የዳንጉርና ጃዊ ወረዳ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር በቅንጅት እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡

333

ሚያዝያ 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙት የዳንጉርና ጃዊ ወረዳ ነዋሪዎች የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር በቅንጅት እንደሚሠሩ ባካሄዱት የሰላምና የአንድነት መድረክ ላይ ገልጸዋል።

በዳንጉር ወረዳ ማንቡክ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ደግአረገ መኩሪያ ቀጣናው ከኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመኾኑ የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ለማወክ ሰርገው የሚገቡ አካላት በተደጋጋሚ ይከሰታሉ ብለዋል።

ግጭት ጠንሳሽ የኾኑ አካላት የብሔር ግጭት እንዲፈጠር ሴራ ከመሥራትም አልፈው ነዋሪው በወረዳና በቀበሌ ጭምር ተከፋፍሎ እርስ በእርስ እንዲጋጭና ተረጋግቶ እንዳያለማም ጥረቶችን እንደሚያደርጉ አቶ ደግአረገ ነግረውናል።

“ግጭት ቀስቃሽ የኾኑ አካላት በሚያናፍሱት ከፋፋይ የሀሰት ወሬ እኛ ነዋሪዎች አንደናገርም” ብለዋል።
የሁለቱም አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች ፀጉረ ልውጥ እና ለሰላም ስጋት የኾነ አካል ሲመለከቱም በንቃት ተከታትለው ለፀጥታ አካል በማቅረብ በአንድነት እና በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ ነው የሚገልጹት።

የጃዊ ወረዳ ነዋሪው የሀገር ሸማግሌ አቶ አበባው አዝመራው በበኩላቸው እኩይ ተግባር ባላቸው አካላት የሚሞከሩ የፀጥታ ችግሮች እንዲከስሙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነግረውናል። የሀገር ሽማግሌዎች ከሁለቱም ክልል እና ወረዳ የሥራ ኀላፊች ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ነወሪዎች ወደ ልማት እንዲሠማሩ እየተደረገ እንደኾነም አቶ አበባው ተናግረዋል።

የሁለቱ አጎራባች ወረዳዎች የጠነከረ ሕዝባዊ ትስስር የፈጠረው ሰላም በቀጣናው ለሚካሄደው የእርሻ ሥራ ውጤታማነት እንዳገዛቸውም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በምክትል ቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሥራ ኀላፊ አቶ ካሳሁን አዳነ የመተከል እና የአዊ ዞን ሁለቱን ክልሎች የሚያስተሳስሩ አካባቢዎች እንደኾኑ ገልፀዋል። ቀጣናው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገኛ በመኾኑ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ትኩረት የሚስብ መኾኑንም አመላክተዋል።

አቶ አዳነ የአካባቢውን ሕዝቦች በዘር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በወረዳና በጎጥ የመከፋፈል ህልም ይዘው የሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

የእነዚህ አካላት ህልም እንዳይሳካም የሁለም ክልሎች ሕዝብና የሥራ ኀላፊዎች በንቃት እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።

የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፀሀይ ጉዩ በበኩላቸው በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ እና በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አጎራባች አካባቢዎች በተወሰነ ደረጃ የፀጥታ ችግር እንደነበር ገልፀዋል። የእርስ በርስ ግንኙነቶችን በማጠናከርና ሰላምን በማስጠበቅ በአካባቢው ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል።

የአማራ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በልማት ዘርፍ ላይ በፈረሙት የጋራ ትብብር ሰነድ መሰረት ጽሕፈት ቤት ተዋቅሮ እየተሠራ መኾኑ ውጤት እንዳመጣም ገልጸዋል።

ግጭቶችን ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላትን በመከታተልና በመቆጣጠሩ በኩል የሕዝቦች አንድነት ከፍተኛ ሚና እንደነበረውም አቶ ፀሐይ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“በሕዳሴው ግድብ እና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ከሽፈዋል” የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር
Next articleአብን ኢትዮጵያዊያን ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ የማዕቀብ ሕጎችን በጋራ እንዲቃወሙ ጥሪ አቀረበ፡፡