
አዲስ አበባ ፡ ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ81ኛው ዓመት የድል ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ሙሉ መልእክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል:-
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቱ ለማድረግ በ1888 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ ወረራ አካሂዷል።
ይህን ተከትሎም ጀግኖች ቅድመ አያቶቻችን ከዳር ዳር ተጠራርተው ወደ ሰሜን በመትመም ለሀገር ክብርና ጥቅም ሲሉ በአንድነት ተዋድቀዋል፤ አጥንት ደማቸውን ከስክሰው ና አፍስሰው በከፈሉት የሕይወት መስዋእትነት አንድነቷ የተጠበቀ ነፃ ሉዓላዊ ሀገር አስረክበውናል። በአንድ ቀን የጦር ሜዳ ውሎ ጀግኖች አባቶቻችን ባደረጉት የአርበኝነት ተጋድሎ የጣልያንን ተስፋፊና ወራሪ ኃይል ዓድዋ ላይ ድል አድርገው፤ አይቀጡ ቅጣት ቀጠው አሳፍረው መልሰውታል።
ዓድዋ ላይ ሽንፈት ያጋጠመው ፋሽስት ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን ለመውረር ተዘጋጀ። የምዕራቡ ዓለም ከደረሰበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት የተፈበረኩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እስከ አፍንጫው የታጠቀና እጅግ የሰለጠነ ዘመናዊ ጦር ይዞ መጣ፤ በዓለም አቀፍ ሕግ ደረጃ የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ጭምር በ1928 ዓ.ም. ሀገራችንን ዳግም ሊወር ችሏል።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር የመጣው ለኢትዮጵያና ሕዝቧቿ ጥቅም አልነበረም፤ ይልቁንም በዓድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈትና አሳፋሪ ጠባሳ ለመሰረዝ፤ ኢትዮጵያን ለመበቀልና ህዝቦቿን ለማዋረድ ነበር።
አልተሳካለትም እንጂ!
ፋሽስት ጣሊያን በአምስት ዓመት ቆይታው በየካቲት 12፣ 1929 ዓ.ም. ያካሄደውን አረመናዊ ጭፍጨፋን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል ፈፅሟል።
ኢትዮጵያውያንን ለማምበርከክና ነፃነታቸውን ለመንጠቅ የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም እንዳሰበው አልሆነም ።
በየአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን እናት አባት አርበኞች ነፍጥ አንግበው ፤ ጎራዴ ስለው፤ ዱር ቤቴ ብለው በዱር በገደሉ ረሃብና ቸነፈር ሳይበግራቸው ፋሽስት ጣሊያንን መግቢያና መውጫ አሳጥተው ታግለውታል። በአርበኝነት ተዋድቀው ጠላትን ከሀገር አባረው ለድል ቀን በቅተዋል፤ ከ5 ዓመት የአርበኝነት ትግል በኋላም አዲስ አበባን በመግባት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዛሬዋ ዕለት ሚያዚያ 27ቀን 1933 ዓ.ም ሊሰቀሉ ችለዋል።
ሀገር በየጊዜው በሚፈጠሩ ጀግኖቿና አርበኞች ልጆቿ አንድነቷ ፀንቶ፣ ነፃነቷ ተጠብቆና ዳር ድንበሯ ተከብሮ በትውልድ ቅብብሎሽ እነሆ ከዚህ ደርሳለች።
የአሁኑ ትውልድም ጊዜው የሚጠይቀውን የአርበኝነት ስራ በመስራት የራሱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።
የእናት አባቶቹ ታሪክ ወራሽ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የራሱን ታሪክ በመስራት ሀገራችን ኢትዮጵያ የበለፀገች፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የስራ መስክ ሁሉ ለሀገር ክብርና ጥቅም የልማት አርበኛ ሊሆን ይገባል።
እናቶቻችንና አባቶቻችን ጊዜው የሚጠይቀውን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ነፃነቷና አንድነቷ
የተጠበቀ ሀገር አውርሰውናል። እኛም ዘመኑ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በመክፈል ከድህነት የወጣች የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ተግተን መስራት ይኖርብናል።
ዘላለማዊ ክብር ለእናት አባት አርበኞች!
እንኳን አደረሳችሁ! አደረሰን!
መልካም የድል ቀን!
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/