‘‘ምን ዓይነት ወኔ ነው፤ ምን ዓይነት ድፍረት መድፍ የጨበጠውን በድንጋይ መምታት!’’

245

እንኳን ለጀግኖች አርበኞች የድል ቀን መታሰቢያ አደረሳችሁ!

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ‘ኳኳኳ …’ የሚል የማያባራ ድምጽ፤ ቀይ ደም እየተፋ የሚያቃስት የሰው ድምፅ፣ ‘በለው! ውጋው! አይዞህ!’ እያለ የሚዋጋና የሚያዋጋ የጀግና ድምፅ፤ ‘‘ደረቱን ውጋው! ጣለው ገርስሰው!’’ የሚል አስደንጋጭ ድምጽ፡፡ እየፈለቀ የጠላት አንገት የሚቀነጥስ ነጭ ጎራዴ፤ ነገሩ ሁሉ ሕልም ይመስላል፡፡

ለማሰብ የሚከብድ ግፍ፣ ሬሳ በሬሳ ላይ ሲደራረብ ልብ ያሸብራል፡፡ አርበኝነት፣ አንድነት እና ፅናት የኢትዮጵያውያን ምልክት ናቸው፡፡
በአርበኞቻችን ተታኩሰናል፣ ጎራዴ መዝዘናል፣ ሳንጃ ስበናል፣ በአንድነት ቆመን ተዋግተናል፤ ታግለን ገፍተን ከምድረ ርሰት ጠላትን አስወጥተናል። በፅናት አሸንፈን ተከብረናል።

አርበኝነት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን መሠረት ነው። ደም ጎርፍ ቢሆን ኢትዮጵያ አፈር አይኖራትም ነበር። አጥንት የሚበቅል ቢሆን ኖሮ ትርፍ መሬት ባልተገኜ ነበር። የአጥንት ዛፍ ሁሉ በአገሩ ቢበቅል የቤት መሥሪያ ቦታ ባልተገኜ ነበር፡፡ ነገር ግን የፈሰሰው ደም ነፃነት፣ አንድነት፣ ፍቅር እና ሰላም ሆነና ደም ያፈሰሱ አርበኞች ልጆች ተንፈላሰው ኖሩ፡፡
ኢትዮጵያ በአርበኝነት የተጠበቀች፣ በፈጣሪዋ አደራ የተሰጠች፣ በደም ተለውሳ በማይወድቅ አጥንት የተገነባች የአለት ላይ ጎጆ ናት፡፡

ጠላት በአራቱም ማዕዘን ይጎርፋል፤ ድንበር ዘልሎ ይገፋል፡፡ አርበኞቻችንም ይተኩሳሉ፤ አፈር አስልሰው ድንበራቸውን ያስመልሳሉ፤ ከጋራው ማዶ ጠላትን አፈር ያለብሳሉ፡፡ አርበኝነት ለኢትዮጵያውን ዘር እና ማንነት ነው፡፡ በዘመን ሽግግር ሁሉ የዘመናቸው አርበኞች እልፍ አዕላፍ ናቸው፡፡ የነገዋን አገራቸውን እያሰቡ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጎሮሮ ግብ ግብ የገጠሙ ሁሉ ለዘመናት ይታሰባሉ፡፡ የዓድዋው ጮራ የአርበኝነት ውጤት ነው፡፡ የጉንደት እና የጉራው ድል አርበኝነት ነው፡፡ የአምስት ዓመቱ ድል የአርበኝነት ውጤት ነው፡፡ አርበኝነት ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ መግለጫ ከጭቁንነት መውጫ በርም ነው፡፡ አርበኝነት በኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪክ ሁሉ አብሮ የመጣ፣ ያለ የሚቀጥልም ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአምስት ዓመቱን የጣልያን ወረራ ወቅት አሻፈረኝ ብለው የተጋደሉትን አርበኞች ታስባለች፡፡ ነገር ግን አርበኝነት በዚያ ዘመን ብቻ ነው የተጀመረው ወይም ከዚያ በፊት የነበሩት ከዚያ በኋላም የመጡት እና የሚመጡት አይታሰቡም አይከበሩም ማለት አይደለም፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ላይ ልትፍቀው የማትችለውን የታሪክ ኪሳራ ከደረሳበት በኋላ ለ40 ዓመታት ዶለተች፡፡ የጠፋውን ስሟን ለማደስ ኀይሏን አጠናክራ ኢትዮጵያ ረገጠች፤ ከፍተኛ እልቂት ተፈጠረ፤ ምድር ቁና ሆነች፡፡ የግፍ ግፍ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጸመ፡፡

