጋ ሁሉ አርበኛ ሊባል ይችላል ይላሉ፡፡
የዘመኗ ኢትዮጵያ ልክ እንዳሳለፈቻቸው ጥንታዊ የመከራ እና የፈተና ዘመኖች ሁሉ ዛሬም እንደዚያ ናት፡፡ ፈታኞቿ ከሩቅም ከቅርብም፤ ከውስጥም ከውጭም በዐይን ጥቅሻ ብቻ እየተግባቡ ሕልውናዋን ሲፈታተኑት ይስተዋላል፡፡ የትናንት አርበኞችን ታሪካዊ ዳራ ማጉላት ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ፈተና መሻገሪያ ጉልበት ማድረግ ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አርበኞችን ስናወሳ እና ስናነሳ ትውልድ ለቀጣይ አርበኛ ይኾን ዘንድ ማብቃት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
