አርበኛ ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባደፋር)

506

“እንዳታባብለው ሙታበት እናቱ፣
ደፋር አኮረፈ እንደልጅነቱ”

ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዛሬው ዕለት ሊታወሱ ከሚገባቸው እልፍ ጀግኖች አርበኞች መካከል አርበኛ ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባደፋር) ማን ናቸው?

በፈረስ ስማቸው አባ ደፋር በመባል ይታወቃሉ ቢትወደድ አዳነ መኮንን፤ ትውልዳቸው ጎንደር ወልቃይት ጠገዴ ዓዴት በምትባል ቦታ ነው፡፡ ከአባታቸው ልጅ መኮንን መንገሻ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ብዙነሽ አበበ ሚያዝያ 1888 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ የትውልድ አካባቢያቸው ለአደን በደንብ ይመች ነበርና ቢትወደድ አዳነ መኮንን ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ነበር አነጣጥሮ በመተኮስ ታዋቂነትን ያተረፉት፡፡

ቢትወደድ አዳነ መኮንን በ1918 ዓ.ም የበጌ ምድር ገዥ የነበሩት የራስ ጉግሳ ወሌ ወታደር በመኾን በደብረ ታቦር መኖር ጀመሩ፡፡ በ1923 ዓ.ም በአንቺም ጦርነት ተካፍለው ከራስ ጉግሳ ሞት በኋላ በአዲሱ የበጌምድር ገዥ በደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ ኣዳነ መኮንን የቀኛዝማችነት ማዕረግን ተቀዳጁ፡፡ ከዛም የአርማጭሆ፣ የጃኒፈንቀራ ፣ የያይራ አሥተዳዳሪ ኾነው ተሹመዋል፡፡

በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ቀኛዝማች አዳነ መኮንን ከፊታውራሪ ኃይሉ ፋሪስ፣ ከቀኛዝማች ዓባይ ወልደ ማርያም፣ ከቀኛዝማች መስፍን ረዳና፣ ቀኛዝማች ገብሩ ገብረ መስቀል ጋር በመኾን የወልቃይት-ጠገዴን ሕዝብ በማስተባበርና በመምራት የሰቲት ሑመራና የመተማን በር እንዲጠብቁ በደጃዝማች ወንደወሰን ካሳ ታዘዙ፡፡
አርበኞቹ የመከላከል ግዳጅ ላይ እያሉ በዘመናዊ ጦር መሳሪያና በግዙፍ ሠራዊት በመታገዝ በጄኔራል አቼሌ የሚመራው የጣሊያን ጦር ሑመራን ጥሶ ጎንደር ከተማ ገባ፡፡
ጀግናው የወልቃይት ጠገዴው ሰሜን አርማጭሆዉ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ቀኛዝማች አዳነ መኮንን ከወንድሞቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ኾነው በረኻ ገቡ፡፡ ጣልያን ጎንደርን ከአስመራ ጋር ለማገናኘት በአርማጭሆ በሠሮቃ፣ በዳንሻ፥ በወይንናት፣ በበኻከር፣ በሑመራ በኦም-ሓጀር ወ.ዘ.ተ አድርጎ የመኪና መንገድ በመጥረግ የጦር ካምፑ ዓዲ-ረመጥ፣ ቃብትያ በሚባሉ ቦታዎች አቋቋመ፡፡

ቀኛዝማች አዳነ መኮንን የወራሪውን ጦር ለመመከት የወልቃይት ጠገዴ አርበኞችን በማሰባሰብ የሽምቅ ጦር በማቋቋም የዕብሪተኛውን የኢጣሊያን ጦር መቅሰፍት ኾነበት፡፡ ሚያዝያ 23/1928 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራው ጦር ደብዛ በሚባል ቦታ በደፈጣ ውጊያ በማድረግ በኢጣሊያን ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ከፍተኛ የሆነ ጠብመንጃና ጥይት ማርኮ ታጠቀ፡፡
በጀግናው ቢትወደድ አዳነ የሚመራው የአርበኞች ጦር የጣሊያን ወራሪ በተለያዩ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች እየተከታተለ እረፍት ነሳው። በተደረጉ ጦርነቶች ያልተሳካለት የጠላት ጦር እጅግ ስላስቆጣው ከግዜ ግዜ እየተጠናከረ የመጣው የአርበኞች እንቅስቃሴ ለመደምሰስ በሁለት አቅጣጫ ማለትም በዓዲ ረመጥ በኩልና በወገራ በኩል ወደ አርበኞቹ መናኸሪያ ወደ ነበረችው ዓዴት ዘለቀ፡፡ በዚህም ከባድ ፍልሚያ ድሉ የአርበኞቹ ኾነ።

