
ባሕር ዳር : ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠላት ሲወርህ በቀላሉ አይተውህም፤ ማቅ ያስለብስሃል፤ የአንተነትህን ዓርማ አስወልቆ የውርደት ካባ ያስለብስሃል፡፡ ለዚህ ውርደት ከተንበረከክ ያንተን ክብር አውልቀህ የገዥህን ዓርማ በገዛ ፈቃድህ እንድትሰቅል ግድ ይኾንብሃል፡፡
አዎ ኢትዮጵያ በታሪክ ምዕራፍ ልጆቿ መቼም ቢኾን አሳፍረዋት አያውቁም፤ ለክብሯ ሲዋደቁ ኖሩ እንጅ፣ ጠላቶቿ መቼም ቢኾን ተኝተውላት የማታውቀው ኢትዮጵያ የማይሸነፉ ልጆች ስላሏት መቼም ቢኾን አንገቷን ደፍታ ዓርማዋን ዘቅዝቃ የሌሎችን ዓርማ በምድሯ እንዲቆም ፈቅዳ አታውቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ የማያሳፍሯት አርበኞች ልጆቿ ሁሌም አሉላትና ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታቱ የጣሊያን እና የወዳጆቿ ወረራ ወቅት ተፈትናለች፤ ልጆቿም ዓርማዋን ይዘው በዱር በገደሉ ተዋድቀው ክብሯን አስመልሰዋል፡፡ ትዕቢት የወጠረው የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኀይል ዓርማዋን ለማስጣል ልጆቿን በባርነት ቀንበር ለማሰር ያላደረገው ያልቆፈረው ጓዳ ጎድጓዳ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጅ አርበኞቹ የብርታታቸው የጽናታቸው መነሻ የኾነችውን ሰንደቅ ይዘው ታግለው ጠላትን አሳፍረዋል፡፡
ማርሻል ባዶሊዮ ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩን የኢትዮጵያ የክብር ሰንደቅ ዓላማ አስወርዶ፣ ቀይ-ነጭና-አረንጓዴውን ባንዲራ ሰቀለ። ይሁን እንጅ ሰንደቃቸው የወረደባቸው የአራቱም ማእዘናት የኢትዮጵያ ልጆች ይህን ውርደት በጸጋ ሊቀበሉ አልቻሉም፤ ከዚህ ይልቅ ሞትን ሞተው ሰንደቋን ወደነበረበት መመለስ ምርጫቸው አደረጉ፡፡
“አርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው፣
ታላቁ አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው፤” ሲሉም ተቀኙ፡፡ ትግሉ ተፋፋመ ለሰንደቋ ክብር የሚዋደቀው አርበኛ በየአቅጣጫው ለጠላት የጣሊያን ዘመናዊ ጦር የእግር እሳት መኾናቸውንም ቀጠሉ፡፡ ለክብር ሲሉ ጠላትን እየቀሉ ሰንደቋን ለብሰው የሚሰው ተበራከቱ፡፡ ይህን ጊዜ ጠላት የማይወጣው እዳ ውስጥ መዘፈቁን ተረዳ፡፡ የገመተው እና ያቀደው እቅድ በቀላሉ እንደማይሳካ ተረዳ፡፡ የኾነ ኾኖ ጠላት የአርበኞቹ በትር ሲበዛበት የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከጀግኖቹ ቀየ መልቀቅ ግድ ኾነበት፡፡
ታዲያ የሰቀላትን ዓርማ አውርዶ ለመውጣት ግድ ኾነበት፡፡ በደማቸው ሰንደቃቸውን ያስከበሩት፣ ክብራቸውን ያስመለሱት አርበኞቹ ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም የዛሬ 81 ዓመት ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ተቀበሉ፤ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት ዓደባባይ ላይ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩን ሰንደቅ ዓላማቸውን መልሰው ሰቀሉት፡፡
የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አስር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት ከቦ ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቋ በክብር ከፍ አለች፡፡ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ነፃነት ትንሳዔና የመላ ሕዝቦቿም ድል አድራጊነትም በሰንደቋ ተረጋገጠ፡፡ የፋሺስት ኃይል ኢትዮጵያን ወረረ እንጂ ከቶ ኢትዮጵያውያንን ሊገዛ አልቻለም፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ባለፉት ክፍለ ዘመናት እንዳደረጉት ሁሉ፣ እንደ ሽምብራ ኩሬው፣ እንደ ዶጋሊው፣ እንደመቅደላው፣ እንደ መተማውና እንደ ዓድዋው ሁሉ የትግሉን ምዕራፍ በማያዳግም ድል ዘጉት፡፡ ሰንደቋም መቸም ላትወርድ በክብር ልጆቿ ከፍ አለች፡፡
ዛሬም ይህችን ሰንደቅ ለማውረድ እና ኢትዮጵያውያንን ለማዋረድ በውስጥ ባንዶች በኩል በጥንት ጠላቶች የሚደረገው ሙከራ መቀጠሉ አልቀረም፤ የማትሰበረው ሀገር በልጆቿ ከብሯን እና ሰንደቋን እያስከበረች ከፍ ማለቷን ቀጥላለች፡፡ ዓርማዋንም በተፈጥሮ በታደለችው ተራራ እና ኮረብታ ላይ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረጓንም ቀጥላለች፡፡ መልካም የአርበኞች ቀን በዓል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