
ሚያዝያ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሏህ ደስ ይለው ዘንድ በታላቁ በዓል ታላቅ ነገር አድርግ። መነሻና መዳረሻ የሌለው፣ የማይመረመር ረቂቅ የኾነ ፈጣሪ መልካም ነገርን ይወዳል፣ ክፉ ነገርን ይፀየፋል፣ የሚወዳቸው፣ በሕግና በትዕዛዝ የሚጠብቃቸው ባሮቹ ቀጥተኛውን መንገድ ይከተሉ ዘንድ ያዝዛል። ትዕዛዛቱን የጠበቁለትን ጀነትን ያወርሳቸዋል፣ ከትዕዛዙ የወጡትን ይቀጣቸዋል። ለመልካሞቹ ጀነት ክፍት ናት፣ ለክፉዎቹ ግን ጀነት ዝግ ናት፣ በሯም በእሳት የምትጠበቅ ናት።
አንቺ የንጉሥ ነጋሽ (የአልነጃሽ) ሀገር፣ ታላቁ ነብይ ነብዩ መሐመድ ተስፋ የጣሉብሽ ምድር፣ አትንኳት፣ አክብሯት፣ እርሷ ሰላምና ፍትሕ የሰፈነባት፣ ኹሉም በእኩልነት የሚኖርባት ናት ያሉሽ። ቅዱሳት መጻሕፍት እየደጋገሙ የሚጠሩሽ፣ ደግነትሽን፣ የተስፋ ምድርነትሽን የሚመሰክሩልሽ ፣ መድረሻ ያጡት የሚጠለሉብሽ፣ የራባቸው የሚመገቡብሽ፣ የጠማቸው የሚጠጡብሽ፣ የታረዙት የሚለብሱብሽ፣ የጭንቁን ቀን የሚያልፉብሽ፣ ጨለማውን አሳልፈው ብርሃን የሚያዩብሽ፣ ያዘኑት የሚረጋጉብሽ ድንቋ ምድር።
በዚያ በረሃ በሚበዛበት፣ ቃጠሎው በሚጠነክርበት በመካከለኛው ምሥራቅ የአሏህ መልዕክተኛ ነብዩ መሐመድ መልካሙን ነገር ያደርጉ ዘንድ ተነሱ። ለመልካም ነገር የተላኩት ታላቁ ነብይ መልካም በሌለባት ምድር የአላህን ቃል ይፈፅሙ ዘንድ ወደዱ። በዚያም ጊዜ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ ፣ መሳፍንቱ በተነሱት የአላህ መልዕክተኛ ተግባር ተደናገጡ ። ለእውነት የተነሱ ናቸውና የዚያ ዘመን ነገሥታት ጠሏቸው፣ ያሳድዷቸውም ጀመር። አላህ የእውነት ነብይ እንደላከላቸው የተረዱት የመካ ሰዎች ነብዩን በፍፁም ፍቅር ተከተሏቸው። አብዝተውም ወደዷቸው። ነገሥታቱ ግን በተከታዮቻቸውም እንግልት አደረሱባቸው። ለእውነት የተጓዘ ኹሉ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይኾንም እና መከራ በዛባቸው። እነርሱ ግን መከራውን ለመቀበል ተዘጋጁ።
ነብዩ መሐመድም እውነታቸው የነገሥታቱን ልብ አለዝቦ እንደሚቀበሏቸው ያውቁ ነበርና ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ ፍትሕ ወዳለባት፣ ሰው ኹሉ በእኩልነት ወደ ሚኖርባት ሀገር ይሔዱ ዘንድ አዘዟቸው። የነብያቸውን ትዕዛዝ የሰሙት መልዕክተኞችም ፍትሕ ወደ አለባት፣ ፈጣሪ ወደ ሚጠብቃት፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ወደ ሚኖርባት ሀገረ ኢትዮጵያ በረሃውን አቋርጠው መጡ። ፍትሕ ያለባት፣ ሕዝቦቿ እንግዳ እግር አጥበው፣ ከመሶቡ እንጀራ አውርደው ስሞት እያሉ አጉርሰው፣ ከአልጋ ወርደው አስተኝተው የሚያስተናግዱ ነበሩና የነብዩ መሐመድን መልዕክተኞች በፍቅር ተቀበሏቸው ። በመልካምነት አስተናገዷቸው። በተወደደችው ሀገራቸው ይኖሩ ዘንድ ፈቀዱላቸው።
እውነትም ሰው ኹሉ በእኩልነት የሚኖርባት፣ ፍትሕና ፍቅር የሰፈነባት፣ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ የበዛባት መኾኗን ተረዱ። ከጭንቀታቸው ተገላገሉ። በተወደደችው ሀገር በፍቅር ኖሩ።
ኢትዮጵያዊነት እንግዳ ተቀባይነት ፣ ኢትዮጵያዊነት መልካምነት፣ ኢትዮጵያዊነት አንድነት ፣ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት ፣ ኢትዮጵያዊነት እኩልነት ፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ፣ ኢትዮጵያዊነት አይደፈሬነት ነው። ኢትዮጵያን ኹሉም ይመኟታል። በታሪኳ መድመቅ፣ በምስጢሯ መርቀቅ የሚሹ በመብራት ይፈልጓታል። እግራቸው እስኪነቃ እየተጓዙ ያስሷታል፣ ባሕር እየሰነጠቁ፣ የብስ እያቋረጡ፣ በረሃና ሀሩሩን፣ ዝናብና ብርዱን እየተቋቋሙ ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛሉ።
ቅዱሳት መጻሕፍት የሚጠሯትን፣ ታሪክ የሚያከብራትን፣ የማይደበዝዝ ብዕር የቀረፃትን፣ የማያረጅ ብራና የመዘገባትን ኢትዮጵያን ለማየት የሚጓጉላት ብዙዎች ናቸው። ቀዳሚነቷን፣ ኃያልነቷን፣ በረከቷን፣ የማይሹ ደግሞ ኢትዮጵያን ይጠሏታል፣ ታሪኳን ለማጠልሸት ይጥራሉ ። ዳሩ ኢትዮጵያ ኃያል ናትና ታሪኳን ከፍ አድርጋ፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረች ትቀጥላለች እንጂ።
ነብዩ የሚወዷት፣ ተስፋ ያደረጉባት፣ እምነትም የጣሉባት፣ መልዕከተኞቻቸውን የላኩባት ኢትዮጵያ ከፍ ያለች ናት። ይህች እስልምናን እና ክርስትናን በአንድ ጥላ ሥር ያኖረች፣ በፍቅርና በአንድነት የከበረች ኢትዮጵያ ልዩ ናት።
ነብዩ ሃይማኖታቸውን በፅናት አስተማሩ። ችግሩን ችለው ለፍትሕ ለእኩልነት፣ ለአንድነት ተጉ። ነብዩ መሐመድ ከአላህ የተቀበሉት የእስልምና ሃይማኖት ዓለምን አዳረሰ። በዓለም ላይም አዲስ ነገር ይዞ መጣ። ሲያሳስዷቸው ከነበሩት ወገን የነበሩትም ተቀበሏቸው። አከበሯቸው። ታላቅ ሃይማኖትም ኾነ እስልምና። ሕግና ሥርዐትንም አደረጉ። አስተምህሮቶችንም አስቀመጡ። በጭንቅ ቀን መልእክተኞቻቸውን የተቀበለችውን ታማኟንና መልካሟን ኢትዮጵያን አብዝተው ወደዷት። አከበሯት። እርሳቸውን የሚወድና ትዕዛዛቸውን የሚጠብቅ ኹሉ እንዲወዳት፣ እንዲያከብራት አዘዙ። ቃልም አሠሩላት።
ነብዩ መሐመድ በእስልምና ሃይማኖት አስተምሕሮ ካዘዙት ትዕዛዝ መካከል ታላቅ ክብር የሚሰጠው የሮመዳን ፆም አንደኛው ነው። ሮመዳን ሙስሊሞች ለአሏህ ምሥጋና የሚያቀርቡበት፣ በፆምና በዱዓ የሚተጉበት፣ ለመልካም ነገር የሚተጉበት፣ እዝነት የሚያደርጉበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ መልካም አስተምህሮዎችን የሚፈፅሙበት ታላቅ ወር ነው። ከአንድ ወር አምልኮ እና ራስን መግዛት በኋላ ለአላህ የከበረ ምሥጋና የሚያደርሱበት፣ ታላቁንና የተቀደሰውን ወር የሚፈፅሙበት፣ ዱዓቸውን የሚያሳርጉበት፣ ከአላህ ዘንድ ታላቅ በረከትን የሚቀበሉበት ኤዳል ፍጥር ወይም ዒድ አልፈጥርን በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዐት ያከብራሉ።
ሙስሊሞች በረመዳን የተቀደሱ ተግባሮቻቸውን ይፈፅማሉ። በዚህ ቅዱስ ወር ይቅርታ ይጥቃሉ፣ ይቅርታ ያደርጋሉ፣ ቁርዓን ይቀራሉ፣ ቁርዓንን ይረዳሉ፣ ከመጥፎ ተግባራት ይርቃሉ፣ ከአሏህ ምህረትን ይለምናሉ፣ ከአሏህ ምህረትን በመጠየቅ ሪዚቅ ያገኛሉ፣ አሏህን አብዝተው ይፈራሉ፣ የአክብሮት ሶላት ያደርጋሉ። በታላቁ በዓል በዒድ አል-ፊጥር ወይም ፆም በሚፈታበት በዓልም የተቀደሰ ተግባርን ይፈፅማሉ። አሏህ ለምድር በረከትን፣ አዝርዒት የሚበቅልበት ዝናብን እንዲያዘንብ፣ የሰውን ልጅ ኹሉ በበረከቱ እንዲመግብ፣ የሰውን ልጅ ኹሉ በአንድነት እንዲሰበስብ፣ በረከትና ሰላም እንዲሰፍን ዱዓ ያደርጋሉ። በተቀደሰው ቀንም የተራበን ያጎርሳሉ፣ የተጠማን ያጠጣሉ፣ የታረዘን ያለብሳሉ፣ ያዘነን ያፅናናሉ፣ የታመመ ምኅረት እንዲያገኝ ዱዓ ያደርጋሉ፣ ወደ ሆስፒታል ሄደው ይጠይቃሉ። ከአላቸው ላይ አካፍለው በዓሉን ያከብራሉ።
የነብዩ መሐመድን አስተምህሮ የተቀበሉት ሙስሊሞች በፅናት ፆመው፣ በፅናት ሰግደው፣ በፅናት ዱዓ አድርገው ሮመዳን በሚጠናቀቅበት በታላቁ ቀን ነብዩ ያዘዙትን መልካም ነገር ያደርጋሉ። በደስታ ያከብሩታል ። በፍቅር ያሳልፉታል።
“የረመዳን፣ የሐጂ ወር የጁማ ቀን
ለተፀፃቾች አላህ ሰጥቶን እንዲታረቀን” እያሉ አሏህን ያመሰግናሉ ። አላህ ተፀፃቾችን፣ አመስጋኞችን፣ ጀነትን ፈላጊዎችን ለመታረቅ ረመዳንን፣ የሐጂ ወርን፣ የጁምዓ ቀንን ሰጥቷልና ስለ ሰጠህን ኹሉ ምሥጋና ለአንተ ይኹን እያሉ ይለምኑታል፣ ያመሰግኑታል። አሏህም ዱዓቸውን ተቀብሎ የልባቸውን መሻት ይፈጸምላቸዋል።
ነብዩ መሐመድ ለተከታዮቻቸው ጸሎት እና ለጋስነታቸውን እንዲያስታውሱ ዒድ አል-ፊጥር እና ዒድ አል- አድሃ የተሰኙ ኹለት ታላላቅ በዓላትን ሰጡ ይላሉ አበው። ሙስሊሞችም ታላላቆቹን በዓላት በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዐት ያከብሯቸዋል።
ዒድ አልፈጥር ዛሬ በሙስሊሞች ዘንድ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዐት እየተከበረ ነው። የነብዩ መሐመድን መልእክተኞች አስቀድማ በተቀበለችው ኢትዮጵያም በድምቀት እየተከበረ ነው። ዒድ አልፈጥር በታላቅ እዝነት፣ በመረዳዳት ፣ በፍቅር የሚከበር በዓል ነው። በዚህ ቀን ደስታ የሚታይበት፣ ፍቅር የሚበዛበት፣ መስጠት የሚበረክትበት ነው። ኢትዮጵያውያንም መረዳዳት ፣ መደጋገፍና አብሮነት ባሕላቸው እና ጌጣቸው ነውና በዓሉን በመረዳዳት ያከብሩታል።
ሙስሊሞች ታላቁን በዓል ሲያክበሩ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የፆም መፍቻ የሌላቸውን ፆም በማስፈታት ነው። በኢትዮጵያ በጦርነት ፣ በድርቅና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እልፍ ዜጎች አሉ። ታላቁን በዓል በቤታቸው፣ ከልጆቻቸው ፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተጠራርተው፣ እርዱን አርደው፣ ተደስተው ማክበር ያልኾነላቸው ብዙዎች ናቸው።
በቤታቸው የሚያከብሩት፣ ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት፣ ለተቸገረ የሚረዱት ትዝ እያላቸው፣ ዛሬ ላይ ለራሳቸውም ያልኾኑ በመጠለያ ውስጥ የሚያሳልፉ ብዙዎች አሉና በታላቁ ቀን አሏህ የሚወደውን አድርጉላቸው። አሏህ በታላቁ በዓል የተቸገሩትን መርዳት ታላቅ ክብር እንደሚያሰጥ አዝዟልና።
ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት፣ በጊዜያዊ መጠለያ ያሉት ብቻ ሳይኾኑ በየጎዳናው፣ በደሳሳ ጎጆዎች እጅ ያጠራቸው፣ በዓሉን በደስታ ማክበር የማይኾንላቸው ሞልተዋልና በተወዳጁ ቀን የሚወደዱውን ለማድረግ ፍጠኑ። ዒድ አልፈጥር አብሮነት የሚጎለብትበት ፣ ወዳጅ ዘመድ የሚጠራበት፣ ጎረቤት ከጎረቤት በደስታ የሚታለፍበት ነውና።
“በሳምንቱ ዒድ በጁምዓ፣ በዓመት ዒዶቹ
ዒድ ሙባረክ ለአሏህ ባሮች ለሙስሊሞቹ ” እንደተባለ ዒድ አልፈጥር በዓልን ለምታከብሩ፣ ለአሏህ ባሮች፣ ለአሏህ ተገዢዎች፣ ለአሏህ ተከታዮች ፣ የአሏህን ትዕዛዛት ጠባቂዎች እንኳን አደረሳችሁ፣ ዒድ ሙባረክ። ከአሏህ ዘንድ ታላቁን በረከት ታገኙ ዘንድ በታላቁ ቀን ታላቅ ነገርን አድርጉ። መልካም በዓል።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/