ይህ ድል በቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራውን የአርበኞቹ ግንባር ትልቅ ዝናና ክብር እንዲያገኝ አደረገው። የጣሊያን ጦር ሽንፈቱን አውቆ ዓዴት፣ ማይገና፣ ቀራቅር፣ ጨጓርኩዶ እና ሌሎች አከባቢዎች ለቆ ለመውጣት ተገደደ፡፡

ጣሊያን በኢትዮጵያ ምድር በቆየባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ደጃዝማች አዳነ መኮንን እና ጓዶቻቸው 56 ግዜ ጥቃት ፈጽመውበታል፤ በዓዴት፣በማይገና፣ በቀራቅር፣ በጨጓርኩዶ፣ በጠለሎ፣ በደጀና፣ በዓዲ ረመጥ፣ በቤተ ሙሉ፣ በአርማጭሆ፣ በጃኖራ ፣በአጅሬ፣ በጭልጋና በወገራ ከፋሽስት ጋር ግብግብ በመግጠም ለድል በቅተዋል፡፡

ፋሽስት ኢጣሊያ ድል ኾኖ ከሀገር ከተባረረ በኋላ 1934 ዓ.ም ደጃዝማች አዳነ መኮንን ከሰሜን ባምብሎ እስከ ተከዜ ጦር አዝማችና አበጋዝ ተብለው በአዋጅ ተሸለሙ፡፡

በ1938 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የወገራ አውራጃ መሪ ኾነውም አገልግለዋል፡፡ በነገራችን ላይ የአካባቢው ጦር መሪነት እና የደጅ አዝማችነት ማዕረግ እስከ 1939 ዓ.ም ሕዝቡ ራሱ ሰጥቷቸው ነበር፤ ከዛ በኋላ ነው በንጉሠ ነገሥቱ የፀደቀላቸው፡፡

• በ1944 ዓ.ም ከወገራ አውራጃ አስተዳዳሪነት ወደ ጭልጋ አውራጃ ተዛውረው አስተዳድረዋል፡፡

• በ1945 ዓ.ም ወደ ወገራ ተመልሰው እስከ 1966 ዓ.ም ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡

• በ1959 ዓ.ም በቀዳማዊ በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የቢትወደድ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡

• ቢትወደድ አዳነ መኮንን የሀገራቸውን ልማት ለማፋጠን ባደረጉት ልባዊ ጥረት ከሰቲት ሑመራ ወደ ጎንደር የተዘረጋውን መንገድና የአከባቢው ልማት ሕዝቡን በማሰባሰብና በማበረታታት ልማቱን መርተዋል።

አርበኛ ቢትወድድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር) ከሌሎች አርበኞች ጋር የፋሽስት ጣሊያን ጦርን በታላቅ ተጋድሎ በማሸነፋቸው እና ሀገራቸውን ነጻ በማውጣታቸው በርካታ ሽልማቶች ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

የደርግ አገዛዝ ያልተዋጠላቸው ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር) በ80 ዓመታቸው በርሃ ገብተው ሸፍተውም ነበር፡፡

የቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር) በእርጅና ዕድሜያቸው በመሸፈታቸው:-

“እንዳታባብለው ሙታበት እናቱ፣
ደፋር አኮረፈ እንደልጅነቱ።”

የሚል ቅኔ የአካባቢው ሕዝብ ተቀኝቶላቸዋል፡፡

አኹንም ድረስ በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ “የደፋር አሽከር” ይባላል።

አባ ደፋር 1975 ዓ.ም አርማጭሆ ዘመነ መሪቅ ላይ ሕወታቸው እንዳለፈ የታሪክ ድርሳናቸው ያስረዳል፡፡

(ምንጭ:-ታማኝ መብራቱ፤ “የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ታሪክ እና ማንነት” (ታኅሣሥ 2006 ዓ.ም) መጽሐፍ)

በየማነብርሃን ጌታቸው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ትዉልዱ ፅንፈኝነትና አክራሪነት ራሱን በልቶ የሚያጠፋ አስተሳሰብ መሆኑን ከፋሺስታዊ አገዛዙ በመማር ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሀገሩን ማፅናት ይጠበቅበታል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Next articleዝክረ ሸዋረገድ ገድሌ – ጀግኒት ኢትዮጵያዊት አርበኛ!