‘‘ማንነቴን አልሸጥም፤ ኢትዮጵያዊነቴን አልለውጥም’’ ያሉት ጀግኖች አርበኞችም ጦር ሰበቁ ከጠላት ጋር ተዋደቁ፡፡ ለ40 ዓመታት የተዶለተበት የቀኝ ግዛት ዘመቻ እንደ ዓድዋው ሁሉ በአንድ ጀንበር አልተመለሰም፡፡ ቀናቶች እየረዘሙ ሄደው፤ ወራቶች አለፉ፣ ዓመታትም ተቆጠሩ፡፡ ግርማዊ ቀደማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ የጣልያንን ጦር እስከ ግንባር ሄደው ተዋጉ፤ ነገሩ በቀላሉ የሚፈታ አልነበረምና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ወደለንደን አቀኑ፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነ፤ ሰብሳቢ ጠፋ፣ አዋጊ መንግሥት ያጡት አርበኞች ‘ዱር ቤቴ’ ብለው ከጠላት ጋር እየተዋደቁ ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዕርዳታ እየጠዬቁ ከአርበኞች ጋር ደብዳቤ ይጻጻፉ ነበር፡፡ አርፎ የሚተኛ አልነበረም፡፡ የእግር ጉዞ ባያደክማቸው ዘመናዊ መሣሪያ ቢኖራቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞች አይደለም ኢትዮጵያ የምትባለውን ምድር ጥቁር የሚኖርበትን የአፍሪካን አህጉር ነፃ የማውጣት ወኔ እንደነበራቸው ይነገራል። አይደለም የተኮሱት ጥይት የወረወሩት ድንጋይ የሚያርፈው ከጠላት ላይ ነበርና።

‘‘አርሶ መራብና ተኮሶ መሳት፣ ያቃጥል የለም ወይ እንደ እግር እሳት’’ እያሉ የተኮሱትን ጥይት ሳያባክኑ በአግባቡ ተጠቀሙበት፡፡

የጣልያን ወታደር ቤተ ክርስትያን የሚያቃጥል፣ ሽማግሌ የሚገድል፣ ሴቶችን የሚደፍር እና የሚያዋርድ፣ ንብረት የሚዘርፍ፣ ደም በከንቱ የሚያጎርፍ ጠላት ነበር። ይህን ክፉ ወታደርም አርበኞች ‘‘በለው በለው አትለውም ወይ፣ የቄሳር መንግሥት ሊገዛህ ነው ወይ? ጥቁር አንበሳ አይደለህም ወይ?’’ እያሉ ከገጠጠው ጦርነት በጦር በጎራዴ ግራና ቀኙን እየጣሉ ይገቡ ነበር።

የጣልያን ወታደር ተስፋ ቆረጠ፤ ሞሶሎኒ ዓይኑ ፈጠጠ፤ ‘‘ኃያሏን ጣልያን ማንም አይበግራትም’’ እያለ ሲዝት የነበረው ሁሉ በጭንቀት አንገቱን ደፋ፡፡ አምስት ዓመታትን በጥይት ተጠብሶ እንቅልፍ ሲያጣ ሮም ላይ የቀመራት የቅኝ ግዛት ቀመር በጥይት ተቆልቶ አርሮ አልቆረጠም ሲል ያመለጠው ፈረጠጠ፤ የቀረው እጅ ሰጠ። ብዙው ደግሞ በአርበኞች ጥይት እየተለቀመ በዱር በገደሉ ቀረ። ኢትዮጵያንም በፍቅር እንጂ በፀብ ላይደፍር እየማለ ሸመጠጠ። የጣልያን ወታደር ከኢትዮጵያ ምድር ወጥቶ ለማምለጥ ሌት ከቀን ይጓዝ ነበር፡፡ አርበኞች ደግሞ ከኋላ ኋላ እየተከተሉ ድባቅ ይመቱት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አንድ የቋራ አርበኛ እንዲህ ሲል ሸለለ ብለው ገሪማ ታፈረ ጽፈዋል፤ ‘‘ተጉዞ ተጉዞ ነጭ እንደዳመና፣ መመለሻው ጠፋው ያገሩ ጎዳና፡፡ ተግዘህ ተግዘህ እንደበርበሬ ፍል፣ ወዴት ትሄዳለህ እዳህን ሳትከፍል?’’ የጠላት ከሀገር መውጣት ብቻ ለእርሱ በቂ አልነበረም። በቆዬባቸው ጊዜያት ላጠፋው ጥፋት ካሳም መክፈል ነበረበት እንጂ። ካሳውም የደም ካሳ ነው፡፡

የአምስት ዓመቱን የጭንቅ ዘመን በዓይናቸው ያዩት ገሪማ ታፈረ ‘ጎንደሬ በጋሻው’ በሚለው መጽሐፋቸው ‘‘ብርቱ ነገር ነው ነፃነት ማጣት የሚያመጣው መከራና ጭንቅ፣ ውርደትና ጉስቁልና፣ መገፋት፣ መንገላታት እና መንከራተት ነው፡፡ ነፃነት የሌለው ሕዝብ ሰብሳቢና ጠበቂ ስለሌለው ፍዳው ይበዛል፤ ከሰው ልጅ ኑሮ ማኅበራዊነት ወጥቶ እንደአራዊነት እንደ እንስሳም ይሆናል። በዚህም ጊዜ ከሰውነት ውጭ ሆኖ መገኜት ስላለበት የፆም እና የጸሎት ጊዜዎች፣ የሀገር ልማዶች፣ መያዣና መጨበጫ ይጠፋባቸዋል። ርሃብና ውሃ ጥም መራቆትም ሲበዛ ያገኙትን መጠጣት፣ መልበስ፣ ግድም ነው። ይልቁንም የሚላስና የሚጎረስ፣ ከሰውነት ላይ የሚለበስ፣ ከመጥፋቱ የተነሳ ሙትት ድርቅ ብሎ መቅረትም የግድ ነው። ይኸውም የሚመጣው በሀገር ላይ ጠላት በወራሪነት ገብቶ ነፃነት ሲደመሰስ ባንዴራህን ጥሎ በሀገርህ በቤትህ፣ በርስትህ፣ በንብረትህ፣ በሰውነትህም ሳይቀር ሲያዝበት እና አንተም ቅንጣት መብት የሌለህ የባዕድ መንግሥት ባሪያ እና ተገዥ ትሆናለህ።

ስለዚህ ነፃነት ማጣትን እንደሌላ ነገር መቁጠር በአንተና በልጅ ልጅህ በጠቅላላው በሚከተለው ተከታታይ ትውልድህ ነፃነት ከማጣቱ በፊት ሞቴን ያድርገው ማለት አለበት።’’ ይላሉ፡፡

አርበኛው ሳይሰለች ሳይደክም ተኮሰ፣ ጠላትም በጥይት እየተጠበሰ ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡ ኢትዮጵያውያንም ዳግም ድል ዳግም ገናናነት በሕልመኛዋ ጣሊያን ላይ ተቀዳጁ፡፡ የሮም ጉልበት ተንኮታኮተ፣ የኢትዮጵያ አቅም ደግሞ ጎለበተ፣ ሮም አፈረች ኢትዮጵያ ደግሞ ኮራች፡፡ የሮም ወታደሮች አቀረቀሩ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ፎከሩ፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን አደነቀ፡፡ ይህችስ ጀግና የወለደች የማትደፈር እናት ሲል በአንድ ድምጽ አመሠገናት፤ አከበራት፡፡

እነዚያ የክፉ ቀን ልጆች ሚያዚያ 27 የወረደችውን ባንዴራቸውን ሚያዚያ 27 ዳግም ሰቀሏት፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከልብ ላይ ያልወረደች አርበኞች ሁሉ ድል በመቱበት የጦር አውድማ ሁሉ ከፍ ብላ ስትውለበለብ የኖረች ነበረች፡፡ ያቺ ታላቅ ቀን እነሆ ዛሬ ትከበራለች፡፡ ክብር ለጀግኖቻችን፣ አንድት ለሕዝባችን ዘላለማዊ ማሸነፍ ለኢትዮጵያችን! ።

ክብር ለጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች !

(ተጨማሪ መረጃ፡- የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት በጳውሎስ ኞኞ)

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“እኛ ቤት ሁሉም ስደት ላይ ናቸው” የባይቶና ዓባይ ትግራይ የውጭ ጉዳይ ኀላፊ ክብሮም በርሀ
Next article“እንደሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነጻ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን