“ትዉልዱ ፅንፈኝነትና አክራሪነት ራሱን በልቶ የሚያጠፋ አስተሳሰብ መሆኑን ከፋሺስታዊ አገዛዙ በመማር ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሀገሩን ማፅናት ይጠበቅበታል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

154

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 81ኛውን የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ጦርነቶችን አካሂዳለች፡፡ ጠላቶቿ የተኙላት ጊዜ የለም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት ፈልጋ እና ተመኝታ፣ የሌላዉን ሉዓላዊነት ጥሳ ወረራ ፈፅማ አታውቅም፡፡

ሁሌም የራሷ በሆነው ሃብት ወይም ሌላ ጉዳይ በጠላቶቿ ትጠቃለች፡፡ ሆኖም ግን ሁሉንም ጦርነቶች በአሸናፊነት አጠናቃለች፡፡ ጦርነቶቹን ያሸነፈቻቸዉ በጠላቶቿ ድክመት ወይም በታጠቀቻቸዉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ብልጫ አይደለም፡፡ ሁሌም ጠላት ሲመጣ በሚሰባሰቡትና ጠላትን በአንድነት በሚመክቱት ጅግኖች ልጆቿ ነዉ፡፡

ሁሌም ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ስትነካ ትዕግስት የሌላቸዉ ዉድ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በደምና በአጥንታቸዉ የአገራቸዉን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ሳይደፈር አስከብረው አቆይተዋታል፡፡

በታሪክ ሁልጊዜ ከሚታወሱት የጀግንነት ታሪካችን አንዱ ከስምንት አስርት-ዓመታት በፊት ለሀገር ክብርና ለሕዝቦች ነፃነት የአባት አርበኞች የፈፀሙት ገድል ነዉ፡፡ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የተደረገዉ የአድዋ ጦርነትና ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መፈፀሙ በወራሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የዉርደት ስሜትና ፀፀት አስከትሏል፡፡ ሽንፈቱ በወቅቱ የበቀል ስሜትን ቀስቅሷል፡፡

ከስሜትም አልፎ የአገዛዝና የአስተሳሰብ ለዉጥን አስከትሏል፡፡ ከነዚህም ለዉጦች መካከል አንዱ የፋሽስታዊ አስተሳሰብ መወለድና የመሪዉ ቤኒቶ ሙሶሎኒ የመንግስት ስልጣን መቆናጠጥ ነበር፡፡ ይህ ፋሽስታዊ ብሔርተኝነትና መሪዉ እንደ ግብ ከያዘዉ አንዱ እና ዋነኛዉ ኢትዮጵያን ዳግም በመዉረር ከሽንፈቱ ድባቴ በመላቀቅ የጣሊያንን ታላቅነት መመለስ የሚል ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ከ40 ዓመት የአድዋ ድል በኋላ ፋሽስታዊ አገዛዙ እ.አ.አ በጥቅምት 1935 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረራት፡፡

በወቅቱ የጠላት ጦር በያዘዉ የጦር መሳሪያና በሰለጠነ የወታደር የበላይነት ምክንያት ለጊዜዉም ቢሆን የወገን ጦርን ለመበተን ቻለ፡፡

ሆኖም ግን ለባርነትና ለጠላት እጅ መስጠጥ የማያዉቁ ኢትዮጵያዉያን ራሳቸዉን በማደራጀት በአዲስ መልክ በጠላት ላይ ተነሱ፡፡ ቀያቸውንና ንብረታቸዉን ትተዉ ዱርና ገደሉን ቤታቸዉ አደረጉ፡፡ እንደ ስሙ የአንበሶች ስብስብ የሆነዉን ‘የጥቁር አንበሳ’ የተሰኘዉን የአርበኞች ስብስብ መሰረቱ፡፡ አርበኞቹ በመላ ኢትዮጵያ በብሔርና በቋንቋ ሳይለያዩ በሁሉም አካባቢዎች በመደራጀትና በመንቀሳቀስ ጠላትን እንቅልፍ አሳጡት፡፡ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ጠላትን እረፍት በመንሳት እ.አ.አ ግንቦት 5/1941 አርበኞቹ የነፃነት ታጋዮች በጠላት ላይ ድል ተቀዳጁ፡፡ ለአምስት ዓመታት አገር ለቀዉ ዉጭ አገር በስደት የቆዩት ንጉሱም በድል ወደ አገራቸዉ ተመለሱ፡፡ ዕለቱም እስከ ዛሬ ድረስ የአርበኞች የድል ቀን በመባል ይከበራል፡፡ ጀግኖች አርበኞችም ለአገራቸዉ ክብርና ለሕዝቦቿ ነፃነት ላደረጉት ተጋድሎ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይወደሳሉ፣ ይታወሳሉ፤ ለዘለዓለም በትውልድ ሲወደሱም ይኖራሉ፡፡

የዘንድሮዉን 81ኛዉ ዓመት የአርበኞች መታሰቢያ ቀን ስናከብር የድሉን ትሩፋቶች በማጉላትና ለትዉልድ በማስተላለፍ መሆን ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ ከሩቅና ከቅርብ በታሪካዊ ጠላቶቿ ስትጠቃና ስትወረር ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ምንም እንኳን ፈልጋ የሰዉን ሀገር ወራ ባታዉቅም ጠላቶቿ አልተኙላትም፣ አይተኙምም፡፡ ሆኖም ግን በሕዝቦቿ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸዉ ሉዓላዊነቷና የሕዝቦች ነፃነት ተጠብቆ ይቀጥላል፡፡ ዛሬም አገራችን ከቅርብና ከሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቿ በሚሰነዘርባት ሁለንተናዊ ጥቃት ሳትንበረከክ ልጆቿ ከአባቶቻችን በወረሱት የአገር ፍቅር ለሕዝቦች ክብርና ለአገር አንድነት ዘብ ቆመዋል፡፡

መጪዉ ትዉልድም ለጋራ ሀገሩና ለክብሩ በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እንደሚያሸጋግራት ጥርጥር የለዉም፡፡

የፋሽስቱ አገዛዝ እንደ ወሳኝ የማሸነፊያ መሳሪያ ተማምኖ የነበረዉ በታሪክ “ፋሺዝም” ተብሎ የሚታወቀዉን ጫፍ የረገጠ ፅንፈኝነትና አክራሪነትን ነበር፡፡

ትዉልዱ ፅንፈኝነትና አክራሪነት ራሱን በልቶ የሚያጠፋ አስተሳሰብ መሆኑን ከፋሺስታዊ አገዛዙ በመማር ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሀገሩን ማፅናት ይጠበቅበታል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleሰንደቋ ከፍ ብሎ በነፃነት ምድር የተውለበለበበት ቀን ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም!
Next articleአርበኛ ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባደፋር)