
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በደምቀት ከሚከበሩት ኹለት ዐመዶች (በዓላት) መካከል አንዱ ኢድ-አልፈጥር ነው፡፡ ዒድ ማለት ትርጉሙ የተከበረ በዓል ማለት ነው፡፡ የረመዳንን ጾም ማብቃት የሚያበስረው ዒድ- አልፈጥር በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ የሕብረት፣ የቤት እና የጎረቤት ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
ከአደባባይ እስከ መስጂድ፤ ከቤት እስከ ጎረቤት በድምቀት የሚከበረው ዒድ- አልፈጥር ተናፋቂ በዓል ነው፡፡
ለአንድ ወር ያክል ራሳቸውን በረመዳን ጾም የሚያነጹት፣ ወደ አሏህ አብዝተው የሚቀርቡት እና የኢማን ዕውቀታቸውን የሚያድሱት የሃይማኖቱ ተከታዮች በዒድ-አልፈጥር በዓል ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን በስኬት ያጠናቅቃሉ፡፡
ረመዳን በኢሰላም ዘንድ ልዩ ወር ነው፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች በወርኃ ረመዳን ፀሐይ ከመውጧቷ በፊት ጀምረው እስክትጠልቅ ድረስ ከምግብ፣ ከውኃ፣ ከመጥፎ ንግግር እና ከክፉ ሥራዎች ኹሉ ርቀው ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው ያስገዛሉ፡፡
የሃይማኖቱ ተከታዮች በረመዳን ወር ቅዱስ ቁርዓንን አንብበው ያጠናቅቃሉ፤ በረመዳን ራሳቸውን በቅዱስ ቁርዓን ዕውቀት አሳድገው ለመመረቅ ዒድ-አልፈጥርን ይጠባበቃሉ፡፡
ረመዳን በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተለየ ነው ሲባል በዚኹ ወር ብቻ የሚገኝ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በመኖሩ እና ለቀሪ ሕይዎት መመሪያ የሚወርድበት ወቅት በመኾኑ ነው፡፡
የሃይማኖቱ ተከታዮች ራሳቸውን በጾም እና በስግደት አድክመው ርሃብ እና ጥም፤ ድህነት እና ጉስቁልና ምን እንደሚመስል የሚረዱበት በረመዳን ነው፡፡ ራስን ዝቅ አድርጎ ለፈጣሪ መገዛት እና መስገድ ያለውን እርካታ በረመዳን ወቅት ይገነዘቡታል፡፡
በአፍጥር ሰዓት እንደ ቤተሰብ ተሰባስቦ እንደ ጎረቤት ተጠራርቶ መመገብ ልዩ ማኅበራዊ ድባብን ይፈጥራል፡፡ ለተቸገሩ መስጠትን፣ ለታመሙ መራራትን እና ለተጎዱ እዝነትን ማድረግ በረመዳን የተለየ ስሜትን ይፈጥራል፡፡
የዚህ ቅዱስ ወር ፍጻሜ እና ምስክሩ ደግሞ ዒድ-አልፈጥር ነው፡፡ ዒድ-አልፈጥር ትርጉሙ ራሱ የጾም ማጠናቀቂያ በዓል ማለት ነው፡፡
ዒድ-አልፈጥር በዓለም ሀገራት ለሦስት ተከታታይ ቀናት በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ቢከበርም የጋራ የሚያደርግ እና ተመሳስሎን የሚፈጥሩ በርካታ ነገሮች አሉት፡፡ አቅም በፈቀደ ጣፋጭ ምግቦች ይዘጋጃሉ እንዲሁም ኹሉም አማኞች በጠዋት ተነስተው ልዩ ሶላትን ወደሚያደርጉበት ቦታ ይተማሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በሌሊት ተነስተው ወደ ስግደት ከመሄዳቸው በፊት ተሰባሰበው ገንፎ በቂቤ ወይም በተልባ ይመገባሉ፡፡ የዒድ-አልፈጥር ስግደት የሚደረገው ሰው ሊያየው ሊለየው በሚችለው እና ኹሉንም አማኝ ሊያሰባስብ በሚችል ገላጣ ቦታ ላይ ይካሄዳል፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች በቡድን በቡድን እየኾኑ እና ተክቢራ እያደረጉ ወደ ስግደቱ ቦታ ላይ ይደርሳሉ፡፡
ከስግደት መልስ በየቤቱ ተደግሶ ከወዳጅ ዘመድ፣ ከጎረቤት እና ቤተሰብ ጋር በመኾን በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ ያለው ለሌለው ተከፋፍሎ እና ተረዳድቶ በየአካባቢው ተጠያይቆ ያልፋል፡፡ በተለይ ዒድ-አልፈጥር በሕጻናት ዘንድ የተለየ ቦታ እና ድባብ አለው፡፡ ሕጻናቱ በዐዳዲስ እና ንጹሕ አልባሳት ተውበው በሰፈራቸው ተሰባስበው ዒድ ሙባረክ ሲሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ይዘይራሉ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸውም ቤት ያፈራውን ይሰጣሉ፡፡
ዒድ-አልፈጥር ለድሆች የተለየች ቀን ናት፡፡ ዒድ-አልፈጥር ለምስኪኖች በረካ የኾነች ዕለት ናት፡፡ ዒድ-አልፈጥር በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተለየ ኾኖ ያልፋል፡፡ ለአንድ ወር የዘለቀው ሃይማኖታዊ ትጋታቸው በስኬት ተጠናቋልና፡፡
መልካም የዒድ-አልፈጥር በዓል!
ምንጭ፡- ኢስላማዊ አስተምህሮ
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/